Time in Ethiopia:

Sep 30, 2013

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሪፖርት ኢትጵያን ከፈጣን አገሮች ተርታ አላሰለፈም

Geez Bet | Monday, September 30, 2013
-የአፍሪካን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች ዘንግቷል በሚል ተተቸ
የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ምልከታን በመንተራስ በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው ሪፖርት (አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውትሉክ)፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የነበረውንና በ2014 ይኖራል ብሎ የተነበየው የኢኮኖሚ መስተጋብር ይፋ ሲደረግ፣ አሥር ፈጣን አፍሪካ ኢኮኖሚዎች ካላቸው ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷ ስህተት መሆኑን ኃላፊዎቹ አመኑ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀውን ሪፖርት ዘንድሮ ይዞ ብቅ ያለው፣ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አሥር አገሮች መካከል ኢትዮጵያን ዘንግቶ ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን ሪፖርቱ ከተዘጋጀ አንድ ዓመት በኋላ ይፋ በመደረጉ ነው ተብሏል፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ለማካተት ሳይቻለው መቅረቱ ስህተት እንደሆነ የገለጹት የባንኩ የኢትዮጵያ ተወካይ ላሚን ባሮው፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሪፖርቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ፈጣን አገሮች ውስጥ ስሟ ባይጠቀስም ዕድገቷ አይካድም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የዘንድሮው ሪፖርት በአፍሪካ እየተካሄዱ ያሉ የፖለቲካ ለውጦችን በአግባቡ አላሳየም ሲሉ ከተቹ ምሁራን መካከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር
ቆስጠንጢኖስ በርሄ አንዱ ናቸው፡፡ ሪፖርቱ በፖለቲካ ጫና ምክንያት እየተለወጡ የሚገኙትን ሕገ መንግሥቶች ከኢኮኖሚ አኳያ ቢመለከት መልካም እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ከአፍሪካ የሚዘረፈው የውጭ ምንዛሪና አኅጉሪቱ ከሙስናና ጋር በተቆራኘ መንገድ የምታጣውን የተፈጥሮ ሀብት ሪፖርቱ ሊተነትን ሲገባው በዝምታ ማለፉም ለወቀሳ ዳርጎታል፡፡
በአጠቃላይ በአፍሪካ አገሮች የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች የዓለም ክፍሎች አኳያ ሲታይ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በፋይናንስ ቀውስና በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የሚከሰቱ ጋሬጣዎች ሳይገድቡት በየዓመቱ የአምስት ከመቶ አማካይ ዕድገት ሊመዘገብ በመቻሉ አፍሪካውያንን አሞካሽቷል፡፡ ይህም ቢባል ግን የአፍሪካ አገሮች ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ድህነትን በሚፈለገው መጠን ለመቀነስ ያላስቻለ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  
Source: http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment