ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ:-
የእስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችን…የዴሞክራሲያዊ መብት የመጠቀም የትግል እንቅስቃሴ ሲመለከት እንደሚዳቋ እየበረገገ የሚስፈነጠረው ማን ነው?
የኢትዮጵያ የነጻው ፕሬስ እና ጦማርያን ቁንጮ የሆነው እስክንድር ነጋ ሀሳቡን በነጻ በመግለጹ ብቻ በአምባገነኑ የወሮበላ ቡድን ስብስብ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት በገዥው አካል የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ሟቹ መለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ስር እንዲውል እና የ18 ዓመቱ የሸፍጥ እስራት እንዲበየንበት ተደርጓል፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ማናቸውም ጋዜጠኞች የበለጠ እስክንድር ነጋን ይፈራዉና ይጠላው ነበር፡፡ ዝሆን አይጦችን “ይፈራል” ከሚለው ኢ-ስነ አመክንዮ አንጻር በተመሳሳለ መልኩ መለስም እስክንድር ነጋን እንደጦር ይፈራው ነበር፡፡
በቅርቡ እስክንድር ከማጎሪያው እስር ቤት ለ8 ዓመት ልጁ ለናፍቆት እንዲህ የሚል ግልጽ ደብዳቤ ጽፏል፣ “እንዲያው ሁኔታውን ሳየው እያለሁ የሌለሁ የዘፈቀደ አባት ሆኛለሁ፣ ምክንያቱም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈረንሳዮች ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍቅር እያሉ ደጋግመው ይጠሯቸው የነበሩትን ሶስት ቀላል ቃላትን በመውሰድ እኔም በሀገሬ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍቅር እንዲሰፍን በማሰብ እነዚህን ቃላት በማስተጋባቴ ነው በሸፍጠኞች ለእስር የተዳረግሁት“ ብሏል፡፡ እስክንድር ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለአብሮነት ፍቅር ጦማሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለእኔ የጀግናዬ ተምሳሌት የሚሆነው!











