-አና ጎሜዝ ወደ እንግሊዝ መመለስ አለባቸው እያሉ ናቸው::
ከዱባይ ወደ አስመራ ለመሄድ የመን ሰንዓ ላይ በየመን የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታስረዋል የተባሉት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል መባሉን እንደ ሰማ የእንግሊዝ መንግሥት አስታወቀ፡፡
ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ ሚስተር ኢያን ኮክስ አቶ አንዳርጋቸውን በሚመለከት ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ እንዳስረዱት፣ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰነዓ ውስጥ መጥፋታቸው ተገልጾላቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ያሉበትን ሁኔታና ሥፍራ ለማወቅ የየመን ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና በእንግሊዝ የሚገኙትን የየመን አምባሳደርን ማነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢያን ኮክስ አንዳንድ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደቻሉት፣ አቶ አንዳርጋቸው ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በመሆኑም ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ አቶ አንዳርጋቸው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደሚገኙ ከሪፖርቶች መረዳት መቻሉን ገልጾ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጫ በአስቸኳይ እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት በእንግሊዝ የየመን አምባሳደርን አነጋግረዋቸው፣ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን ለቤተሰቦቻቸው መንገራቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል፡፡