Time in Ethiopia:

Dec 3, 2013

የዓርብ ግዞተኞች ፪

Geez Bet | Tuesday, December 03, 2013
(አስራት አብርሃም)
ባለፈው ሳምንት በዚህ ርዕስ ልፅፈው የፈለኩትን አልጨረስኩም ነበርና እነሆ ዛሬ የመጨረሻውን ክፍል ይዤ ቀርቤያለሁ። አብዛኛውን በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተገኝቶ የተያዘ (ከመንገድ የተያዙም ነበሩበት) እስረኛ ቪድዮ ቀርፀው፤ ስሙንም መዝግበው ወደ አስር ሰዓት አከባቢ አስናበቱት። እኛ አስራ አምስት የምንሆን ግን ለይተው እንድንቆይ አደረጉን። ማደራችን እንደሆነ አስብኩ፤ በንጋታው ቅዳሜ በመሆኑ ከፈለጉም እስከሰኞ ሊያቆዩን እንደሚችሉም አስብኩ። ለሁሌስ ቢሆን ሊያስሩን ከፈለጉ ማን ይከለክላቸዋል፤ ወደ ቃሊቲም ሊልኩን ይችላሉ።

ብዙዎቹ ግን ምንም ጥፋት እንደሌለን እና በአጭር ጊዜ ውስጥም ልንፈታ እንደምንችል እየተናገሩ ራሳችውን አበርትተው እኛንም ያበረታቱን ነበር። ለነገሩ እዚያ በእንዲህ ባለ ሁኔታ እንድንታሰር የሆነው እኮ ወንጀል ስርተን አልነበረም። እነርሱ ሊያስሩን ስለፈለጉ እንጂ! ስለዚህ የእኛ መፈታትና መታሰር ወይም በእስር መቆየት የሚወስነው የሰራነው ወንጅል ቅለትና ከብደት ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎትና መልካም ፍቃድ ነው። ብቻ እኛ የታሰርነው በሀገራችን በመሆኑ፤ በሰው ሀገር እየተሰቃዩ ከነበሩት ወገኖቻችን
አንፃር የእኛ መታሰር ቀላል ነው ማለት የሚቻል ነው። ቢያንስ እንደእኛ እኩል የሚያዝኑ የተወሰኑ ፖሊሶች ነበሩ። ከሁኔታው እንደታዘብኩት ከሆነ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ሆኖባቸው ነው እንጂ እኛን አስሮ ለመጠበቅ ምንም ዓይነት ፍላጎት የላቸውም። እንዳንዶቹማ ሲያሳዝኑ!
ማታም ሊሆን ሆነ! ከዚያም “እዚህ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ማደርያ የለም” ተባለና ወደ ጨርቆስ ፖፑላሬ ፖሊስ ጣቢያ ትሄዳለችሁ ተባልን፤ እዚያ ከነበሩ አንዳንድ ፖሊሶች ጋር ጥሩ መግባባት ጀምረን ስለነበር፣ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል እንደሚባለው ሀገርኛ ብሂልም ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ እዚያው በዋልንበት ማደሩ መርጠነው ነበር። ነገር ግን እኛ እንደምንፈልገው ሳይሆን እነርሱ እንደፈለጉት የሆን ዘንድ ሁኔታውና ቦታው ግድ የሚልነውና እናድርበት ወደ ተመደበልን ቦታ ለመውሰድ በአንድ ትልቅ አውቶብስ ውስጥ አስገቡን። በዚህ ጊዜ ፖሊሶቹ በኦሮምኛ የሆነ የሆነ ነገር ከተነጋገሩና አንዱ “ቶኮ… ለማ… ሰዲ… አፉር… “ ብሎ ከቆጠረን በኋላ ጎዞ ወደ ፖፑላሬ ፖሊስ ጣቢያ ሆነ። በዚህ ምክንያት “እንዴት ነው የላንቻ ፖሊሶች በብሄር እየተደራጁ ነው እንዴ ጥበቃ የሚወጡት?” ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። ምክንያቱም ቀን ላይ የነበሩ ፖሊሶች አብዛኞቹ ትግርኛ የሚናገሩ የነበሩ ሲሆን ወደ ማታ ላይ ተቀይረው የመጡት ደግሞ አብዛኞቹ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሆነው ስላገኘኋቸው ነው።
እግዚሄር ይስጣቸው እንኳን እያንዳንዱ ብሄረሰብ የመጠበቅ ተራ እስኪደርሰው ድረስ ብለው አስረውን ለሰማኒያ ቀናት አላቆዩን። ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የበዕዉቀቱ ቀልድ ትዝ አለኝ፤ አንዱ ሰውዬ ሁለት ብሄረሰቦች በሚኖሩበት ክልል የሆነ ወንጀል ሰርቶ በመገኘቱ ወደ ፍርድ ቤት ይቀርባል፤ የአንዱ ብሄረሰብ አባል የሆነ የመሀል ዳኛ ሁለት ዓመት ይፈረድበታል፤ ይህን የታዘበው አጠገቡ የነበረው የሌላኛው ብሄር አባል የሆነ ዳኛ ደግሞ ከዚያኛው ብሄር ጋር እኩል መሆኑን ለማሳየት በማሳብ እኔም ሁለት አመት ጨምሬለታለሁ ብሎ በድምሩ የአራት ዓመት እስራት ተፈረደበት ነው። የእኛም ጉዳይ እንደዚያ ሊሆን ትንሽ ነበር የቀረው ነበር። የሆነ ሆኖ አውቶብሳችን ፖፑላሬ ፖሊስ ጣቢያ ደርሳ ቆመች። አጅበውን የመጡ ፖሊሶች እና የጨርቆስ ፖፑላሬ ፖሊሶች የእስረኞች ርክክብ አደረጉ። እንደ አዲስ ተቆጠረን፤ እንደ አዲስ ተመዘገብን። ተረካቢና አስረካቢ ፖሊሶች ተፈራረሙ እና በስርዓት ተረካከቡ። ከዚያ ይዘውን የመጡት ፖሊሶች “አይዟችሁ! እሺ እነርሱም ጥሩ ፖሊሶች ናቸው፤ ይተባበሩዋቸዋል። ደህና እደሩ!” ሲሉን ከእኛ ውስጥ አንዱ "ችግር የለም፤ መቼም እዚህ የሳውዲ ፖሊስ አይኖርም!” ሲል ጊዜ ሁላችንም ሳቅን ፖሊሶቹም ጭምር! በሀገር ሲኮን እንዲህም መቀለድ ይቻላል! ወደ ቃሊቲ ከገቡ በኋላ እንዲህ መቀለድ መቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም። የሀገራችን የእስር ቤት ሁኔታ ምን እንደሚመስልና አስከፊነቱም እስከምን ድረስ እንደሆነ እንሰማለን፤ እናውቃለንም።
አጋጣሚ ሆኖ ፖፑላሬ ፖሊስ ጣቢያ ብዙም እስረኛ አልነበረምና ለወንዶቹ ለብቻችን አንድ ክፍል ተሰጠን። ክፍሉም ገና አዲስ የተሰራ፤ ለመጀመርያ ጊዜ በባለፈው የሞስሊሞች ግርግር ጊዜ የተያዙ የታሰሩበት አዲስ እና ያማረ ክፍል ስለነበር ለመጀመርያ ጊዜ የታሰረ ሰው ስለአገራችን የእስር ቤት ሁኔታ ፍፁም የተሳሳተ ምስል የሚሰጥ ነው። ለነገሩ እኔም ከአሁን በፊት በዓረና ዋና ጽህፈት ቤት ስሰራ አንዳንድ ጊዜ ለቀናት የምታሰርበት ሁኔታ ስለነበር የእስር ቤቶቹ ሁኔታ፣ ጥበትና ቆሻሻነት በደንብ አውቃዋለሁ። ከእኛ ውስጥ ሁለት ሴቶች ነበሩ እነርሱ እዚያ ከነበሩ ሌሎች ሶስት እስረኞች ጋር ቀላቀሏቸው። ከዚያ ከእስረኛ ቤተሰቦች የመጣውን ምግብ በአንድ
አስራት አብርሃም
ትልቅ ጠረጴዛ ላይ ቀረበና በደንብ ተመገብን። በዚህ ጊዜ ጓደኞቼ፣ የዓረና ወጣቶች ፍራሽና ብርድ ልብስ ይዞውልኝ መጡ። ከዚያ በኋላ ወደ ሽንት ቤት መሄድ የሚፈልግ ካለ እንዲሄድ ፖሊሶቹ ሲናገሩ እኔም በተራዬ ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ ተነሳሁ፤ በዚህ ጊዜ ሊያሸናኝ የወሰደኝ ፖሊስ አብሮኝ ወደ ሽንት ቤቱ ሊገባ ትንሽ ቀርቶት ነበርና በቀልድ አስመስዬ “እንዲህ በትልቅ አጥር በተከበበ ግቢ ወዴት እንዳልጠፋ ነው?| ስለው “በአጥር ዘለህ ብትጠፋስ” አለኝ እርሱም እየሳቀ። “ሰልፍ ወጣሁ እንጂ አጥር የሚያዘል ወንጀል አልሰራሁ” አልኩት። እንዲህ የማሸናቱ ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ ፖሊሶቹ እንደገና ቆጥረውን ወደ ክፍላችን አስገብተው ዘግቡን። በመጨረሻ የተገኘውን ምንጣፍ ሁሉ አንጥፈን ጋደም አልንና ወግና ቀልድ ተጀመረ። እኔ ከሁሉም በላይ የሳቀኝ ጨለማው ከመወፈሩና ከመጥቁሩ የተነሳ የሀገረው ሰው ጨለማውን እንደ እንጨት ተደግፎት ይቆማል ስለተባለው ቦታ ነው። ይሄ ቦታ መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን አለበት። ከዚያ ዘላለም የተባለ የራስታ ሽሩባ የተሰራ ልጅ የቦብ ማርለይን “Slave driver” የተባለውን
ሰፈን እንዲህ ዘፈነልን፤
   Ooh-ooh-oo-ooh. Oo-oo-ooh! Oo-oo-ooh. 
Slave driver, the table is turn; (catch a fire) 
Catch a fire, so you can get burn, now. (catch a fire) 
Slave driver, the table is turn; (catch a fire) 
Catch a fire: gonna get burn. (catch a fire) Wo, now! 
Ev'rytime I hear the crack of a whip, 
My blood runs cold. 
I remember on the slave ship, 
How they brutalize the very souls. 
Today they say that we are free, 
Only to be chained in poverty. 
Good God, I think it's illiteracy; 
It's only a machine that makes money. 
Slave driver, the table is turn, y'all. Ooh-ooh-oo-ooh. 
Slave driver, uh! The table is turn, baby, now; (catch a fire) 
Catch a fire, so you can get burn, baby, now. (catch a fire) 
Slave driver, the table is turn, y'all; (catch a fire) 
Catch a fire: so you can get burn, now. (catch a fire) 
Ev'rytime I hear the crack of a whip, 
My blood runs cold. 
I remember on the slave ship, 
How they brutalize the very soul. 
O God, have mercy on our souls! 
Oh, slave driver, the table is turn, y'all; (catch a fire) 
Catch a fire, so you can get burn. (catch a fire) 
Slave driver, the table is turn, y'all; (catch a fire) 
Catch a fire ... /fade out/
በእውነቱ ልጁ ድምፃዊ እንደሆነ ከሁኔታው ብረዳም የቦብ ማርለይን ዘፈን የድምፁን ትክክለኛ ቅላፄ ጭምር አስመስሎ ስለዘፈነው እኔ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ከራሱ ከቦብ ጋር የታሰርኩ ያህል ነው የተሰማኝ። በዚያው ብዙ ብዙ እያወራንና እየተጫወትን አመሸን። የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል የሆነው ወረታው ዋሴ ሰልፉ ላይ ፌደራል ፖሊሶቹ በብዙ ቦታ ላይ በዱላ በኃይል ተመቶውት ስለነበረ፣
ቀድመው ከተኙት ውስጥ ነበር። እኔም ትንሽ ቆይቼ እንቅልፍ ወሰደኝ። ሌሊት ላይ መኝታው ሲቆረቁረኝ ጊዜ “የት ነው እንዴ ያለሁት ብዬ?!” እንቅልፍ በተጫጫነው ሁኔታ ማሰብ ያዝኩኝ፤ ከአልጋም የወደቁ መሰለኝ። ነገር ግን በቀኘም በግራዬም ለሌች ሰዎች እንዳሉ ስገነዘብ ቤት እንዳልሆንኩ ገባኝ። በዚህ ጊዜ በከፊል ነቃሁ፤ አንድ ሰውም ግርማ ሞጎስ ባለው ሁኔታ በኃይል ያንኮራፋ ነበር፤ ጉሬዛ የተባለው የድሮ በሬያችን ይመስላል። ጉሬዛ በሬያችን የምንጋው ንጉስ፤ የጋጡ ጌታ ነበርና ንጉስነቱን ሁሉም እንዲሰማለት ነው መስል ሲያንኮራፋ የሚያገሳ አንበሳ ነበር የሚመስለው።
ከዚያ በኋላ እየተገላበጥኩ ብዙ ቆየሁ። በዚህ ጊዜ አንዱ ሌላኛውን ሰዓት ሲጠይቀው “አስራ አንድ ሰዓት ሆኗል” አለው። ከዚያ በኋላ ግን ሌሊቱ ሳይነጋ በጣም ረጅም ጊዜ በመቆየቱ “እንዴት ነው ይሄ ሰውዬ በኤርትራ አቋጣጠር ነበር እንዴ የነገረው” እያልኩ አማሁት።
በነጋታው ቅዳሜ ዕለት እጃችን እንደ ወንጀለኛ በካቴና ታስሮ ሜክስኮ ወደሚገኘው የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተወሰድን። ዳኛዋ በጣም ልጅ እግር ነች የመርማሪውን ክስ በፅሞና ሰማች በኋላ ከምትፅፍበት ቀና ብላ አየችንና “የምትሉት ነገር አለ?” አለች። ሰልፍ መውጣታችን ትክክል ነው። ሌሎች በመርማሪው በእኩል የተባሉትን ነገሮች ግን አላደርግንም አልን። ቃላችንን ሰምታ “በአምስት መቶ ብር ዋስ ይለቀቁ።” ብላ መዝገቡን ዘጋችው። ከፍርደ ቤቱ ከወጣን በኋላ አምስት መቶ ብር ይቅርና በመታወቂያ ዋስ ትለቀቃላችሁ ተብለን ወደ ፖፑላሬ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። በነገራችን ላይ ዳኛዋ በአምስት መቶ ብር ዋስ ይውጡ ብላ ከወሰነችና መዝገቡን ከዘጋች በኋላ እነርሱ በራሳቸው ጊዜ በመታወቂያ ብቻ እንድንወጣ ማደረጋቸው ምን ይባላል?! የዳኛዋ ውሳኔ የማያከብሩ ከሆነ ደግሞ መጀመርያውኑ ለምን ወደ ፍርድ ቤት አመጡን! ወይስ ዳኛዋ ሊታዘቧት ፈልገው ኖሯል። ምክንያቱም ለፍርድ ቤት ውሳኔ የማይገዙ ከሆነ እዚያው በራሳቸው ጊዜ እንደሚደረግ አድርገው ሊፈቱን ይችሉ ነበር ማለት ነው። የሚገርመው ደግሞ ፖፑላሬ ፖሊስ ከደረስብን በኋላ የዋስ መሙያ ፎርም አልቋል፤ የለም ተባለና እንደገና ጭነውን በመጀመርያ ወደ ታሰርንበት የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን።
እዚያ እንንደደረስን አራት ኪሎ ታስረው የነበሩትን እነ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ሌሊት ላይ ራሳቸውን በራሳቸው ዋስ እንዲሆኑ ተደርገው ተፈተው ኖሮ እኛን ሊጠይቁ መጥተው እዚያው ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ አገኘናቸው። ዋስ እንደሚያስፈልግ ሲነገሯቸው እዚያ የነበርነውን ሁሉ ሊዋሱን የዋስ ፎርሙን መሙላት ጀመሩ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ጓደኞቼም ቤተሰቦቼም መጥተው ስለነበር፤ አባቴ እንዲዋሰኝ ሆኖ በዋስ ተፈታሁኝ። ከዚያ ወጥተን ወደ ቤታችን ጉዞ ሆነ። አንድ ቅን ወገንም በራሱ መኪና ሸኘን። ውጪ በጎደናው ጭፈራ በጭፈራ ሆኖ ነበር። ኢትዮጵያ ከናይጀርያ ጋር የመልስ ጨዋታ የሚያደርጉበት ቀን ነበርና ሰው ሁሉ በመኪናም ብእግሩም እየሆነ ይጨፍራል። መንገድ ለመንገድ ይሮጣል፤ ለመጀመርያ ጊዜ ይሄ ነገር ምንም ስሜት አልሰጥህ አለኝ፤ “ይሄ ሁሉ ሆታ እና ጭፈራ የኳስ ፍቅር ነው ወይስ የሀገር ፍቅር ነው?” የሚለውን ጥያቄ ነበር ወደ አእምሮዬ የሚመላለሰው።
ከዚያ ቤት ደረስን። ልጄ ከቴሊቭዥኑ ጋር እኩል ትጨፍራለች፤ “ማታ ነው ድሌ!” እያለች ትዘላለች። ለሁለት ቀን ስለተለየኋት ብቻ ሳያት የሆነ ስሜት ውርር አደረገኝ። በዚህ ጊዜ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ ውብሸት ታዬ አስታውሼ ጥልቅ ሀዘን ተሰማኝ። ልጆች አሏቸው፤ ልጆቻቸውን ትተው ነው እስር ቤት እየማቀቁ ያሉትና የልጅ ናፍቆት እንዴት ያርጋቸው ይሆን ብዬ ተከዝኩኝ፤ ከሁሉም በላይ የልጅ ናፍቆት ከባድ ነውና!

No comments:

Post a Comment