Time in Ethiopia:

Oct 2, 2013

ኢትዮጵያን ያየሁበት ዓይን

Geez Bet | Wednesday, October 02, 2013
ያን ፊሊፕ ቫይል ተወልዶ ያደገው በክሬፌልድ ከተማ ጀርመን ሀገር ሲሆን ጀርመናዊው ወጣት ገና የ14 ዓመት ልጅ ሳለ ነው ከጓደኛው ጋ በመሆን ለኢትዮጵያ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው። ይሄው ወጣት በአሁኑ ሰዓት «ኤምራ እና ዳቦ» የሚል ፊልም ኢትዮጵያ ውስጥ በመቅረፅ ላይ ይገኛል። 

« 8ኛ ክፍል ነበርን ያኔ። በዕረፍት ሰዓት ያለማቋረጥ ቋሊማ እና ከስንዴ እና እንቁላል የተሰራ ጣፋጭ ቂጣ( ዋፍል) እንሸጥ ነበር። ከዛም በተጨማሪ ክሪፌልድ በሚገኙ የምሽት ክበቦች የተለያዩ የአፍሪቃ ድግሶች እናዘጋጅ እና ገንዘብ እናሰባስብ ጀመር። ከዛም 11ኛ ክፍል ስንደርስ ባንድ ጊዜ ያሰባሰብነው ገንዘብ 20 000 ዩሮ ደረሰልን።» ይህንንም ገንዘብ ያሰባሰቡት ካርል ሀይንስ በኧም ለመሰረቱት «ሰዎች ለሰዎች» ለተሰኘው ድርጅት ነው። ያን እና ጓደኛው ለ ድርጅት ብዙ ገንዘብ ስላሰባሰቡም ካርል ሀይንስ ቡም ሁለቱንም ኢትዮጵያ ሄደው እየተሰራ ያለውን እንዲጎበኙ ጋበዙዋቸው። በዕውን ለማያውቋት ሀገር ገንዘብ ያሰባሰቡት ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ጀመሩ ። ከዛ ሲመለሱም የበለጠ ለመርዳት ተነሳሱ። ለት/ቤት ግንባታ የታቀደው 20000 ዮሮ በቂ ስላልነበረም አስፈላጊ የነበረውን 50 000 ዮሮ ለማሰባሰብ እንደተበረታቱ ያን ይናገራል።

« አዎ! ተመልሰን እንደመጣን ክሪፌልድ በሚገኙ ት/ቤቶች እና በቤተ ክርስትያን የአባላት ማህበር ስለ ሰዎች ለሰዎች ስራ እና በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እንገልፅ ጀመር። ኋላም የርዳታ ማህበር አቋቋምን። 150000 አባላት አሉን በየወሩ አንድ ዮሮ ርዳታ መስጠት የሚችሉ። በአሁኑ ሰዓት የተሰበሰበው 75 ሺ ዮሮ ደርሷል። እና የተጀመረውም ት/ቤት ተሰርቶ አለቀ። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ በበጎ ፍቃደኝነት የጀመርኩትን ስራን በ2009 ዓም አልቆ ማየት መቻሌ እጅግ የሚያስደስት ነበር። »
ከኢትዮጵያ ጋ ጥብቅ ትስስር እንዲኖረው ትልቅ ሚና የተጫወቱት የወቅቱ የማህበራዊ ኢኮኖሚ አስተማሪው እንደሆኑ ይናገራል። ዛሬ የ26 አመቱ ያን ባለትዳር ነው። ባለቤቱ ኢትዮጵያዊት ናት። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሙኒክ በሚገኝ ዮንቨርስቲ የፊልም ስራ ያጠናል። በተጨማሪም « ኤምራ እና ዳቦ» የተሰኘ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀርፀው ፊልም፣ ደራሲ የፊልም መሪና ዋና አዘጋጅ ነው።
« ኤምራ እና ዳቦ»
« ኤምራ እና ዳቦ የሁለት ጓደኛሞች ታሪክ ነው። በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጓደኛሞች ኤምራ እና ዳቦ በልጅነታቸው ይለያያሉ። ኃላም ሁለቱም በተለያየ መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሚኖሩባት አዲስ አበባ ይጓዛሉ። እዛም ህልማቸውን እውን ማድረግ ይፈልጋሉ። አንደኛው ጎበዝ ማራቶን ሯጭ ለመሆን ሲጥር ሌላኛው ደግሞ ፎቶ አንሽ መሆን ይፈልጋል።» ይሁንና ፎቶ አንሽ ለመሆን ያለመው ወጣት መጨረሻው የአዲስ አበባ ጎዳና ይሆናል። ሁለቱ ጓደኞችም ዳግም አዲስ አበባ ላይ ይገናኛሉ። ታሪኩ አንድ ሰው ምኞቱን ዕውን ለማድረግ ምን አይነት ጥረት እንደሚያደርግ እና ለጓደኝነት ምን ያህል መስዋት መክፈል እንደሚቻል ያንፀባርቃል ይላል፣ የፊልሙ ደራሲ። ታሪኩ ልብ ወለድ ብቻ ሳይሆን በከፊል በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ነው።
« ኤምራ እና ዳቦ» ፊልሙ በሚቀጥለው ዓመት በሲኒማ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል
« በታሪኩ መካከል በርግጥ የተከሰቱ ነገሮች ይንፀባረቃሉ። ለምሳሌ ሁለቱ አዳጊ ወጣቶች መንደራቸውን ትተው የሚሄዱበት ሁኔታ፣ መንደራቸው ያገኙት ነጭ የውጭ ዜጋ በዲጂታል ካሜራ ፎቶ ማንሳቱ እና ኤምራ የራሱን ፎቶ ሳይ እሱም ካሜራ እንዲኖረው ተመኝቶ መንደሩን ትቶ ወደ ከተማ መሰደዱ…» ሌላም ሌላም በእውነታ ላይ ያተኮሩ ነገሮች በፊልሙ ላይ ይስተዋላሉ። ያን እና ባልደረቦቹ የጀመሩት ፊልም ግን ተሰርቶ አላለቀም። ከ90 ደቂቃው ፊልም 50 ደቂቃው ገና አልተቀረፀም።
« እስካሁን ሁሉንም ወጪ ራሳችን ነን የቻልነው። 18 የጀርመን ባልደረቦቼ የበረራ የመኖሪያ እና ምግባቸውን ራሳቸው ችለው ነው እየሰሩ ያሉት። ከ25 የሚበልጡ የፊልም ባልደረቦች እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፤ እነሱም በጠቅላላ ለነበረን የ 3 ወር የቀረፃ ጊዜ ያለ ምንም ክፍያ ነው ሲሰሩ የቆዩት። ፊልሙን ጀርመን ውስጥ ሲኒማ ቤት እንደሚታዩ ፊልሞች ከከተማው ድጎማ አግኝተን ለመስራት አንችልም። »ስለሆነም ያን እና ባልደረቦቹ በአሁኑ ሰዓት ፊልሙን ለመጨረስ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት እንደ አማራጭ ያዩት የህዝብ መዋጮ (ክራውድ ፈንዲንግ) ነው።
«ክራውድ ፈንዲንግ ማለት፤ አንድ ሰው ያለውን የፕሮጀክት ሀሳብ ኢንተርኔት ላይ ያወጣል። ከዛ ያንን ፕሮጀክት የሚደግፉ ወይም የዛ አካል መሆን የሚፈልጉ ሰዎች የተወሰነ የድጋፍ ገንዘብ በመስጠት ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ኤምራ እና ዳቦን የክራውድ ፈንዲንግ ገፅ indiegogo.com ላይ ከ40 ቀን በፊት አውጥተንዋል። ፊልሙን ለመቅረፅ በአጠቃላይ የሚያስፈልገንን 200,000 ዶላር ለማሰባሰብ አሁን 2 ሳምንት ተኩል ይቀረናል። »
ገንዘቡን ለማግኘታቸው ምንም ዋስትና የለም። ይሁንና ርዳታ ሰጪው ገንዘብ ብቻ መስጠት እንዳይሆንበት ትናንሽ ስጦታዎች ከድጋፍ ጠያቂዎቹ ያገኛል። ፊልሙን የሚፃወቱት ተዋናዮች ሳይሆኑ ራሳቸውን ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች ናቸው ይላል ያን ። የፊልሙን ታሪክ ለመፃፍ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት እንዲህ ይገልፀዋል። «በ2007 እና በ2008 በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ9 ወራት ቆይቻለሁ። ለ7 ሳምንታት የታቀደው ጉዞዬ በመጨረሻ 9 ወራት ፈጅቷል። በዚህ ጊዜም ለፊልሜ አስፈላጊ የነበረውን ሁሉ ማሰባሰብ ችያለሁ። ያ ማለት ለ 4 ሳምንታት አዲስ አበባ ከሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ጋ አብሬ በቅርበት ቆይቻለሁ፣ ከምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ ርቄ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ከገበሬ አባወራዎች ጋ ቱኩል ውስጥ ቆይቻለሁ። በእንጦጦ ተራራ ላይ ከታዋቂ የማራቶን ሯጮች ጋ አብሬ ሰልጥኛለሁ። እና በዚህ መንገድ ነው ልገልፀው የፈለኩትን ታሪክ ያሰባሰብኩ።»
ፊልሙ በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋ ሲሆን በሌሎች ሀገሮች እንዲታይም በጀርመንኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችም ተተርጉሞ ይቀርባል። የያን እና ባልደረቦቹ ምኞች ዕውን ከሆነም በሚቀጥለው ዓመት በሲኒማ ይታያል።
ልደት አበበ
ተክሌ የኋላ
Source: www.dw.de

No comments:

Post a Comment