ተሰባስበን በመጠጣት ላይ እያለን እንዳጋጣሚ አንዱ ጓደኛችን ቪያግራ ስለሚባለው
የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት አነሳን፡፡ እሱ እንደነገረን ግን የስንፈተ ወሲብ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ በሞቀ ስሜት
ለመቆየት የሚያስችል እና በቅርብ ጓደኛው ከዱባይ እንዳመጣለት ነገረን፡፡ የተወሰኑት በእረፍትና በድፍረት መሀከል
ሆነው እስኪ እንሞክረው ሲሉ ተስማሙ፡፡
እኔና አንዱ ጓደኛችን በድምፅ ተአቅቦ ዝም ብለን ማዳመጥ ቀጠልን፡፡ እርግጥ
አልፎ አልፎ ከባለቤቴ ጋር ወሲብ ለመፈፀም ስፈልግ ስሜቴ ስለማይነቃቃ ባለቤቴ ላይ መከፋት አያለሁ፡፡ እናም
እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር እንደጓደኞቼ ምን አለ ብጠቀም ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ግን ስጋቴ ከዛ በኋላስ ምን
ሁኔታ ውስጥ እገኛለሁ ብዬ ሳስብ ይጨንቀኛል፡፡ ታዲያ ለዚህ ብዬ ባለሙያዎችን ለማማከር ወደ ህክምና ብሄድ ቅብጠት
ይሆንብኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጠቀም አልጠቀም በሚል ውዝግብ ለመውጣት ሁሉንም ለመርሳት ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን
መድኃኒቱን ከሌላ ሰው እጅ በማግኘቴ ገዝቼ አስቀምጬዋለሁ፡፡ እንደው ምን አልባት ቢያስፈልግ ብዬ፡፡ ሲል ስሙን
እንዳልጠቅስ ከነማስጠንቀቂያ የነገረኝ ጓደኛዬ ያነሳልኝን ጨዋታ ተመርኩዤ በዚህና መሰል የስንፈተ ወሲብና አማራጭ
መድኃኒቶች ዙሪያ ባለሙያ አነጋግሬ ይዤላችሁ ቀረብኩ፡፡ ችግሩ በአበባ ወጣቶች ላይ መንሰራፋቱን ከተለያዩ ሰዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ እናስ ህክምናው ምን መልስ አለው፡፡ ዶ/ር ድጋፌ ፀጋዬ የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ከስንፈተ ወሲብ በመነሳት እንዲህ ያስረዱናል፡፡
በወንዶች
ላይ የሚታዩት የስንፈተ ወሲብ ችግሮችን በሶስት መልኩ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው የብልት መነሳት ችግር
(Reactive dysfunction) ወይም የወሲብ ስንፈት እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ሁለተኛው እርካታ ደረጃ
ሳይደርስ የዘር ፈሳሽ ማውጣት (premature ejaculation) ሶስተኛው የወሲብ ስሜት አልባነት ናቸው፡፡
የመጀመሪያውን ስንመለከት የብልት መነሳት ችግር ያለባቸው ሰዎችን በብዛት እናገኛለን፡፡ በተለያየ ዕድሜ ክልል
ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቢያጠቃም በተደጋጋሚ ወደ ህክምና የሚመጡት ግን ዕድሜያቸው ከስልሳ ዓመት በላይ
በሆኑት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶችም ሪፖርት ሊያደርጉ ችለዋል፡፡
ችግሩ ከየት ይነሳል? ብለን ስንመለከት ሁለት አይነት ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ከስነ ልቦና
(Phylogenic) ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኦርጋኒክ (ምክንያታዊ) የሆኑ የተለያዩ በሽታዎች
በሚፈጥሩት ተፅዕኖ ይከሰታል፡፡ ዋነኛው የስንፈተ ወሲብ መንስኤ ተብሎ የሚጠቀሰው የስነ-ልቦና ጉዳይ ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ ጭንቀት እና የተለያዩ ሀሳቦች ለስንፈተ ወሲብ ያጋልጡናል፡፡ ሌላው
የአካል ድካም እና መዛል ነው፡፡ ለምሳሌ አካሉ በብዙ ስራ ሲንቀሳቀስ የዋለ ሰው በግንኙነት ወቅት የብልት
መነሳት፣ ስሜት ማጣት አሊያም ለወሲብ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ብልት እርቀት ደረጃ ሳይደርስ
አስቀድሞ ጥንካሬውን የሚያጣበት ምክንያት የሀሳቦችን መደራረብ በመኖራቸው ነው፡፡ ይህን በምሳሌ ብንመለከት ከፍቅር
ጓደኛው ጋር ወሲብ በሚፈፅምበት ወቅት ነጋዴ ከሆነ ስለተጋረጠበት የንግድ ችግር የመስሪያ ቤት ኃላፊ ከሆነ
ስላልተሳኩ የድርጅቱ እቅዶች ካለው ኃላፊነት ጫና የተነሳ በአዕምሮው ሊመላለሱበት ይችላሉ፡፡ ይህም ጥሩ ያልሆነ
ግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ግብረስጋ ግንኙነት ደግሞ በባህሪው ሙሉ ለሙሉ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው በባልና በሚስት መካከል
አለመግባባት /ቅሬታ በሚኖርበት ጊዜ ተነሳሽነቱ በሁለቱም ወገን ይቀንሳል፡፡ በቀጥታ ከአዕምሮ ጋር የሚያያይዘው
የግብረ ስጋ ግንኙነት ስነ-ልቦናና አካላዊ ዝግጁነት ጅማሪ አይምሮ ውስጥ በሚፈጠር ኬሚካሎች አማካይነት ነው፡፡
የአንድሮጂን ኬሚካል መመረት ወንዶች ላይ ብዛት የደም ፍሰቱ ወደ ብልት እንዲሆን በማድረግ ብልት እንዲነሳ
ያደርጋል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ይህን ኬሚካላዊ የዝግጁነት ቅመም እንዳይፈጠር ስለሚያደርጉ የፓርኖግራፊ
ፊልሞች በሚፈጥሩት፣ በአደጋ (ግጭት) ጫና፣ በሃዘን፣ በድካም መካከል ስንፈተ ወሲብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም
ነው ብልት የመነሳት ችግር የሚያጋጥመው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ኦርጋኒክ የሚባለው ሲሆን የተለያዩ ህመሞችን ተከትሎ የሚመጣ የወሲብ ችግር ሲሆን ስኳር፣
ደም ግፊትና የአባላዘር በሽታዎች ሲያጠቁን ነው፡፡ ሌላው የተለያዩ አደገኛ መድኃኒቶች አልኮልና ጫት የደም ዝውውርን
የሚቀንሱ ናቸው፡፡ በግንኙነት ወቅት ብልት እንዲነሳ ካስፈለገ ከፍተኛ የደም ዝውውር ሊኖር ይገባል፡፡ በቂ የሆነ
የነርቭ መነቃቃትም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሉት ጫና ደግሞ በወሲብ የመነቃቃትና ትክክለኛውን ኡደት
ጠብቆ በሚጠበቀው ደረጃ እርካታ ላይ ለመድረስ እንዳይችሉ እንቅፋት ይሆናል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉን ህክምናዊ መፍትሄዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ስንመለከት በቅድሚያ
ወሲባዊ ህይወት እንደ ምስጢር በየሰው አዕምሮ ውስጥ በመቀበሩ ችግሮችን አውጥቶ ከህክምና ባለሙያዎች እና ከትዳር
አጋር ወይም ፍቅረኛ ጋር ለመወያየት አለመቻል በራሱ ችግሩን የሚያባብሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከህክምናው ጋር
የተገናኙትም በትክክል ህክምና ተከታትለው ሲያጠናቅቁ አይታዩም፡፡ በመሆኑም በቀላሉ መፍትሄ ላያገኙ ከሚችሉበት
አጋጣሚ በመራቅ ለተለያዩ አላሰፈላጊ የጊዜና ገንዘብ ብክነቶች ይዳረጋሉ፡፡
በመሆኑም መፍትሄው የመጀመሪያው እርምጃ የችግሩን መነሻ ምክንያትን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ እንደመንስኤው የተለያዩ
ህክምናዎች እንዲሰጡበት ያደርጋል፡፡ ከስነ-ልቦና ጋር የተያያዘ ከሆነ ያለመድኃኒት ሊስተካከል ይችላል፡፡ ያለውን
ችግር ማለትም አካላዊና አዕምሮአዊ ሁኔታ የስነ-ልቦና ድጋፍ በማግኘት በማስተካከል ሊቀረፍ ይችላል፡፡ ከተለያዩ
ህመሞች የሚነሳው የስንፈተ ወሲብ ችግር ከመቆጣጠርና ከመከላከል ባሻገር መድኃኒቶችን ለደም የሚገባውን የወሲብ ስሜት
መጠበቅ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ በዚህ ውስጥ አልፈን መፍትሄ ካልተገኘ የመጨረሻው አማራጭ ረዳት መድኃኒቶችን
ማካተት ይሆናል፡፡
እነዚህ መድኃኒቶች ያላቸው ጥቅም ምንድን ነው ካልን የደም ዝውውር በመጨመር ነርቮች እንዲነቃቁ የወንዱ ብልት
አካባቢ ያሉት ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ እና ብልት እንዲጠነክር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ መድኃኒቱም በህክምና ባለሙያ
ትዕዛዝ መሰረት በጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም አይነትና መጠኑ ሊያውቅ የሚችለው በህክምናው ዘርፍ በቂ
ትምህርትና ልምድ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ተያይዘው ለሚመጡ ተጓዳኝ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ተጠንተው ቅድመ እና ድህረ
ጥንቃቄ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ችግሩ እንዲቀረፍ 50 በመቶ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ከችግሩ አይነትና መጠን ተነስተን
ነው መድኃኒቶቹን የምናዘው፡፡
መድኃኒቶች ያሏቸውን ጥቅም ያህል ብዙ ጉዳቶችንም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው የባለሙያ ድጋፍ
አስፈላጊነት ሁኔታዎችን በማገነዛብ መድኃኒቶችን ማዘዝ ውጤታቸውንም መከታተል ከተቻለ መድኃኒቱ ያለምንም ጉዳት
የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ይረዳዋል፡፡
መድኃኒቱ መታዘዝ ያለበትን ወቅት በተመለከተ ምክንያቱ ታውቆ አማራጭ መፍትሄዎች ታይተው ግድ የሚሉ ሁኔታዎች
ሲፈጠሩ ነው፡፡ የመድኃኒቱ መጠን እና አይነት መቼስ መውሰድ አለበት? እነማንናቸው መድኃኒቱን መውሰድ የሚችሉት? እነማንስ መድኃኒቱንሲወስዱ ችግሮች ይገጥማቸዋል? የሚለውን የሚወስነው ባለሙያው ነው፡፡
ሰዎች
ከተለያዩ ምንጮች ካገኟቸው መረጃዎች ተነስተው መድኃኒቶችን ያለህክምና ትዕዛዝ ይወስዳሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ
ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሄ ሊሰጥ ወደሚችለው ባለሙያ ለመሄድ ያለው ተነሳሽነት በጣም ዝቅተኛ መሆን፣ የወሲብ
ምስጢራዊነት እሳቤ፣ የመድኃኒቶቹን የጎንዮሽ ችግር ያለመረዳት፤ የጓደኛና የተለያዩ የወሲብ ትዕይንቶች ከሚያስከትሉት
ጫና የተነሳ ነው፡፡ ችግሩ ሳይኖር መድኃኒቶችን አፈላልጎ መጠቀም የመቻል አቅምና ድፍረት በተጨማሪ ህገ-ወጥ
የመድኃኒት ዝውውር መኖሩ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
ለምሳሌ ቪያግራ ተሰኘውን መድኃኒት በተለያየ መልኩ ማግኘት የቻሉ ሰዎች ዝም ብለው ቢጠቀሙበት ምን ያስከትላል
ስንል የልብ ድካም ያለባቸው (አርቴፊሻል መሳሪያዎች በልባቸው የተገጠመላቸው ሰዎች) ችግር ይገጠማቸዋል፡፡
መድኃኒቶቹ በዚህ ሁኔታ ከጥቅም ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡
በተጨማሪም ከልክ ያለፈ የብልት መነቃቃት ሳቢያ ብልት ቆሞ ላይመለስ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህም
Persistence stimulation ያስከትላል፡፡ ሌላው በግንኙነት ወቅት ብልት በጣም ከመወጣጠሩ የተነሳ የብልት
ዘንግ ስብራት ሊያጋጥም የሚችላቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ አንድም ጊዜያዊ ከፍተኛ ህመም፡፡ በተጨማሪም የልብ ስራን
የማዛባት ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶቹን ማግኘት ስለተቻለ ብቻ መጠቀሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ብዙ ጊዜ መድኃኒቱ እንደ
ችግሩ ሁኔታ ታይቶ በቀን አንዴ ግንኙነት ከማድረጊያ ጊዜ አንድ ሰዓት ቀድሞ እንዲወሰድ የሚታዘዝ ሲሆን በተደጋጋሚ
እንዲወሰድ አይመከርም፡፡
መድኃኒቱን ደጋግሞ መውሰድ አስቀድመን የጠቀስናቸውን ችግሮችን ማባባስ ያስከትላል፡፡ በተለምዶ የወንዶች ብልት
ከተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለረጅም ሰዓት ተነስቶ በሚቆይበት ወቅት እጅግ በጣም
ከፍተኛ ህመም አለው፡፡ መልሶ ግንኙነት ማድረግ በሚያስፈልግበት ጊዜም ሊያስቸግር ይችላል፡፡
እንደ ቪያግራ ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም የጀመረ ሰው የጥገኝነት ባህሪ ስለሚዋሃደው ያለው በራስ መተማመን
ይቀንሳል፡፡ ያለመድኃኒቱ በተፈጥሮአዊ መንገድ ለወሲብ መዘጋጀት እና መደሰትም ያቅተዋል፡፡ የቪያግራ መድኃኒት
በኪኒን መልክ የሚሰጥ ሲሆን አልፎም በመርፌ መልክ ወንድነትን የሚያላብሰው የቴስቴስትሮን ሆርሞን በጊዜ ሂደት
ሲቀንስ ቅመም አመንጭውን ክፍል ለማነቃቃት (መጠኑን ለመጨመር) የሚያስችል በሳምንት አንድ መርፌ ይሰጣል፡፡
ስለሆነም ስንፈተ ወሲብ ያስከተለው የቴስቴስትሮን ማነስ፣ የስነ-ልቦና ጫና አካላዊ ድካም ወዘተ… መንስኤዎች ውስጥ
የትኛው እንደሆነ ታውቆ መድኃኒቶች ይመረጣሉ፡፡
አብዛኛው ስንፈተ ወሲብ ችግሮች ባህሪን ከማስተካከል፣ ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እና ምክር በመስጠት ያለመድኃኒት
ሊታከሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ህክምና ቦታ መጥተው ፈራ ተባ እያሉ የመናገር ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ይህ ተወግዶ ግልፅነት
ከዳበረ ችግሩ እንዲቀረፍ ይረዳል፡፡ በወጣቶች በኩል ለዚህ ችግር የሚጋለጡበት ዋነኛ ምክንያት በሱስ መጠመድ ሲሆን
በተለይም ለረጅም ጊዜ ጫት መቃም እና በብዛት አልኮል የሚወስዱ ከሆነ ለስንፈተ ወሲብ ይጋለጣሉ፡፡ ከጋብቻ በፊት
የሚኖር ከግብረ ስጋ ግንኙነት ለስንፈተ ወሲብ ያጋልጣል፡፡ በደንብ ሳይተዋወቁ ስሜታዊ ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ
ሰዎች በሚያድርባቸው ስነ-ልቦና ጫና የስንፈተ ወሲብ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
እኛ አገር ባይኖርም በባለትዳሮች መሀከል የሚደረግ የወሲብ ህክምና በተለያዩ ሀገሮች የሚሰጥ ሲሆን ከትዳር
አጋር ጋር በሚያጋጥም የወሲብ አለመጣጣም ችግሮችን በማጥናት መፍትሄ ማስቀመጥ የሚቻልበት ሂደት ነው፡፡ በወሲብ
ህይወት ውስጥ ዝግጁነት እና ግልፅነት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ ስለ ወሲብ ከትዳር አጋር
(ፍቅረኛ) ጋር በግልፅ በማውራት ለችግሮቹ መፍትሄ ለመፈለግ ይረዳል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚደርስ የትዳር መፍረሶችን
መታደግ ይቻላል፡፡ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እና በተለይም ቤተሰባዊ መረዳዳት እና በወሲብ ወቅት ማዘጋጀት፣ እራስን
የተረጋጋ፣ ፍቅር የተሞላበት እና መተማመን የሰፈነበት ወሲብ ሙሉ ደስታን ያጎናፅፋል፡፡
ቪያግራን ወንዶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሲጠቀሙበት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም የታወቀ ሲሆን ይህ መድኃኒት
ለሴቶች ጥቅም ስለማይኖረው በድፍረት እና ባለማወቅ የወሲብ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለው ሴቶች እንዳይቀጠሙበት
እናስጠነቅቃለን፡፡
መድኃኒቶች ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ሲገቡ ጥራታቸው ያልተፈተነ፣ የማዳን አቅማቸው፣ የጎንዮሽ ጉዳታቸው፣
የአወሳሰድ መጠናቸውና ልዩ ጥቅም የሚያስገኝባቸው ችግራዊ መንስኤዎች ስለማይታወቁ ያለሐኪም ትዕዛዝ መውሰዱ ለከፋ
ችግር ያጋልጣሉና የጥንቃቄ እርምጃው እየተስተዋለ ሊሆን ይገባዋል፡፡
Source: http://www.tenaadam.com/
No comments:
Post a Comment