ከ123 አብያተ ክርስትያን የሚወጡ ታቦታት በ46 ጥምቀተ ባሕሮች ያድራሉ
በየዓመቱ በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሀገሪቱ ውስጥ
በጐዳናና በአደባባይ ከሚከናወኑ በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዲት የውጭ ሀገር ዜጋ በአንድ ዘመን ይህን በዓል
ከተመለከተች በኋላ፤ “በየትኛውም ሀገር የሚከበር ካርኒቫል የማይተካከለው፣” ስትል አድንቃ ጽፋለች።
ይቺ ጸሓፊ
በብራዚል ዘመን መለወጫ ላይ የሚፈፀመውን ካርኒቫል ጭምር በመጥቀስ ነበር የጥምቀቱን አቻ የለሽነት የገለጠችው፡፡
አውሮጳዊቷ ጥምቀትን የተመለከተችው አዲስ አበባ ላይ ነበር፡፡ የጥምቀትን በዓል የደመቀና ቀለማም የሚያደርገው
ከአከባበሩ ሥነሥርዓት ጋር በዓሉ የሚከናወንበት ቦታም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። በከተማና በገጠር ያለው አከባበርሥነ ሥርዓት አንድ ቢሆንም በድምቀቱ ይለያያል፡፡ ይህም ማለት በከተማ ውስጥ ብዙ ሕዝብና ብዙ ታቦታት በመኖራቸው ነው፡፡ “አርባ ዓራቱ ታቦት” የሚል የተሳሳተ ጥሪ የፈጠረው የጐንደሩ ጥምቀት፣ በነገሥታቱዋ ዘመን በጐንደር የነበሩት ፵፬ አድባራት በአንድነት ወጥተው፣ በነገሥታቱ የመዋኛ ቦታ ተሰብስበው እጅግ ልዩ ድምቀትና የበዙ ቀለሞችን ስለሚፈጥሩበት ነው፡፡ እንደዚህ ሲታይ ነው ጥምቀት በአዲስ አበባ እጅግ ልዩ ኾኖ የሚገኘው፡፡
በየትኛውም የሀገሪቱ ከተሞች ጥምቀት የሚከበረው በአንድ ቦታ
ሲኾን በአዲስ አበባ ውስጥ ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ የሚያስገርም ነው:- ጥምቀት አዲስ አበባ በሚባለው
ክልል ውስጥ በ46 የጥምቀት ባሕሮች ላይ ይከበራል! በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ120 በላይ የሚኾኑ
አብያተ ክርስትያኖች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቤተክህነት ባገኘነው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል
አከባበር መርሐ ግብር ዝርዝር መሠረት፤ 123 አብያተ ክርስትያን ወደተለያዩ ቦታዎች ታቦታቶቻቸውን ይዘው ይወጣሉ፤
ይመለሳሉ፡፡ መንገዶች ኹሉ ወደ ጥምቀተ ባሕሮች በሚሔዱ፣ ከጥምቀተ ባሕሩም ወደየቤታቸው በሚመለሱ ታቦታት እና
እነሱን አጅቦ በሚከተል ጥምቀትን አክባሪ ምዕመናን፣ ከከተራ ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ የተሞላ ይኾናል፡፡
በአንዳንድ ቦታዎችም አራተኛ ቀኑን (ጥር 13) ይጨምራል፡፡ ከእያንዳንዱ ቤተክርስትያን በትንሹ ሁለት ታቦታት
መውጣታቸው አይቀርም፡፡ በድምሩ ከሁለት መቶ ሃምሳ ያላነሱ ታቦታት፤ ዛሬ ጥር 10 ቀን ከየአድባራቱ በመውጣት ወደ
46ቱ ጥምቀተ ባሕሮች ይወርዳሉ፡፡
ከነዚህ የአዲስ አበባ ባሕረ ጥምቀቶች ውስጥ 15ቱ ብቻ ናቸው
የአንድ አንድ ቤተክርስትያን ታቦቶች ማደሪያና ጥምቀትን ማክበሪያ የሚሆኑት። ሁለት ሁለት ቤተክርስትያኖች
የሚያከብሩባቸው 12 ጥምቀተ ባሕሮች ያሉ ሲሆን፣ የሦስት ሦስት አብያተ ክርስትያን ታቦታት የሚያድሩባቸው ደግሞ 7
ባሕረ ጥምቀቶች ናቸው፡፡ በአምስት ባሕረ ጥምቀቶች አራት አራት ቤተክርስትያኖች እንደሚያድሩም ከቤተክሕነቱ ዝርዝር
ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ስሌት፣ አምስት አምስት አብያተ ክርስትያናት ጥምቀትን የሚያከብሩባቸው አራት
ባሕረጥምቀቶች ሲኖሩ፣ ከቀሩት ሦስት ባሕረ ጥምቀቶች ሁለቱ፤ ከስድስት እና ከሰባት አድባራት የሚወጡ፤ አንዱ ደግሞ
ከአስር አድባራት በሚወጡ ታቦታትና ምዕመናን በድምቀት የሚከበርበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጃንሜዳው ጥምቀተ
ባሕር፣ ከዚህ በፊት የ11 አብያተ ክርስትያናት ጥምቀት ማክበሪያ እንደነበረ የሚታወቅ ቢኾንም፣ በዘንድሮው ዝርዝር
ላይ ለማረጋገጥ የተቻለው በጥምቀተ ባሕሩ የሚያድሩት ከ10 አድባራት የሚወጡ ታቦታት እንደሆኑ ነው። ምናልባት
እንደምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ያለውንም በመቁጠር ይሆናል 11 ሲባል የቆየው ያስብላል፡፡ ስደተኛው በመባል
የሚታወቀው የምስካየኅዙናን መድኃኔዓለም ግን ለጥምቀትም ታቦቱ ከቤተክርስትያኑ የማይወጣበት ሥርዓት ካላቸው ገዳማት
አንዱ ነው፡፡ በጃንሜዳው የሚያድሩ ታቦታት ከታዕካ ነገሥት በዓታ፣ ከመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ፣ ከገነተጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ፣
ከመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም፣ ከቀጨኔ ደ/ሰ/መድኃኔዓለም፣ ከደ/ነ/ቅ/ዮሐንስ፣ ከመ/ል/ቅ/ማርቆስ፣
ከቀበና መ/ሕ/አ/ገ/መ/ቅዱስ፣ ከገነተ ኢየሱስ እና ከአንቀጸ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚወጡ ታቦታት
ናቸው፡፡ ከጃንሜዳው በመቀጠል ከሰባት አድባራት የሚወጡ ታቦታት፤ ጥምቀትን የሚያከብሩበት ጥምቀተ ባሕር ደግሞ
በኮልፌ - ቀራንዮ፣ በትንሹ አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኘው ገዳመ ኢየሱስ ቅጽረ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ቦታ የቀራንዮ
መድኃኔዓለም፣ የደብረ ገሊላ ዓማኑኤል፣ የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ የገዳመ ኢየሱስ፣ የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ
ፊልጶስ፣ የወይብላ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም እና የፊሊዶሮ አቡነተክለሃይማኖት ታቦታት ያድራሉ፡፡
በኮተቤው ወንድይራድ ት/ቤት አጠገብ በሚገኘው ጥምቀተ ባሕር
ደግሞ ከ6 አድባራት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ፡፡ በጉለሌው የራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 24 ቀበሌ 15፣
በደብረ ዘይት መንገድ ፍሬሕይወት ት/ቤት አጠገብ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 26 ቀበሌ 06 አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኙት
ባሕረጥምቀቶች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ከአምስት አብያተ ክርስትያናት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ። ከጥምቀት በዓል ቀጥሎ
ጥር 12 ቀን በሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓልም በጥምቀተ ባሕሩ ሁለት ሌሊቶችን የሚያድሩት የቅዱስ ሚካኤል አብያተ
ክርስትያን ታቦታት ወደየቤተክርስትያናቸው ይመለሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ በቅዱስ ሚካኤል ስም የሚታወቁ 14
አብያተ ክርስትያን አሉ፡፡ እነዚህም በ14 የተለያዩ ጥምቀተ ባሕሮች የሚያድሩ ናቸው። በጃንሜዳ፣ በየካ ወረዳ 16
ቀበሌ 11 ኳስ ሜዳ፣ በኮተቤ ወንድይራድ ት/ቤት፣ በቦሌ ወረዳ 20 ቀበሌ 01፣ በየረር ሠፈራ አካባቢ፣ በጉለሌ
ራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በቤቴል ኳስ ሜዳ፣ በላይ ዘለቀ መንገድ አዲሱ ገበያ፣ በመንዲዳ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ በመካኒሳ ወረዳ
23 ቀበሌ 04፣ በአፍሪካ አንድነት አካባቢ ወረዳ 23 ፊት ለፊት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጨፌ ዳዲ ሜዳ፣ በአቃቂ
ወንዝና በቃሊቲ አካባቢ የሚያድሩ የሚካኤል ታቦታት በጥር 12 ነው ወደየቤተክርስትያናቸው የሚመለሱት፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የሚካኤል ታቦትን በድርብ የያዘው የቅዱስ
እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን ታቦቶችም በዚሁ እለት ነው ወደቤታቸው የሚመለሱት፡፡ በአዲስ አበባ ከጥምቀት ጋር ተያይዞ
የሚከበረው የእግዚአብሔር አብ የንግሥ በዓልም በተመሳሳይ ኹኔታ ታቦታት ወደመንገዶች እና አደባባዮች በመውጣት
የሚከበር ነው። በአራተኛው ቀን ጥር 13 በተመሳሳይ ሁኔታ የሚከበርባቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ የደብረ ምጽላል
እግዚአብሔርአብ፣ በአዲሱ ገበያ ደብረ ሲና እግዚአብሔርአብና በጉለሌው ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ጥምቀት
በአዲስ አበባ በሰሜን ከእንጦጦና ከቃሌ ተራራ ጀምሮ እስከ ደቡብ የቃሊቲ ገጠሮች ድረስ፣ በምዕራብ ከትንሹ አቃቂ
ወንዝ እስከ ምሥራቅ ወንድ ይራድ ት/ቤት (ኮተቤ) ድረስ በጐዳናዎች፣ በአደባባዮችና በየማርገጃው ለአራት ቀኖች
ያህል እንዲህ ባለ አጀብና ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ፀሐፊውን በሚከተሉት የኢ-ሜልና ፌስቡክ አድራሻ ማግኘት
ይቻላል::
Source: Addis Admass
No comments:
Post a Comment