ማክሰኞ ምሽት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ኢቲቪ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አስመልክቶ ያቀረበው ዜናን ብዙዎች በተቀላቀለ ስሜት ነበር የተከታተሉት፡፡
ዜናው የአቶ አንዳርጋቸውን ንግግር ለአፍታ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱ ግን ግራ ያጋባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ‹‹እኔ አሁን ከራሴ ጋር ታርቄ ሰላም አግኝቻለሁ፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እኔ እንደ ምርቃት ነው የተቀበልኩት፡፡ አሁን የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም፡፡ ጥሩ ዕረፍት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በጣም በጣም ደክሞኛል … ሰልችቶኛል፡፡ እውነቴን ነው የምልህ ተረጋግቼ ያለሁበት ሁኔታ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጥላቻ በውስጤ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ብስጭት የለኝም፡፡ ምንም ዓይነት መጥፎ ስሜት አይሰማኝም፡፡ በቃ … የመጨረሻ እርጋታና ዕረፍት ውስጥ ነው ያለሁት፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከአንዴም ሁለቴ በፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ከሶ የሞት ፍርድ ባስፈረደ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው በጤናው ደስተኛነቱን አይናገርም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የንግግሩን አንድምታ በተመለከተ የተራራቀ መላምታቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለአንዳንዶች የአቶ አንዳርጋቸው ንግግር ባልተጠበቀ መንገድ በጠላቶቹ እጅ የወደቀ ሰው ያለበትን ሁኔታ ባለመቀበል የሰጡት ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ በአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያሰማ ላለው ሥጋት ምላሽ ለመስጠት መንግሥት አስገድዷቸው የሰጡት ቃል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልገሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰንዓ በኩል ወደ ኤርትራ ሊገቡ ሲል ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ በዚያው ዕለት ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታ
ቸውን አስታውቋል፡፡ ይህ ከሁለት ሳምንት በላይ የዘለቀውን የአቶ አንዳርጋቸውን መገኛ ቦታ ጥያቄና መላምት የሚያስቆም ቢሆንም፣ በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ መያዝ ግለሰቡ ካላቸው የእንግሊዝ ዜግነት አኳያ የሚያስከትለው የሕግና የፖለቲካ አንድምታ ግን አሁንም የመወያያ አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡ በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የየመን፣ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግሥታት ሚና፣ ወቅታዊ ሁኔታና የመጪ ጊዜ ግንኙነት ግልጽ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ የሰጠችበት መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጠይቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ አይደለም በማለት እየተቿት ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ግንቦት 7 ለኢትዮጵያውያን መብትና ነፃነት እታገላለሁ እያለ በአመራሩ እርከን ከሊቀመንበሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመቀጠል የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው እንግሊዛዊ መሆናቸው ስሜት አልሰጣቸውም፡፡ በአንድ በኩል እንግሊዝ ዜጋዋ የሆነውን የአቶ አንዳርጋቸውን መብት ለማስጠበቅ ከየመንም ጋር ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጠበቅባትን አላደረገችም በሚል እየተተቸች ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ለሚሠራው ግንቦት 7 አመራር ዜግነት የሰጠችው እንግሊዝ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ሽብርተኝነት እንዲጠፋ ከኢትዮጵያ ጋር በጥምረት መሥራቷ የተቃርኖ ስሜት የፈጠረባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባለውን የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ግንኙነት አይጐዳውም ወይ ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእንግሊዝን ፓስፖርት የያዙ ግለሰብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ጥልቅ ያደርጋቸዋል? ዜግነታቸውን ጥለው ከሄዱ በኋላ ማንን ነው ነፃ የሚያወጡት? ይህ ዓይነቱ ድርጊትስ አንድን ሉዓላዊ አገር መዳፈር አይደለም ወይ? ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በዋና ጸሐፊነት ያገለግሉት የነበረው ግንቦት 7 በ2000 ዓ.ም. በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አማካይነት የተቋቋመ ሲሆን፣ አወዛጋቢው ምርጫ 97 የተካሄደበትን ቀን ለማስታወስ ስሙን እንደመረጠው ንቅናቄው ይገልጻል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተካሂዶ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ኢሕአዴግን በከፍተኛ ሁኔታ የተፎካከረው ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ፍፁም የበላይነት ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ቅንጅት በኋላ ላይ የአዲስ አበባን አስተዳደርና የፓርላማ መቀመጫውን አልረከብም ቢልም ዶ/ር ብርሃኑ የዋና ከተማዋ ከንቲባ እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫውን አጭበርብሯል በሚል ለተቃውሞና ለአመፅ የወጡ አካላት ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በፈጠሩት ግጭት ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ፣ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ የቅንጅት አመራሮች ታስረው የነበረ ሲሆን ዶ/ር ብርሃኑ ግንቦት 7ን የመሠረቱት ከእስር ቤት እንደተለቀቁ ከአገር ቤት ከወጡ በኋላ ነው፡፡
ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እታገላለሁ የሚል ቢሆንም፣ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለማስወገድ የትጥቅ ትግልን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት መንገድ እንደሚጠቀም ይገልጻል፡፡ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያው ወራት በግንቦት 7 መሪነት የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ ሲያደርጉ ነበር ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወቅቱ በአምስት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ሲወስን፣ በሌሎች 33 ግለሰቦች ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስኖ ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት የሞት ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
በወቅቱ በሌሉበት የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው አቶ አንዳርጋቸው ከቅጣቱ በኋላ ለቢቢሲ ‘ፎከስ ኦን አፍሪካ’ ፕሮግራም በሰጡት አስተያየት ቅጣቱን ጠብቀውት እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ይኼ ውሳኔ ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስገራሚ አይደለም፡፡ የነፃነትን ዋጋ እናውቃለን፡፡ መብቶቻችንን ለማስጠበቅ ሁሌም ቢሆን መስዋዕትነት ለመክፈል እንገደዳለን፡፡ ይኼ መስዋዕትነት የሞት ቅጣት ከሆነ እሱን በፀጋ እቀበላለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በዚያ ቃለ ምልልስ ንቅናቄው የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት የትጥቅ ትግልን ጭምር እንደ አማራጭነት እንደሚጠቀም አስታውቀው ነበር፡፡ ‹‹ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊሰማ እስካልፈቀደ ድረስ እንዲሰማንና ከሥልጣንም እንዲለቅ ለማድረግ የምናስገድደው ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡
በ2003 ዓ.ም. ፓርላማው በሽብርተኝነት ከፈረጃቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ግንቦት 7 ሲሆን ሌሎቹ ኦብነግ፣ ኦነግ፣ አልቃይዳና አልሸባብ ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በድጋሚ ተከሰው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት በድጋሚ የሞት ቅጣት ተላልፎባቸው ነበር፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያ ዓመት አካባቢ የኢሕአዴግ መሥራች ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አባል እንደነበሩ በጻፉት መጽሐፍ ገልጸዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. በገዛ ፈቃዳቸው ከኢሕአዴግ እንደለቀቁ ‹‹ነፃነትን የማያውቅ ‹‹ነፃ አውጪ››” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ላይ አትተዋል፡፡ በስደት ይኖሩበት ከነበረው እንግሊዝ በ1983 ዓ.ም. ተመልሰው የብአዴን አባልና በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ኮሚቴ አባል በመሆን እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ ማገልገላቸውን አስፍረዋል፡፡ በተለያዩ የአመለካከት ልዩነቶች ከኢሕአዴግ ጋር መለያየታቸውን የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው ከእነዚህ መካከል ኢሕአዴግ በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ላይ ያለው አቋም፣ የኤርትራ ሪፈረንደም፣ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አስተዳደር፣ የኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሙስና መበራከት፣ አቅምን መሠረት ያላደረገ የአባላትና የአመራር ምልመላና ዕድገት፣ በኢሕአዴግ ላይ ከማንም ነፃ በሆኑ ኦዲተሮች ዓመታዊ የሒሳብ ቁጥጥር አለመደረጉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ኢሳት በተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ የኢሕአዴግ አባል እንዳልነበሩ ደግሞ አስተባብለዋል፡፡
የየመን አወዛጋቢ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የመን በቁጥጥር ሥር አቶ አንዳርጋቸውን እንዳዋለች ወዲያው ለኢትዮጵያ መስጠቷን ያረጋገጠ ሲሆን የመን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ለእንግሊዝ ሳታስታውቅ በሚስጥር ለኢትዮጵያ አሳልፋ መስጠቷ ከዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ ትችት የሚያቀርቡባት አሉ፡፡ ነገር ግን የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠችው በ1991 ዓ.ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በቀድሞ የየመን ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ መካከል በሁለቱ አገሮች የሚፈለጉ ወንጀለኞችን አሳልፈው ለመስጠት ባደረጉት ስምምነት መሠረት እንደሆነ በመግለጽ ራሷን ትከላከላለች፡፡
‘ዘ ኢኮኖሚስት’ መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ ግን የመን አሳልፎ መስጠቱን ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ተገቢነት ያላቸው ሥነ ሥርዓቶችን አልፈጸመችም፡፡ ለእንግሊዝ ባለሥልጣናት ቀድማ ሳታሳውቅ አሳልፋ መስጠቷ አንዱ ጥሰት እንደሆነም ጠቅሷል፡፡ መጽሔቱ ያነጋገራቸው አናንድ ዱባይ የተሰኙ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ሕግ ኤክስፐርት ቅድሚያ የማሳወቅ ሥነ ሥርዓት በቪዬና የኮንሱላር ግንኙነቶች ኮንቬንሽን የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የመን ለእንግሊዝ ኤምባሲ ሳታሳውቅ አሳልፋ መስጠቷ ሕጉን እንድትጥስ እንዳደረጋት አስረድተዋል፡፡
የሒዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ በበኩላቸው የየመንና የኢትዮጵያ ድርጊት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሕግ በሚጥልባት ግዴታ መሠረት አቶ አንዳርጋቸው በጠበቃቸው፣ በቤተሰባቸውና በእንግሊዝ ኮንሱላር ኃላፊዎች እንዲጐበኙ ማድረግ እንዳለባት ጠይቀዋል፡፡ የመንም ምንም ዓይነት የቅድመ አሳልፎ መስጠት ሥነ ሥርዓቶችን ሳትጠብቅ ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ አሳልፋ መስጠቷ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡
ሌፍኮ የመን ግርፋትን ለማስቀረት የተፈረመው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አፅዳቂ መሆኗን አስታውሰው፣ በኮንቬንሽኑ ተላልፎ የሚሰጠው ወንጀለኛ ለግርፋት የሚጋለጥ ስለመሆኑ በቂ ምክንያት ካለ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔው ሊቀር እንደሚገባ የተደነገገ ቢሆንም፣ የመን ይህን ችላ በማለት አሳልፋ መስጠቷም ሌላ ጥሰት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ሌፍኮ የኮንቬንሽኑ ድንጋጌ ኢትዮጵያና የመን ወንጀለኛን አሳልፎ ለመስጠት ከፈጸሙት ስምምነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ተከራክረዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የየመን ባለሥልጣናት መረጃ እንዲሰጡት በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ እንዳጣ በመግለጽ ሥጋት እንደገባው አስታውቆ ነበር፡፡ ድርጊቱም ከቪዬና ኮንቬንሽን ተፃራሪ እንደሆነ አመልክቶ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ቢሮው አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ አስቀድሞ የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው አስታወሶ እንግሊዝ በመርህ ደረጃ የሞት ቅጣትን ስለምትቃወም ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ እንዳታደርግ ጠይቋል፡፡
ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርት የየመን ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግን ስለመጣሱና አለመጣሱ ለመግለጽ የአገሪቱን ብሔራዊ ሕግና በኢትዮጵያና በየመን መካከል ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት የተፈራረሙትን ስምምነት በቅድሚያ ማጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የመንና ኤርትራ በሃኒሽ ደሴቶች ጉዳይ ግጭት ውስጥ ስለሆኑ ኤርትራን ለመጉዳት አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ መስጠቷን በመግለጽ የመን ሕጋዊ ግዴታዋን ለመወጣት አለመሞከሯን የሚተቹም አሉ፡፡
‹‹ለኢትዮጵያውያን የሚታገል እንግሊዛዊ››
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም በዜግነታቸው ግን እንግሊዛዊ ናቸው፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ አባል የነበሩበት ቅንጅት ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር የነበረውን አተካሮ ተከትለው አስቀድሞ ይኖሩበት በነበረው እንግሊዝ ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ፣ ዜግነት እንደተሰጣቸው የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ኑሯቸውን በኤርትራ አድርገው ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበርና ከሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመሥራት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ሲጥሩ እንደነበር አስታውቋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በኤርትራ ለሽብርተኞች ሥልጠና ሲሰጡ እንደነበር መረጃ እንዳለውም ተቋሙ አመልክቷል፡፡
ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን እንቆቅልሽ የሆነው ጥያቄ አቶ አንዳርጋቸው እንግሊዛዊ ከሆኑ ሉዓላዊ አገር የሆነችውን የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚታገል ንቅናቄን ለምን ይመራሉ የሚል ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ከሕግ አንፃር ሳይሆን የፖለቲካ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ከሚያስፈልግ የሞራል አቋም ጋር የሚያያዙት የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡ የትውልድ አገር በተለይ ከፖለቲካ ጋር በተገናኙ ምክንያቶች ዜግነትን በምትከለክልበት ወቅት፣ ለፖለቲካ ሥራ እንዲመች ሲባል የሌላ አገር ፓስፖርት መያዝና የሚቆሙለት ዓላማ ግን ዜግነት የከለከለችውን አገር ሕዝብ ማገልገል መሆኑ የተለመደ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደ ምሳሌም የቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የትጥቅ ትግል ያካሂድ የነበረውን ሕወሓትን እየመሩ የነበራቸው የሶማሊያ ፓስፖርት እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኤክስፐርት ግን የአቶ አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ፓስፖርት ከአገር አልባነት ዓውድ መታየት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹እርግጠኛ ነኝ እንግሊዝ የአቶ አንዳርጋቸው የጥገኝነት ጥያቄ ላይ ከመወሰኗና ፓስፖርት ከመስጠቷ በፊት የግል ሁኔታውን መርምራለች፡፡ ለምሳሌ አቶ አንዳርጋቸው በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልንና የመሳሰሉ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የተቀበላቸውን ወንጀሎች የትም ቢሆን ስለመፈጸማቸው የሚጠቁም ማንኛውም ዓይነት መረጃ እንዳለ ካወቀች ጥያቄውን ልትቀበለው አትችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ምክንያቶች በሌሉበት ሁኔታ ግን ጥያቄ ካቀረቡለት አገር ጋር ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ጠያቂዎቹ ካረጋገጡ ዓለም አቀፍ ሕግ አገር አልባነትን ለማስወገድ ዜግነት እንዲሰጥ ያበረታታል፤›› ሲሉ ኤክስፐርቱ ገልጸዋል፡፡ ኤክስፐርቱ በተጨማሪም የዜግነት ጥያቄው በዘፈቀደ ተከልክሏል ብሎ ያሰበ አመልካች በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር መብት እንዳለው ዓለም አቀፍ ሕግ ማረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡
ኤክስፐርቱ አገር አልባነትን ለማስወገድ በተመድ ሥር የተፈረሙት ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችን በርካታ አገሮች ባያፀድቋቸውም ግለሰቦች ዜግነት ሲያጡ ሌሎች አገሮች እንዲሰጡ የሚያበረታቱ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ዜግነት ሊጠፋ የሚችለው ወይ ዜጋው በፈቃደኝነት ዜግነቱ ይቅርብኝ ሲል አልያም ደግሞ ተገዶ ዜግነቱን ሲያጣ እንደሆነ የጠቆሙት ኤክስፐርቱ፣ ተገዶ ዜግነቱን የሚያጣ ግለሰብ ማመልከቻ ካስገባበት አገር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማረጋገጥ ይበልጥ እንደሚቸገር አመልክተዋል፡፡ በውጭ አገር ለረዥም ጊዜ መኖር ትክክለኛ ግንኙነት ለማረጋገጥ ጠቃሚ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ግን ዜግነትን ለማጣትም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕግ ከኢትዮጵያ ውጪ ተደራቢ የሌላ አገር ዜግነትን ይከለክላል፡፡ ይኼም ማለት አንድ ሰው የሌላ አገር ዜግነትን ሲያገኝ የኢትዮጵያ ዜግነቱ እንደተሰረዘ ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አገልግሎት በመግለጫው፣ ‹‹ጥምር ዜግነት መያዝ ማንንም ከተጠያቂነት አይከላከለውም፤›› ሲል አስታውቋል፡፡
ኤክስፐርቱ በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው ውሳኔዎች በሁለት ምክንያት ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡ አንደኛው ግለሰቡ ከኢትዮጵያ ጋር ጠላት ከሆነችውና በጦርነት ውስጥ እንዳለች ከምትወሰደው ኤርትራ ጋር መሥራታቸው እንደ ወንጀል የሚወሰድ መሆኑ ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በየመን ሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ እያሉ ነው፡፡ ኤርትራ በ1985 ዓ.ም. በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላ የአፍሪካ ቀንድ እየተባለ የሚጠራውን አካባቢ በማበጣበጥ የምትታወቅ ናት፡፡ በቅርቡም ተመድ በይፋ በሶማሊያ ከመሸገው አልሸባብ ጋር በመሥራት ሽብር እያስፋፋች ለመሆኗ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ኤርትራ ግንቦት 7ን ጨምሮ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚሠሩ ኃይሎች መቀመጫ ናት በሚል በኢትዮጵያ ሁሌም ትወቀሳለች፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው መሆኑን ኤክስፐርቱ ያስረዳሉ፡፡
የእንግሊዝ አቋም
ታዋቂው ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትን ጨምሮ በርካታ ተንታኞች በጉዳዩ ላይ የእንግሊዝ ድምፅ በጉልህ አለመሰማቱን ተችተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ዜጋው ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዳይሰጡ የውጭ ጉዳይ ቢሮው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አለማድረጉን በመኮነን በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው አስቀድሞ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ ልታደርግ ትችላለች በሚል ሥጋት የገባቸው አሉ፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮም ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ እንዳታደርግ ጠይቋል፡፡
የግንቦት 7 ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማደቦ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ የምሥራች ኃይለ ማርያምና በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ልዑካን በመምራት መጥተው የነበሩትና አሁንም የአውሮፓ ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጎሜዝ፣ በተለያዩ ሚዲያዎች የእንግሊዝ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን አነስተኛ ትኩረት አውግዘዋል፡፡ አንዳንድ የእንግሊዝ ሚዲያዎች እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸውን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ዘግበዋል፡፡
እንግሊዝና ኢትዮጵያ አብረው ከሚሠሯቸው ነገሮች መካከል ዋነኛው በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን መዋጋት መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ከሚያሴረውና በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ግንቦት 7 አመራሮች መካከል አንዱ ለሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዜግነት መስጠቱ ያልተዋጠላቸው አካላት፣ ጉዳዩ የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳያበላሽ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከርም የአቶ አንዳርጋቸውን ዜግነት መሰረዝ እንዳለባትም የጠየቁ አሉ፡፡
እንደ ቀደመው ጊዜ ሌላው አገር ለሚያራምደው ፖሊሲ ተቃውሞ ለማሳየት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት ዜግነቱን ለአቶ አንዳርጋቸው እንግሊዝ የሰጠች እንደሚመስላቸው የገለጹት ኤክስፐርቱ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ዜግነት የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጐዳል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡ አሁን የአቶ አንዳርጋቸውን ዜግነት መሰረዝ ለእንግሊዝ ቀላል እንደማይሆንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የግለሰቡ ፖለቲካዊ ባህርይ በተለይም ዜግነት የሰጠውን አገር የሚጐዳ ተግባር መፈጸሙ ዜግነቱን ለመሰረዝ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በተያያዘ መጠየቅ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ እንግሊዝ ግንቦት 7 እንዴት ነው የምትወስደው የሚለው ነው፡፡ ዜግነት ጥቅም ብቻ ሳሆን ግዴታም አለው፡፡ ዜግነት ለሰጠህ አገር ታማኝ መሆን አለብህ፡፡ የግለሰቡ እንቅስቃሴ ከዚያ አገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር ሊፃረር አይገባም፡፡ ይኼ የግንቦት 7 ድርጊት ከእንግሊዝ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ነው ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ አቶ አንዳርጋቸው በሽብርተኛነት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ነገር ግን እንግሊዝ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ለሽብርተኝነት የሰጠው ትርጉም በጣም ሰፋ ብሎ መተርጐሙ ላይ ተቃውሞ እንዳላት በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ ድንገት ያለመግባበት ምክንያት ሊሆን አይችልም፤›› ሲሉም ኤክስፐርቱ ይደመድማሉ፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ፖለቲካው ከዓለም አቀፍ ሕግ የበለጠ የሚመዝን በመሆኑ፣ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ ግንኙነት ዙሪያ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማይኖረው አመልክተዋል፡፡
ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሱት በቅርቡ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተነጋገሩትን የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ሊኔ ፊዘርስቶንን ነው፡፡ ሚኒስትሯ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አገራቸው በየዓመቱ የምትሰጠውን 300 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የልማት ድጋፍ አጠናክራ መቀጠልዋን ማስታወቃቸው፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከምንም ነገር በላይ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዓርብ ምሽት ከቢቢሲ ‹‹ፎከስ ኦን አፍሪካ›› ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ የሞት ፍርዱ ተፈፃሚ ይሆናል ወይ ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አሁን መናገር አልችልም›› በማለት ከማረጋገጥ የተቆጠቡ ሲሆን፣ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያን የኤርትራ መልዕክተኛ ሆነው የመበጥበጥ ሥራ እስከሠሩ ድረስ የእንግሊዝ ዜጋ መሆናቸው እሳቸውን በቁጥጥር ለማዋል ኢትዮጵያ ያለባትን የሞራልና የሕግ ግዴታ እንደማያስተጓጉለው ገልጸዋል፡፡ በሌሉበት ስለተፈረደባቸው በድጋሚ ጉዳያቸው እንዲታይ ይደረጋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ ‹‹በአገር ከሌሉ ምን ማድረግ እንችላለን›› ያሉ ሲሆን ጉዳዩ በድጋሚ ሊታይ እንደማይችል ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment