-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ግብፅ ለድርድር ፈቃደኛ ናት ብለዋል::
በግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሆኑት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን በመጐብኘት የሁለቱን አገሮች የዓባይ ውኃ ግጭት በውይይት ለመፍታት እንደሚጥሩ አስታወቁ፡፡
በተመሳሳይም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋህሚ የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኗን መግለጻቸውን፣ የግብፅ ጋዜጣ አል አህራም ዘግቧል፡፡
ከ‘አል አህራም’ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቀድሞው የጦር ኃይሉ መሪ አልሲሲ፣ ‹‹የግብፅና የኢትዮጵያን ቀውስ ለመፍታት ምርጡ መንገድ የሁለትዮሽ ድርድርና መግባባት ነው፤›› ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ከግጭትና ከጠላትነት ይልቅ ስምምነት የተሻለ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው የገለጹት አልሲሲ፣ ግብፅን የሚጠቅም ከሆነ ኢትዮጵያን ለመጐብኘት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
‹‹ይህ ወደ ግጭት ከመግባትና ከማንም ጋር ጠላት ከመሆን የተሻለ ነው፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
የቀድሞ የግብፅ የጦር ኃይል አዛዥ የግብፅ የውኃ መብት ጉዳይ የሕይወትና የሞት ጉዳይ መሆኑን ግን አስረግጠው ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋህሚ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር አገራቸው ለመደራደር ያላትን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ያደረጉት ድርድር ፍሬያማ እንዳልሆነ መጠቆማቸውን የገለጸው የአል አህራም ዘገባ፣ ሚኒስትሩ ይህ ሌላ ውይይት ለማድረግ ግብፅን እንደማያዳግት መግለጻቸውን ገልጿል፡፡
ከቀናት በፊት አሜሪካ ሁለቱ አገሮች ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ ማድረጓን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment