አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በአዲስ አበባ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ / የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ጎን ለጎን ተገናኝተው የተደራደሩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው የቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር በ60 ቀናት ውስጥ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድርድር ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።
ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ሁለቱን ወገኖች አግኝተው ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማያም ኪርና ማቻር በ60 ቀናት ውስጥ የሽግግር መንግስትን እንዴት፣ መቼና በማን ይመስረት የሚለውን ድርድር አካሂደው ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
በኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ አቶ ሀይለማርያም ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ግጭት ተወናዮች አዲስ አበባ ላይ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰዋል ሲሉም ወቅሰዋል።
በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ጦርነቱን የመቀጠል ዝንባሌ ታይቶ የነበረ ቢሆንም፥ ኪርና ማቻር ዳግም ለሰላም ስምምነቱ ዳግም ቃላቸውን ማደሳቸውን አንስተዋል አቶ ሀይለማርያም።
ሁለቱ ሰዎች ለገቡት ስምምነት የማይገዙ ከሆነ ኢጋድ ማእቀቦችን ሊጥል እንደሚችልም ነው የገለፁት።
የትናንቱ የኢጋድ የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ማምሻውን ተጠናቋል።
መሪዎቹ ባወጡትም መግለጫ በተቀመጠው የ60 ቀናት ገደብ ውስጥ አሳታፊ የአንድነት የሽግግር መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድርድር ሁለቱ ወገኖች እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።
በፈረንጆቹ ግንቦት 9 ቀን 2014 ላይ ሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር የተፈራረሙትን የተኩስው አቁም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩና ለረድኤት ስራዎች ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹም ነው የጠየቁት።
በጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የኡጋንዳና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንቶች፣ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የሱዳንና ኬኒያ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።
Source: www.fanabc.com
No comments:
Post a Comment