(ተመስገን ደሳለኝ)
…አውሮፕላኑ ቅዳሜ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ደርሶ ከተርሚናሉ ስወጣ፣ ተጠራጥሬ ሰዓቴን ተመለከትኩ፤ የድሬ የጠዋት ፀሐይ ከተለመደው ንዳዷ ጋር የአዲስ አበባን የቀትር መራራ ፀሀይን ታስከነዳለች፤ እናም አጥበርባሪ ጨረሯን ያለምህረት ስትለቅብኝ፣ ጓደኛዬ መኪና ይዞ እቦታው እስኪደርስ መጠበቁ በገዛ ፍቃድ መለብለብ ስለመሰለኝ፣ በቀጥታ ከተደረደሩት ታክሲዎች አንዱን ይዤ ወደ ከዚራ አመራሁ፤ ድሬ የሄድኩት በዋናነት ከማህበራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምክንያት በመሆኑ ሊቀበለኝ የተዘጋጀውን ጓደኛዬን ደውዬ ከማውቃቸው የአንዱን ሆቴል ስም ጠቅሼ እዚያ እንድንገናኝ ነገርኩት፡፡
የሆቴሉ ፍተሻ ከወትሮው ጠንከር፣ ጠጠር ያለ በመሆኑ ትዕግስትን ይፈትናል፡፡ እንዲህም ሆኖ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ማረፊያ ክፍሎች በሙሉ መያዛቸው ተነግሮን ቀኝ ኋላ ለመዞር ተገደድን፤ ይሄኔም ነው የጓደኛዬ ፊት ልውጥውጥ ሲል ያስተዋልኩት፤ ጭንቅላቴን በማነቃነቅ በምልክት ምን እንደተፈጠረ ጠየኩት፤ ለአፍታ አመንትቶ ከፊት ለፊታችን በግምት አስር ሜትር ርቀት ላይ ወደቆሙ ሁለት ሰዎች ጠቆመኝ፤ ልብ ብዬ አየኋቸው፤ ሁለቱንም ከዚህ ቀደም አይቻቸው አላውቅም፤ ደግሞም በዙሪያችን ከሚርመሰመሱ ሰዎች የተለየ ምንም አይነት
ሁኔታ ላስተውልባቸው አልቻልኩም፤ እናም ወደ ጓደኛዬ ዞሬ በግርታ ግንባሬን ቋጥሬ ጥያቄ በተሞላ ዓይን አተኮርኩበት፤ ጓደኛዬም ከሁኔታዬ እንዳልገባኝ ተረድቶ ከሹክሹክታም ዝቅ ባለ ድምፅ ‹‹ደህንነቶች ናቸው፣ እየተከታተሉህ ነው›› አለኝ፤ ቢሆኑስ ታዲያ!? በግዴለሽነት ትከሻዬን እየሰበቅሁ ‹‹ለራሳቸው ጉዳይ መጥተው ሊሆን ይችላል›› ብዬው ወደ ሌላ ሆቴል አቀናን፤ እዛም የተለቀቀ ክፍል አለመኖሩ ተነግሮን ፊታችንን ከእንግዳ መቀበያው ‹‹ዴስክ›› ዘወር ስናደርግ እነዛ ‹ደህንንቶች› ቆመው ተመለከትኳቸው፡፡ አሁን ከልምዴ በመነሳት ክትትል ሊሆን እንደሚችል ለማመን በተቃረበ ጥርጣሬ ተውጬ ሌላ ሆቴል ደርሰን ክፍል ጠየቅን፤ በለስ ቀናንና የሆቴሉን መስፈርት አሟልቼ ሳበቃ ጓደኛዬን ቡና ቤቱ ውስጥ እንዲጠብቀኝ አድርጌ፣ ክፍሉን ከተረከብኩ በኋላ ሻንጣዬን አስቀምጬ፣ ገላዬን ተለቃልቄ፣ ልብስ ቀይሬ ደረጃውን መውረድ እንደጀመርኩ ከሰዎቹ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምኩ፡፡ የጭንቅላት ሰላምታ ሰጥቼ አለፍኳቸው፤ ምላሽ የለም፤ ፈገግ አልኩ፡፡ ከወዲሁ የሰሞኑ ምስራቅ ኢትዮጵያ አክራሞቴ ምን ሊመስል እንደሚችል አሰብኩና፣ በልጅነቴ ከሰፈር ማቲዎች ጋር የምንጫወተውን የአኩኩሉ ድብብቆሽ አስታውሼ፣ በድጋሚ ለራሴ ፈገግኩ፡፡
ገና ከአዲስ አበባ ስነሳ ማህበራዊ ጉዳዬን ስጨርስ የድሬዳዋ፣ ሐረር እና ሶማሌ ክልልን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ለማዳመጥ ለተጨማሪ ስድስት ቀናት የሚያቆይ ፕሮግራም አስቀድሜ ይዤ ነበር፤ ከአራት ቀን ቆይታ በኋላም ቀጥታ ወደዚሁ ስራዬ ነበር የገባሁት፡፡ ለጉዳዩ ትኩረት እንድሰጥ ያደረገኝ በቅርቡ ሐረር ከተማ ውስጥ በተከበረው ‹‹የዓለም የመቻቻል ቀን›› ላይ በክልሉ የተንሰራፋው መድልዎና የሐብሊ ተፅዕኖ ተደብቆ፣ ፍትሐዊ አስተዳደር የሰፈነ ለማስመሰል መሞከሩ፤ እንዲሁም ህዳር 29 ቀን በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ (ጅግጅጋ) የሚከበረውን ‹ስምንተኛው የብሔር ብሔረሰብ ቀን›ን አስመልክቶ አካባቢውን ከዋጠው ስጋት በተቃራኒው መንግስት እየነዛ ያለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ከተጨባጩ እውነታ ጋር ለመፈተሽ ፍላጎት አድሮብኝ ነው፡፡
ፊታችሁን ወደ ምስራቅ…
ምስራቅ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ የ3ሺ ዓመት ታሪክ ዕኩሌታውን ሰላምና መረጋጋት የተሳነው ከመሆኑም በላይ፣ ለማዕከላዊ መንግስት የስጋት ምንጭ ሆኖ ነው ዛሬ ድረስ የቀጠለው፡፡ ከአቶማን ተርኪሽ ወታደሮች እስከ አል-ሸባብ ሰርጎ ገቦች ድረስ መተላለፊያ ‹‹ኮሪደር›› ሆኖ አገልግሏል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ሶማሊያውያን የዘር ግንድ ከጐረቤት ሀገራት ሶማሊያና ጅቡቲ ጋር የሚተሳሰር መሆኑና የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ምንጭም ተመሳሳይነት አካባቢውን በበቂ ደረጃ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው የፖለቲካ ተንታኞች ያምናሉ፤ ነዋሪዎቹ በቀላሉ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ የሚኖሩ መሆናቸውም ሌላው ችግር እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ቅኝ ገዥዎቹ የአውሮፓ ሀገራት በበኩላቸው አካባቢውን ‹ፍሬንች ሶማሌ ላንድ›፣ ‹ብሪታኒያ ሶማሌ ላንድ› እና ‹ኢታሊያ ሶማሌ ላንድ› በሚል ከፋፍለው ማስተዳደራቸው፣ ከሶማሊያ ነፃነትም በኋላ የሞቃዲሾን ቤተ-መንግስት የተቆጣጠሩ ገዢዎች ‹ታላቋን ሶማሊያ እንመሰርታለን› በሚል ቀቢፀ ተስፋ ከአንድም ሶስቴ የኢትዮጵያን ወሰን ተሻግረው የኃይል ወረራ መፈፀማቸው የአካባቢውን ውጥረት ይበልጥ አባብሶት ነበር፤ ከዚያም ባሻገር የዚያድባሬ ሶማሊያ መፈራረስም የቀጠናውን ሠላምና ፀጥታ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡
በዚህ ሁሉ ከባቢያዊ ውጥረት እየታመሰ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በአንድነት በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ስር ሲተዳደር የቆየው የምስራቁ የሀገራችን ክፍል፣ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ባነበረው ‹‹ፌደራሊዝም›› በሶስት ሊከፈል ችሏል፤ ‹‹የሶማሌ እና ሐረር ክልል›› እንዲሁም ‹‹የድሬዳዋ አስተዳደር›› በሚል፡፡ ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በውጭ ተፅዕኖ ይተራመስ የነበረውን ‹ጂኦ-ፖለቲክስ› ብሔር
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ተኮር ለሆነ ተጨማሪ አዲስ ቁርቁስ አጋለጠው፡፡ በአናቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ኦጋዴን፣ ጎዴ፣ ደጋሀቡር፣ ቀለፎን የመሳሰሉ ከተሞች ክልሉን ‹እንገነጥላለን› የሚሉት የኦጋዴን ብሔራዊ ግንባር ታጣቂዎች መርመስመሻ መሆናቸው አካባቢውን የስጋት ቀጠና አድርጎታል፤ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ድሬዳዋ ላይ ያነጋገርኳቸውና በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአስተዳደሩ አባል የነበሩ አቶ ኡስማን (ለዚህ ፅሁፍ ስማቸው የተቀየረ) ‹‹የዚህ ሁሉ ተጠያቂ ለጣልቃ ገብነቱ ያልተመቹትን የአካባቢው ልሂቃን ‹ለወረራ የመጡ የዚያድባሬ መኮንኖች› እያለ አሸማቅቆ ከፖለቲካው ገፍቶ በማስወጣት ክልሉን ዛሬ ላለው ደካማ አስተዳደር የዳረገው ኢህአዴግ ነው›› ይላሉ፡፡ በግልባጩ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ካሳ ተክለብርሃን የተገፉት ሰዎች ኢትዮጵያዊ አለመሆናቸውን ለ‹‹ዘመን›› መፅሄት የገለፀው እንዲህ በማለት ነበር፡-
‹‹ሶማሊያ የፈራረሰበት ወቅት ስለነበር በጣም ትላልቅ የሶማሊያ ተፈናቃዮች የሰፈሩባቸው ካምፖች ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ አንዱ የስደተኞች ካምፕ የነበረባት አገር ነበረች፡፡ በተለይ አርትሼክ አካባቢና ሌሎች አካባቢዎችም ትልልቅ ካምፖች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የመጡ የዚያኛው ሶማሊያ መኮንኖች፣ ሲቪል ሰራተኞች ኢንጂነሮችና ፓይለቶች ነበሩ፤ በአካል ያገኘናቸው የምናውቃቸው እነዚህ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ጋር የሚለያቸው ነገር ስላልነበረ በአብዛኛው በስደተኛነት ከመጡ በኋላ የአካባቢውን የፖለቲካ ስልጣኑንም ያደራጁት እነሱ ነበሩ፡፡ አንዱ ትዝ የሚለኝ ይሄ ነው፡፡ ይሄንን የኢህአዴግ ሰራዊትና ከላይ የሄደው የኢትዮጵያ ሰራዊት ሊለየው አይችልም ብቻ ሳይሆን ያ የመጣውን እንዳለ የሚያቅፍ ሁኔታ ነው የነበረው በአካባቢው፡፡ ስለዚህ ለረጅም ጊዜ ያ ኃይል ነው እንግዲህ አዲስ በተፈጠረው አጋጣሚ የታላቋ ሶማሊያን አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ላይ ለመዝራት ትልቅ ጥረት ያደረገው››
ይህ ክርክር በራሱ ኢህአዴግ ‹‹ፊታችሁን ወደተረጋጋችው ምስራቅ ኢትዮጵያ (ሶማሊ ክልል) መልሱ›› ያለበት አውድ የተለመደው የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ እንጂ አካባቢው የጦርነት ወረዳን ያህል የሚያሰጋ መሆኑን ያመላክታል ፡፡ እናም ከአርቲስቶች እና ጋዜጠኞች እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፊት-አውራሪነት የተካሄደው የጉብኝት ፕሮግራም፣ መንግስት ምንም እንኳ የህዝቦችን አንድነት ‹የማጥበቅ ዕቅድ› የሚል የዳቦ ስም ቢሰጠውም፣ ‹ሶማሌ ክልል ፍፁም ሰላም ነው› የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ለመንዛት መሆኑን ለመረዳት በአካባቢው ያለውን የፀጥታ አጠባበቅ ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል፡፡
የቦምባስ ዕገታ
ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ‹‹ሕገ-መንግስታችን ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ለመለካት ረቡዕ ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ወፍ ጭጭ ሳይል ነበር ድሬዳዋን ለቅቄ ወደ ሐረር ጉዞዬን የተያያዝኩት፡፡ ይህንን ሰዓት የመረጥኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ላይ እንኳ ጋብ እየለ የመጣውን የደህንነት ሰራተኞች ክትትል ድሬዳዋ ላይ በየደረስኩበት ሲያንዣብብብኝ፣ በማስተዋሌ፣ ምናልባት ከዕይታ ውጪ መንቀሳቀስ ብችል በሚል እሳቤ ነበር፡፡ መኪናው ከአንድ ቀን በፊት የተከራየሁትና ድሬ ውስጥ ያልተጠቀምኩበት በመሆኑ፣ በስጋት የሚንጠውን የደንገጎ አቀበትም ሆነ ጥንታዊቷን ሐረር ከተማ አቋርጠን እስክናልፍ አንዳች ችግር አላጋጠመንም፡፡ ይሁንና ከሐረር በግምት 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሶማሊያ ክልል የምትገኘው ቦምባስ ከተማ ደርሰን ጥቂት እንደተጓዝን፣ መኪናውን ዳር አስይዞ እንዲያቆም አንድ የትራፊክ ፖሊስ ለሹፌሩ የእጅ ምልክት አሳየው፤ ይሄኔም ነው ድሬ ላይ እንደ ተሰወርኩባቸው እርግጠኛ ሆኜ በልቤ ከሳቅኩባቸው ሁለቱ ሰላዮቼ ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጥነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜን ጠርተው አነጋገሩኝ፤ እኔም ከምንም ነገር በፊት መታወቂያቸውን እንዲያሳዩኝ ጠየቅኩ፤ ሳያቅማሙ አሳዩኝ፤ ወዲያውኑም የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ እንዳልሆነ የአነጋገር ዘዬው በግልፅ የሚያስታውቀው አንደኛው የደህንነት አባል፣ ከዚህ በላይ ጉዞውን መቀጠል እንደማልችልና በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ መመለሱ እንደሚጠቅመኝ ሊነግረኝ ሞከረ፡፡ ከመገረሜ ብዛት ንግግሩን ለመረዳት ጥቂት ሰከንዶች ፈጅተውብኝ ነበር፡፡ መቼም ይህ ሰው ቀልደኛ መሆን አለበት! አለዛ በገዛ ሀገሬ የት ድረስ መሄድ ወይንም የት ቦታ ጉዞዬን መግታት እንዳለብኝ ሊወስንልኝ ባልደፈረ ነበር፤ ሆኖም ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ምን ማለት እንደፈለገ እንዲያስረዳኝ በትህትና ጠየኩት… ይኼኔ ጓደኛው ጣልቃ ገባና ወደ ጅግጅጋ ለመሄድ ማሰቤን እንደደረሱበትና ወደ ከተማው እንድገባ እንደማይፈቅዱልኝ ቆጣና ኮስተር ብሎ አሳወቀኝ፡፡ እኔም ፈርጠም ብዬ እዚህ ድረስ መጥቼ ጅጅጋ ሳልደርስ እንደማልመለስ ቁርጡን ነገርኳቸው፡፡ ቃለ-ምልልሱ እየከረረ ሲሄድ ማስፈራራቱን ወደ ሹፌሩ አዞሩትና በብርቱ ያዋክቡት ያዙ፤ ይህ ድርጊታቸው ያልጠበቅኩት በመሆኑና የሹፌሩንም ምላሽ አለማወቄ መጠነኛ ድንጋጤ አጫረብኝ፡፡ እንደገመትኩትም ሁኔታውን በፍርሃት ተውጦ ይከታተል የነበረው ሹፌር ትንሽ እንኳ ሳያንገራግር መኪናውን ቆስቁሶ ወደ ሐረር አዞረው፡፡
‹‹ምን ሆነሃል?›› አልኩት በንዴት ጮኽ ብዬ፡፡
‹‹ወንድሜ እኔ ቤተሰብ የማስተዳድር ሰው ነኝ፡፡››
‹‹ብትሆንስ!?››
‹‹አንተም እነዚህ ሰዎች ምን መዓት ሊያደርሱብህ እንደሚችሉ ብታውቅ እንዲህ አትከራከራቸውም ነበር፡፡››
የውጥረቱ ውስጠ-ምስጢር ሲጋለጥ
በርግጥ መንግስት ጅጅጋን ስለምንድነው እንዲህ አጥሮ ከሌላው ዕይታ ሊሸሽጋት የሚሞክረው? ምን እየተሴረባት ቢሆን ነው? የሚያስተዳድራትስ ማን ነው?
ከዚህ ሁሉ በኋላ ያለኝ አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ጅጅጋ የሚመላለሱ የመንግስት ሰራተኛ ወዳጆቼን አፈላልጎ የውጥረቱን ነገረ-ምስጢር መረዳት፡፡ የዕድል ጉዳይም ሆኖ በግማሽ ቀን ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን መረጃዎች ላሰባስብ ቻልኩ፡፡
…ከተማዋ በመከላከያና ፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም የክልሉ ፕሬዝዳንት በቀጥታ በሚያዛቸው ልዩ ኃይሎች ጥብቅ ጥበቃ ስር ወድቃለች፤ ከነዋሪዎች ቁጥር የሚስተካከሉ የፀጥታ ሰራተኞችም ሃያ አራት ሰዓት በአይነ ቁራኛ እየጠበቋት ነው፡፡ ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ምንም አይነት መኪና ወደ ክልሉ እንዳይገባ ለአንድ ወር የሚቆይ እግድ ተጥሏል፤ ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊም ታውጇል፤ ለከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ‹‹ባጃጅ›› ተሽከርካሪዎች የላይ መሸፈኛቸውን አንስተው፣ ተሳፋሪዎችን በግላጭ እያሳዩ እንዲንቀሳቅሱ ታዝዘዋል፤ ወደ ከተማዋ ለመግባት በቂ ምክንያት የሌለው እና መታወቂያ ወረቀት ያልያዘ ማንኛውም ሰው በመጣበት እግሩ እንዲመለስ እየተገደደ ነው… (በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ከድሬዳዋም ሆነ ከሐረር መንገደኞችን የሚያጓጉዙ ሚኒባሶች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ከተከለከሉ ከሶስት ወር በላይ አልፏቸዋል፡፡ በርግጥ አስተዳደሩ ለክልከላው የሰጠው ምክንያት ሚኒባሶቹ የሚያደርሱት አደጋ መብዛት ቢሆንም፣ ስማቸውን መግለፅ ያልፈልጉ ሁለት ሹፌሮች ግን ይህንን አይቀበሉትም፡፡ እንደነሱ ግምት አምባገነን እንደሆነ የሚነገርለት የክልሉ ፕሬዝዳንት ባለቤት እናት፣ ከክልከላው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በሚኒባስ አደጋ ህይወታቸው ከማለፉ ጋር ያያይዙታል)
በተቃራኒው የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን የጥበብ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ክልሉን ካስጎበኛቸው በኋላ በጥቅምት ወር ከታተመው ‹‹ዘመን›› መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ አካባቢው ፍፁም ሰላም የሰፈነበት እንደሆነ የገለፀው እንደሚከተለው ነበር፡-
‹‹የ84 ሌላኛው ትዝታ… ከሀረር ተነስቶ ወደ ጐዴና ወደ ፌርፈር የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ያለ ኮንቫይ የሚሞከር አልነበረም፡፡ ትልቅ የሠራዊት ኮንቫይ ተይዞ ነው አንድ ነገር ወደ አካባቢው የሚሄደው፡፡ …ዛሬ ያ አካባቢ በጦር ኃይል ሊጠበቅ የሚችል አይደለም፡፡ ሰፊ አገርና ሜዳ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝብ ልብና ፍቅር ነው አገርን የሚጠብቀው፡፡ …ሰላሙ አስተማማኝ ነው፡፡ እንደማንኛውም የአገራችን አካባቢ ሆኗል፡፡ አሁን ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ማለት ነው፡፡››
መቼም ከብአዴን አመራሮች መካከል ቁመተ-መለሎው አቶ ካሳ የሥራ ጉዳይ ባይሆንበት ኖሮ እልፍ አእላፍ መከላከያ ሠራዊት ስለተከማቸበት፣ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ወፍ ዝር የማያሰኝ ጥብቅ ሰዓት እላፊ ስለታወጀበት የሶማሌ ክልል ደፍሮ እንዲህ ሊል አይችልም ነበር፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መሪነት ከፍተኛ ባለስልጣናት ‹‹የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር›› በሚል ዓላማ ክልሉን ከጎበኙ በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት መሆኑን ማረጋገጣቸውን ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. የታተመው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ በግልባጩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅጅጋ ቅርንጫፍ ሰራተኛ የሆነ ወዳጄ የከተማዋን አስፈሪ ድባብ የገለፀልኝ ‹‹ለእያንዳንዱ ነዋሪ አንድ የፀጥታ አባል የተመደበ ይመስላል›› በማለት ነበር፡፡
‹‹ፌደራሊዝም›› በምስራቅ ኢትዮጵያ
ከአብዛኛው የሀገሪቱ ክልሎች ምስራቅ ኢትዮጵያ ብሔርን መሰረት ላደረገው ፌደራሊዝም ክሽፈት በቂ ማሳያ ነው፡፡ መከራከሪያውን ምክንያታዊ ለማድረግም በአካባቢው የሚገኙትን ሶስቱንም መስተዳድሮች ብቻ ለብቻ ነጥለን በአዲስ መስመር እንቃኛቸዋለን፡፡
ሐረሪ
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ቁጥሩ ከመቶ ሺ በታች የነበረው የሐረሪ ብሔረሰብ ራሱን የቻለ ክልል እንዲኖረው መደረጉ፣ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚልቅ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች በክልል ደረጃ መዋቀር መከልከላቸው ቀላል የማይባል አዋራ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይም በሚሊዮን የሚቆጠሩት የሲዳማ ተወላጆች በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄውን አቅርበው ውድቅ
ከመደረጉ አኳያ እየተነፃፀረ ጠንካራ ትችት ቢቀርብበትም፣ የአቶ መለስ መንግስት ‹‹ጆሮ ዳባ…›› በማለት በአቋሙ መፅናቱ ይታወቃል (በነገራችን ላይ የሲዳማን ጥያቄ መንግስት ደም በማፍሰስና በኃይል አዳፈነው እንጂ በመተማመን አልፈታውም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ዛሬም ድረስ በብሔሩ ልሂቃኖች እና በደቡብ ክልል መስተዳደር መካከል አልፎ አልፎ ግጭት ሲፈጠር የምንሰማው)
የሆነ ሆኖ ክልሉን ከቀድሞዋ ሐረርጌ ነዋሪዎች በቁጥር አናሳ የሆኑትን ሐረሪዎች የሚወክለው የ‹‹ሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)››፣ ከኦህዴድ ጋር በጣምራ እንደሚያስተዳድረው ቢነገርም፣ ከመቶ ዘጠና በላይ የመንግስት ቢሮዎችን ጠቅልሎ ይዟል፤ ኦህዴድ በአፈ-ጉባኤነት፣ በግብርና ቢሮና በምክትል ቦታዎች ላይ ተቀምጧል፡፡ ለማሳያ ያህል የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙራድ አብዱላሀዲ፣ ከንቲባው ዶ/ር ባህር፣ ከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ነቢል መሀመድ፣ ውሃና ፍሳሽ ዋና ስራ አስኪያጅ አሪፋ መሀመድ፣ የሴቶች ጉዳይ አፊዛ በድሪ፣ መንገድ ስራዎች ባለስልጣን ሌላኛው ነቢል መሀመድ፣ ቤቶች ኤጀንሲ አብዱልሀኪም አብዱልማሊክ፣ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልቃድር፣ በፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር ያህያ አብዱልሰታር፣ ፍትህ ቢሮ፣ ባህልና ስፖርት፣ ገቢዎች… የመሳሰሉት የሐብሊ ርስተ-ጉልት ናቸው፡፡
ከዚህ ውጪ የግብርና ቢሮው በኦህዴዱ ሀምዛ መሀመድ እንዲመራ የተደረገው ሐረሪዎች በእርሻ ስራ ካለመሰማራታቸውም በላይ በሐረር ዙሪያ ባሉ ከተሞች ከሚገኙ አርሶ አደሮች አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጅ ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡ የፌደራሊዝሙም አንዱ ግርታ ይህ ነው፤ ምክንያቱም የኦሮሞ ከተሞች በምን መስፈርት ነው ለሐረሪዎች የተሰጡት? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና፡፡ በጥቅሉ ይህ አይነቱ አስተዳደር ሀገርንና ሕዝብን ሊጠቅም አለመቻሉን ለመረዳት በሐረር የተንሰራፋውን ስር የሰደደ ድህነት መመልከቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሊጉን ተንጠላጥለው ሀብት ያካበቱ ሰዎች እንኳን በከተማው ውስጥ ሊጠቀስ በሚችል ኢንቨስትመንት ላይ አልተሰማሩም፡፡ በሙስናና በዝምድና አሰራር የተተበተበው ምክር ቤት፣ ሐረርን ከመስራች አባቶቿ አሚሮች ዘመን ሳይቀር ወደከፋ አዝቀት እየከተታት እንደሆነ የሚያሳየው ደግሞ የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ዳይሬክተር አብዱልናስር ኢድሪስ ከተማዋን አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጠውን አስተያየት ስናነብ ነው፡- ‹‹ወደ ከተማው የሚመጣውን ቱሪስት በተገቢው ደረጃ ለማስተናገድ የሚችሉ ሆቴሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የሉም፡፡›› …ጨለንቆ ላይ ሆኖ ሐረርን በርቀት ላስተዋለ እንዲህ ነጋዴ-ፓርቲ፤ ሙሰኛ-ሹማምንት፤ አድሎኛ-አስተዳደር፤ ከሕግ በላይ የሆኑ-ባለሥልጣናት መተንፈሻ አሳጥተዋት መንግስት የሚያስተዳድራት ክልል ሳትሆን፣ በቁፋሮ የተገኘች ጥንታዊት የከተማ ፍርስራሽ ብትመስለው አይገርምም፡፡
በነገራችን ላይ አስተዳደሩ የሆቴል እጥረቶችን ለመፍታት ‹‹ምርጥ ቀመር›› እንዳለው የሚያሳየን የሚከተለው ክስተት ነው፤ በሶማሌ ክልል የሚከበረው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› ከተጠናቀቀ በኋላ እንግዶቹ ወደ ሐረር ጎራ የሚሉበት ፕሮግራም መዘጋጀቱንና በቂ ሆቴል አለመኖሩን አስመልክቶ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አሚራ አሊ ለመንግስት ጋዜጠኞች ስትናገር ቃል-በቃል እንዲህ ነበር ያለችው ‹‹(ያሉት) ሆቴሎች በሙሉ አቅማቸው እንዲዘጋጁ ይደረጋል፤ በበዓሉ ወቅትም ከእንግዶች ውጪ ሌሎች ተስተናጋጆችን እንዳይቀበሉ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡›› መቼም የ‹‹መግባባት›› ቃልን ሰሙን ትተን ወርቁን ስንፈትሸው ‹ትእዛዝ ሰጥተናል› እንደማለት መሆኑ ነው፤ ይህንንም ይበልጥ አፍታተን ስንተረጉመው ደግሞ ልክ እንደ ጅጅጋ ሁሉ በዓሉ እስኪያልፍ ከከተማው ነዋሪ ውጪ ማንም ሰው ድርሽ ማለት አይችልም የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ …ታዲያ ለሐብሊ ህገ-መንግስቱ ምኑ ነው? ማን ነበር የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ያለው?
ከሁለት ሳምንት በፊት በሐረር የተከበረውን ‹‹የዓለም የመቻቻል ቀን››ን አስመልክቶ የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ለጋዜጠኞች ‹‹መቻቻል የሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ መሰረትነት ባሻገር ከሕገ-መንግስታዊ እሴቶች መካከል አንዱ ነው›› ብሎ ቢሳለቅም፤ በሐረር የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ሀገረ ስብከት የሐዋሪያዊ ሥራ አስተባባሪ አባ ተክለብርሃን ‹‹በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚንፀባረቁ አፍራሽ አስተሳሰቦች›› መኖራቸውን መግለፃቸው እውነታውን ያሳያል፡፡ በአናቱም የሐብሊ የአመራር አባላትና ካድሬዎች በክልሉ ነዋሪ በሆኑና በቁጥር በብዙ እጥፍ የሚበልጧቸውን፣ የሌላ ብሔር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ ግልፅ የአስተዳደር መድልዎ እንደሚያደርጉ የከተማው ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ (በአካባቢው ላይ ኦህዴድ የተሻለ ተቀባይነት እንዳለው ካነጋገርኳቸው ሰዎች ሰምቻለሁ) ሐብሊዎች አልፎ ተርፎም የጥላቻ መግለጫ ድርጊቶችን እንደሚፈፅሙ ይሰማል፡፡ ጀጎል ውስጥ ያገኘሁት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማኔጅመንት የተመረቀው አበባው በለጠ (ስሙ የተቀየረ) ከዚህ ጉዳይ ጋር አያይዞ የነገረኝ ገጠመኝ ለችግሩ እውንነት አስረጅ ሊሆን ይችላልና ሙሉ ታሪኩን እነሆ፡-
ክስተቱ 2005 ዓ.ም. በወርሃ ጥቅምት አጋማሽ ላይ፣ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ግድም የተፈፀመ ነው፡፡ የሐረሪ ተወላጆች የሆኑ ጥቂት የፖሊስ አባላት በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ እየተዝናኑ ነበር፡፡ ሞቅታ የተሰማውም አንዱ የፖሊስ አባል ከራሱ ጓደኞች ጋር መነታረክ
ይጀምራል፤ አለመግባባቱም እየከረረ ሄዶ በወገቡ የታጠቀውን ሽጉጥ መዝዞ እስከማቀባበል ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም ገላጋይ ገብቶ ፀቡን አበረደውና ሁሉም ተያይዘው ወደ መምሪያ ይመለሳሉ፡፡ ይኼኔ መምሪያ ውስጥ የነበረ አንድ የስራ ባልደረባው ‹በደም ፍላት ጉዳት እንዳያደርስ› በሚል መሳሪያውን ሊቀማው ሲታገለው በድንገት የተቀባበለው መሳሪያ ይባርቅና ራሱኑ ባለመሳሪያውን ይመታዋል፡፡ በዚህ ክፉኛ የተደናገጡት የፖሊስ አባላት አንከብክበው ወደ መንግስታዊው ጃጉላ ሆስፒታል ይወስዱታል፤ የህክምና ባለሙያዎቹ ተጎጂውን መርምረው ‹‹ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ከአቅማችን በላይ ነው›› ይሉና የግል ወደሆነው ሐረር አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲወስዱት ይነግሯቸዋል፡፡ የሐረር አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ሰውየው የፈሰሰውን ብዙ ደም የመተካቱን ሂደት ቅድሚያ ሰጥተው ብርቱ እርብርብ በሚያደርጉበት ወቅት፣ የተጎጅው የስራ ባልደረቦች ‹‹ችሎታው የሚነገርለት የዕለቱ ተረኛ ሐኪም ዶ/ር ጥሩሰው ኪዳኔ ተጠርቶ በቀዶ ጥገና ጥይቱን ሊያወጣለት ይገባል›› በማለት ከጤና ባለሙያዎቹ ጋር ንትርክ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተጎጂው እንዲህ ብዙ ደም በፈሰሰበት ሰዓት ዶ/ሩ ተጠርቶ ቢመጣም ቀዶ ጥገና ሊያደርግለት እንደማይችል ቢያስረዷቸውም፣ አስገድደው ስልክ እንዲደወል ያደርጋሉ፡፡ በአጋጣሚ የዶ/ሩ ስልክ ጠርቶ ጠርቶ ይዘጋል እንጂ አይነሳም፤ ደግመው ደወሉ፤ ሰለሱም… መልስ የለም፡፡
ሊነጋጋ አካባቢ ተጎጂው ህይወቱ ያልፋል፡፡ ይህን ጊዜም ህዝብንና የህዝብ መገልገያ ንብረቶችን ለመጠበቅ ቃለ-መሀላ የፈፀሙት ፖሊሶች ከሟች ቤተሰቦች ጋር በመተባበር የሆስፒታሉን ንብረት ማውደም፣ በአቅራቢያቸው ያገኙትን የጤና ባለሙያ ሁሉ መደብደብ ይጀምራሉ፡፡ ለሀላፊዎቻቸው ተነግሮ ለዕርዳታ የተላኩት በርካታ ፖሊሶችም፣ ከሰነበተ ጥላቻ የሰረፀውን ይህን የበቀል ጥቃት ለመከላከል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ጠዋት እሆስፒታሉ የተገኘው የክልሉ ፕሬዝዳንትም ሀዘኑን ብቻ ገልፆ፣ ቢያንስ ስርዓት አልበኞቹን እንኳን ሳይገሰጥ ይመለሳል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ከዚህ ሁሉ ውድመትና ጉዳት በኋላ ዶክተሩን ካለበት አንቀው እስር ቤት መክተታቸው ነበር፡፡ አንድ ወር ከአስር ቀን ታስሮ ቢለቀቅም ክሱ አሁንም በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡ የክሱ ጭብጥ እንደሚያስረዳው ሆስፒታሉ ለሟች ቤተሰብ የአራት ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፍልና እስከ ወዲያኛው እንዲዘጋ፣ ዶ/ሩም በነፍሰ ገዳይነት እንዲቀጣ የሚጠይቅ ነው (እንዲዘጋ የጠየቁት ሆስፒታል 25 አልጋ፣ 5 አይ.ሲና 3 ማዋለጃ ክፍሎች ሲኖሩት፤ ከባለሞያ አኳያ ደግሞ 5 የማህጸንና 3 የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች፣ 30 ነርሶች በአጠቃላይ በ115 ሰራተኞች የሚመራ ነው)
ከሳሾቹ በማመልከቻቸው ላይ አራት ሚሊዮን ብር ካሳ የጠየቁበት ምክንያት፡- የሟች ባለቤት ቋሚ ገቢ የሌላት በባለቤቷ የምትተዳደር ስለነበረች እርሱ በህይወት ቢኖር ደሞዙ እስከ ጡረታ መውጫው ድረስ ሊያገኝ በሚችለው ጭማሪ ተባዝቶ፣ በቀን ውስጥ ትርፍ ሰዓት ቢሰራ፣ በተለያየ የስራ ግዴታ ቢሰማራ ማግኘት ይችል የነበረው አበል ገቢው ላይ ተደምሮ በአጠቃላይ እስከ አራት ሚሊዮን ይደርሳል የሚል በአስቂኝ መላ-ምት የተቀናበረ ግምት ነበር፡፡ እንደ መረጃ ምንጬ አባባል ከሆነ፣ የዚህ ሁሉ መግፍኤ ሆስፒታሉ ከተመሰረተ በኋላ የተቀላቀሉት ሶስት የሐረሪ ተወላጆችን ሳይጨምር በ19 የሌላ ብሔር ተወላጆች መቋቋሙ እና የቁጥጥር ግንኙነቱ ቀጥታ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ጋር መሆኑ የሐብሊ የጥላቻ አይን እንዲያርፍበት ማድረጉን ነው፡፡
(ድሬዳዋን እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን መቃኘቱን ሳምንት እመለስበታለሁ)

No comments:
Post a Comment