"ለአማርኛ ስነፅሁፍ ቅርብ ነኝ ለማለት አልችልም። የሚታተሙ መጻሕፍትን እንደልቤ ለማግኘት ስለምቸገር ስለታተሙ መጻሕፍት በልበ ሙሉነት አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። በጥቅሉ ግን የአማርኛ ስነፅሁፍ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ይሰማኛል። አማርኛ በአዲሳባና በአማራ ክልል ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ብዙ ተሰርቶበታል። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ስነፅሁፍን ክፉኛ ጎድቶታል። አማርኛ ቋንቋ ጠላት ስለበዛበት ስነፅሁፉም ባለቤት አጥቶአል። ይህ አሳዛኝ እውነት ነው።" ተስፋዬ ገብረአብ ከላይፍ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ |
(ይህ ቃለመጠይቅ አዲስ አበባ ላይ በየ15 ቀኑ ከሚታተመው "ላይፍ" መጽሔት ጋር የተደረገ ሲሆን፤ ቃለመጠይቁ የተካሄደው ከመጽሔቱ ጋዜጠኛ ጋር በጽሑፍ ነው።)
ላይፍ፦ አዲሱ "የስደተኛው ማስታወሻ" መጽሐፍህ ከ"የደራሲው ማስታወሻ" እና ከ"የጋዜጠኛው ማስታወሻ" በምን ይለያል?ተስፋዬ፦ "የስደተኛው ማስታወሻ" ከቀዳሚዎቹ ማስታወሻዎች የቀጠለ ነው። በዚህ ቅፅ በተመሳሳይ ገጠመኞቼን ነው ያሰፈርኩት።