የግብፅን የናይል ታሪካዊ መብቶች ያስጠብቃል በሀይማኖት፣ በዘር፣ በፆታ እና በአካባቢ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት አይቻልም የግብፅ የጦር ኃይል አዛዥ በምርጫው ይወዳደራሉ
ከግብፅ የታህሪር አደባባይ አብዮት በኋላ የተደረገውን ምርጫ
አሸንፈው ስልጣን ላይ የወጡት “የሙስሊም ወንድማማቹ” ሞሀመድ ሙርሲ፤ በአጭር የስልጣን ዘመናቸው ህዝበ ውሳኔ
ተግባራዊ
አድርገውት የነበረው የ2012 ህገመንግስት ሰሞኑን በተደረገው የህገመንግስት ሪፈረንደም ተሽሯል። የሞርሲ
ህገመንግስት አጭር ጊዜ ስራ ላይ የዋለ ቢሆንም ብዙ ውዝግቦችንና አለመግባባቶችን ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡ ሙርሲ
ተግባራዊ ባደረጉት ህገመንግስት ውስጥ የተካተቱት አብዛኞቹ አንቀፆች እና አረፍተ ነገሮች በአዲሱ ህገመንግስት
ተሰርዘዋል። ነገር ግን አዲሱ ህገመንግስትም የወታደሩን የበላይነት የሚያስጠብቅ ነው በሚል ትችቶች እየተሰነዘረበት
ይገኛል፡፡ የናይል ጉዳይ በሁለቱም ህገመንግስቶች የተጠቀሰ ሲሆን አዲሱ ህገመንግስት ጠንከር ባለ አገላለፅ ነው ያስቀመጠው፡፡ በሙርሲ የፀደቀው ህገመንግስት “የናይል ወንዝ እና የውሀ ሀብቶች ብሄራዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ መንግስት እነዚህን ሀብቶች ለመጠበቅ እና ለማልማት ቁርጠኛ ነው፡፡
እንዳይባክንም ይከላከላል፡፡ የውሀው አጠቃቀም በህግ ይወሰናል”
ሲል ሰሞኑን የፀደቀው አዲሱ ህገመንግስት በአንቀፅ 44 ላይ ስለ ናይል የሚከተለውን ይላል፡- “መንግስት የናይል
ወንዝን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው፡፡ የግብፅን ታሪካዊ መብቶች ያስጠብቃል፡፡ የናይል ተጠቃሚነትን ያሳድጋል። ውሃው
እንዳይበከል እና እንዳይባክን ያደርጋል፡፡ የማእድን ውሃውን ለመጠበቅና የውሀውን ደህንነት ለማስጠበቅ በመስኩ
የሚካሄደውን ሳይንሳዊ ምርምሮች ይደግፋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የናይልን ወንዝ የመጠቀም መብት አለው፡፡ ውሀውን
ያለአግባብ መጠቀም ወይም አካባቢውን መጉዳት የተከለከለ ነው፡፡ ዝርዝሩ በሌላ ህግ ይደነገጋል፡፡” ሰሞኑን ህዝበ
ውሳኔ ተደርጎ አብላጫ ድምፅ እንዳገኘ የተነገረለት የግብፅ ህገመንግስት፤ ልክ እንደ ቀደምቶቹ የአገሪቱ
ህገመንግስቶች መነሻው ያደረገው የ1971ን የአገሪቱን ህገመንግስት ነው።
አዲሱ ህገመንግስት ከአንድ አመት በፊት በመሀመድ ሞርሲ አጭር
የስልጣን ዘመን በህዝበ ውሳኔ ከፀደቀው ህገመንግስት ጋር ቢመሳሰልም መሰረታዊ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ በመሀመድ
ሞርሲ ዘመን ተግባራዊ በተደረገው ህገመንግስት፤ “አልአዝሀር” ለተባለው ተቋም የእስልምና ህጎችን በተመለከተ ህግ
አውጭዎችን የማማከር ስልጣን ሰጥቶት የነበረ ሲሆን በአዲሱ ህገመንግስት ይህን ስልጣን ተነስቷል። የመከላከያ
ሚኒስትርን በተመለከተ ሁለቱም ህገመንግስቶች የመከላከያ ሚኒስትር ወታደራዊ መኮንን እንዲሆን ሲደነግጉ፣ የአሁኑ
ህገመንግስት እጩው በጦር ሀይሉ ከፍተኛ ምክር ቤት መፅደቅ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ የምርጫ ኮታን አስመልክቶ የቀድሞ
ህገመንግስት ገበሬዎች እና ሰራተኞች በታችኛው ምክር ቤት ቢያንስ የሀምሳ በመቶ መቀመጫ እንዲኖራቸው የሚደነግግ
ሲሆን አዲሱ ህገመንግስት ከላይ ለተጠቀሱት ቡድኖች ተሰጥቶ የነበረውን መብት በዝርዝር ህግ ይገለፃል በሚል
አልፎታል፡፡
በአዲሱ ህገመንግሥት በግብፅ ህገመንግስት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚመለከት አንቀፅ የተካተተ ሲሆን ከወሲብ ንግድ ጋር የተያያዘ እና ማናቸውም ህገወጥ
የሰዎች ዝውውር መከልከሉን ይደነግጋል፡፡ ማንኛውንም መልእክተኛ እና ነብይ መስደብ በወንጀል ያስቀጣል የሚለውን
በሞርሲ ህገመንግስት ላይ የተካተተ አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ያስወጣው አዲሱ ህገመንግሥት፤ የአለም አቀፍ ስምምነቶችን
በተመለከተም በሰብአዊ መብቶች ዙርያ የተደረጉ እና የፀደቁ ስምምነቶች እንዲሁም ቃልኪዳኖች ተግባራዊ የሚሆኑት
ታትመው ሲወጡ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ህግ አውጪውን አስመልክቶ የሞርሲ ዘመን ህገመንግስት ዋና አቃቤ ህግን የመሾምን
ስልጣን ለፕሬዚደንቱ የሰጠ ሲሆን በአዲሱ ህገመንግስት ስልጣኑ ወደ የህግ ከፍተኛው ምክር ቤት ተዛውሯል፡፡ የሞርሲ
ዘመን ህገመንግስት፤ ሴቶችን የወንዶች እህቶች በሚል ሲገልፅ፣ አዲሱ ህገመንግስት ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው
የሚል ሲሆን፤ ሴቶችን ከማንኛውም አይነት ጥቃት ለመከላከል መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አዲሱ ህገመንግስት
ሀይማኖትን፣ ዘርን፣ ፆታን እና አካባቢን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋም የተከለከሉ መሆናቸውን
በመደንገግ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በላይኛው ምክር ቤት የነበረውን ቦታ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል፡፡
ድብደባን በተመለከተ የበፊቱ ህገመንግስት ማንኛውም በእስር ላይ
ያለ ግብፃዊ ድብደባ ሊፈፀምበት እንደማይችል ሲያስቀምጥ አዲሱ ህገ መንግስት ማንኛውም ግብፃዊ በማንኛውም ሁኔታ
ድብደባ ሊፈፀምበት እንደማይቻል እና ድርጊቱም ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ሁለቱም ህገመንግስቶች የጦር ሰራዊት
(የመከላከያ) በጀት በህግ አውጭው አካል እንዳይጠየቅ ከለላ ሰጥተዋል፡፡ አዲሱ የግብፅ ህገመንግስት የ2011
አብዮትን ሌጋሲ ያስጠበቀ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ከሀይማኖት የተለየ ህገመንግስት ነው ቢባልም በህገመንግስቱ የተካተቱ
አንዳንድ አንቀፆች ግን የወታደራዊውን መንግስት አቋም የሚያጠናክሩና ግብፅን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ የሚመልሱ ናቸው
በሚል ትችቶች በስፋት እየተሰነዘሩ ነው፡፡ የቀድሞውም ሆነ አዲሱ ህገመንግስት ችግር “በሁለቱም ህገመንግስቶች
የተንፀባረቀው የቡድን ስሜት እንጂ ግብፅን እንደ አገር ማእከል ያደረገ አይደለም፡፡
ህዝበ ውሳኔው ላይ የቀረበው ከእስልምና ወንድማማችነት እና
ከመፈንቅለ መንግስት ወይም ከኢስላም እና ከሚሊተሪ የሚል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ቅድሚያ የተሰጣት ግብፅ ሳትሆን
ቡድኖች ናቸው” ይላሉ - ሁለቱንም ህገመንግስቶች የሚነቅፉት ወገኖች፡፡ የህገመንግስቱ ትልቁ ስህተት ይዘቱ ላይ
ሳይሆን የተረቀቀበት አካሄድ ላይ ነው የሚሉት በእስራኤል የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ጥናትና ዲፕሎማሲ ምርምር
ማዕከል ሊቀመንበር ዮራም ሜይታል ናቸው፡፡ እንደእሳቸው አገላለፅ፤ ህገመንግስቱ የተረቀቀበት መንገድ በወታደራዊው
መንግስት እና በእስልምና ወንድማማችነት መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከማካተት ይልቅ
ማስወጣት ላይ ያተኮረው አዲሱ ህገመንግስት፤ ስር እየሰደደ ያለውን የግብፃውያንን ልዩነት ለማከም የሚያስችለውን
ቅመም አጥቷል ይላሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የአዲሱ ህገመንግስት መፅደቅ በቀጣይ በግብፅ ለሚደረገው ምርጫ መንገድ
ይጠርጋል የተባለ ሲሆን የግብፅ የጦር ሀይል አዛዥ በምርጫው መወዳደር እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል፡፡ ይህም የሞርሲን
ደጋፊዎች እና የጦር ሃይሉን ፍጥጫ የሚያባብሰው ሲሆን የግብፅን ሰላምና መረጋጋትም በጥርጣሬ የተሞላ እንደሚያደርገው
የሚናገሩት ብዙዎች ናቸው፡፡
Source: Addis Admass
No comments:
Post a Comment