Time in Ethiopia:

Oct 5, 2013

ከ3ሺህ በላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከግቢ ተባረሩ

Geez Bet | Saturday, October 05, 2013
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ አመትና የሁሉም የምህንድስና ዘርፍ ተማሪዎች ከትላንት በስቲያ ከግቢ መባረራቸውን የአዲስ አድማስ ምንጮች ገለፁ፡፡ ለተማሪዎቹና ለዩኒቨርሲቲው ግጭት ምክንያት የሆነው የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሆነም ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡
የሁሉም የምህንድስና ተማሪዎች አራተኛ አመት ላይ ሲደርሱ የብቃት ምዘና ፈተና ይወስዳሉ ያሉት ምንጮቹ፣ የዘንድሮው ተማሪዎች ግን ለእረፍት ወደየቤታቸው ሲሄዱ ሞጁል ይዘው ሄደው አጥንተው መፈተን ሲገባቸው፣ ድንገት ተፈተኑ መባላቸው እንዳስደነገጣቸው ገልፀዋል፡፡

“የሁለት ቀን ትምህርት ተሰጥቷችሁ ተፈተኑ መባላችን ትክክል አይደለም” ያለችው አንዲት የዩኒቨርስቲው ተማሪ፤ “ከእኛ በፊት የነበሩት የአራተኛ አመት ተማሪዎች ሳይፈተኑ “Holistic pass” (ምዘናውን እንዳለፉ የሚልጽ) ወረቀት እንደተሰጣቸው እናውቃለን” ብላለች፡፡
የብቃት ምዘና ፈተናው የሚጀምረው ካለፈው አመት ተማሪዎች እንደነበር የገለፀችው ተማሪዋ፤ ዘንድሮ ከእኛ መጀመሩ አግባብ አይደለም፣ ቢጀመርም ከልምምድ በኋላ እንዲሆን ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም ብላለች፡፡
“እኛ አንፈተንም አላልንም ግን የሶስት አመት ትምህርት በሁለት ቀን ቲቶር ለፈተና አያበቃም” ያለው ሌላው ተማሪ፤ የፈተናው ጊዜ ይራዘምልን ብለው በመጠየቃቸው “ብትፈተኑ ተፈተኑ ያለበለዚያ ግቢውን ልቀቁ” ተብለው በፖሊስ ሃይል ከግቢ መባረራቸውን ገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሶስት ሺህ በላይ ተማሪዎች ከግቢው እንደተባረሩና በአርባ ምንጭ ከተማ ሲቀበላ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ብዙ ተማሪ እንደሚገኝ የተናገረው የሲቪል ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ፤ ሌሎቹም በመስጊድና በየአስፓልቱ ላይ እየተንገላቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡
“ያለ ምግብና ያለ መጠለያ በረሃብ ልናልቅ ነው” ያለው ሌላው ተማሪ፣ መንግስት በአስቸኳይ ለጉዳዩ እልባት ይስጥልን ሲል ተማጥኗል፡፡ ከአራተኛ አመት ተማሪዎች በተጨማሪ የአምስተኛ አመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎችም መባረራቸውን የጠቀሰው ተማሪው፤ ሳናጠና እና ሞጁል ሳይዘጋጅ በሁለት ቀን የክፍል ጥናት ብቻ የሶስት አመት ትምህርት ተምረን ውጤት ልናመጣ ስለማንችል ባንፈተን ይሻላል የሚል አቋም መያዛቸውን ተናግሯል፡፡
“ዩኒቨርስቲው ሃላፊዎቹ የሚሏችሁን ሰምታችሁ ካልተፈተናችሁ ምንም አይነት አገልግሎት ከግቢው አታገኙም በሚል በፖሊስ ሃይል ተባረናል” ያለው ይሄው ተማሪ፤ ወደ ቤተሰብ ለመመለስም ሆነ እዛው ከተማ ውስጥ አልጋ ይዞን ለመቆየት ምንም ገንዘብ እንደሌላቸው ጠቁሞ በችግር ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ትላንትና ረፋድ ላይ በከተማው ፖሊስ ጣቢያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ “ተሰብሰቡና እንነጋገር” የሚል ሃሳብ ከዩኒቨርሲቲው ሰዎች ቀርቦ ተማሪዎች አዳራሹን ሞልተው፣ ሃላፊዎቹን ለረጅም ሰዓት ቢጠባበቁም ማንም እንዳልመጣና በመጨረሻም ተማሪዎች መበታተናቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለምህንድስና ተቋሙ ፕሬዚዳንት ለዶ/ር ካሳሁን እና ለዩኒቨርስቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ሃላፊ ለዶ/ር ተሾመ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ልናገኛው አልቻልንም በዩኒቨርስቲው የተለያዩ የቢሮ ስልኮች ደውለን ጉዳዩን ለማጣራት ያደረግነው ጥረትም ስልኮቹ ባለመነሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
Source: http://www.addisadmassnews.com/
 

No comments:

Post a Comment