Time in Ethiopia:

May 19, 2014

ኢትዮጵያና ግብፅ ያቋረጡትን ድርድር እንዲጀምሩ የአሜሪካ መንግሥት ጥሪ አቀረበ

Geez Bet | Monday, May 19, 2014
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግብድ ግንባታ የአሜሪካ መንግሥት ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠውና ግድቡን በተመለከተ የኢትዮጵያና የግብፅ መንግሥታት ያቋረጡትን ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቀረበ፡፡ 
የአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ባለፈው ረቡዕ የአሜሪካ መንግሥት ከሰሐራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች የሚሰጠውን ትኩረት አስመልክቶ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ከአሜሪካ ሆነው በቀጥታ ቪዲዮ ኮንፈረንስ ተነጋገረው ነበር፡፡ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት ከታላቁ የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያና ከግብፅ መንግሥታት ጋር ትልቅ ውይይት በማካሄድ፣ ሁለቱ አገሮች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል፤›› ሲሉ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
 የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ባለችው የታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ያለውን አቋም አስመልክቶ በተጨማሪ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በመጀመሪያ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የሚስተዋለው የቃላት ጦርነት የአሜሪካ መንግሥትን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ሁለቱ መንግሥታት ወደ ንግግር መምጣት እንዳለባቸውና ተገናኝተው ሊወያዩ ይገባል፣ ያሉት ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ፣ ልዩነታቸውን ሊያስታርቁ ይገባል ሲሉ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሁለቱ ኢትዮጵያና ግብፅ መካከል የተወሰነ ድርድር እንደነበር የአሜሪካ መንግሥት የሚገነዘብ መሆኑን የገለጹት ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ፣ አሁንም ሁለቱ መንግሥታት ያቋረጡትን ድርድር በድጋሚ በመጀመር ለሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅም የሚበጅ መፍትሔ ላይ ቢደርሱ እንደሚሻል አስረድተዋል፡፡ 
ረዳት ሚንስትሯ ሊንዳ ቶማስ ከአፍሪካ ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ያደረጉት ውይይት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ፣ የአፍሪካ ጉብኝት በቅርቡ በአሜሪካ በሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቅርቡ በሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የኤርትራ፣ የዚምባቡዌ፣ የሱዳንና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች እንደማይጋበዙ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን የሚስተዋለውን የእርስ በእርስ ግጭት አስመልክቶ ሁለቱ የግጭቱ ተዋናዮች የሰላም ስምምነቱን ወደ መተግበር እንዲገቡ፣ ካልሆነ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment