Time in Ethiopia:

Apr 2, 2014

የአንድነት አመራሮች በወላይታ ሶዶ እንግልትና የንብረት ውድመት ደረስብን አሉ

Geez Bet | Wednesday, April 02, 2014
 ለውይይት ወደ ወላይታ ሶዶ ሄደው የነበሩት የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች  ከፍተኛ እንግልትና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው ገለፁ፡፡ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊውን ጨምሮ  የፓርቲው የወረዳው አመራሮች ተንቀሳቃሽ ስልኮች ባልታወቀ ኬሚካል ተነክረው ከጥቅም ውጭ መደረጋቸውን የአንድነት ፓርቲ አመራር  አቶ ዳንኤል ተፈራ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ 
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በአንድነት አጠቃላይ እንቅስቃሴና በተሻሻለው የፓርቲው ፕሮግራም ላይ ለመወያየት አቶ ዳንኤል ተፈራና ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ በተደረገላቸው ጥሪ፣  ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ መጓዛቸውን ገልፀው፣ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ በአንዱ የአንድነት አባል መኖርያ ግቢ ውስጥ ቡና እየጠጡ ለመወያየት መወሰናቸውን  ይናገራሉ፤ አቶ ዳንኤል ተፈራ፡፡ 

በምክትል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው የመግቢያ ንግግር ተደርጐ ውይይቱ ሊጀመር ሲል ከስምንት እስከ አስር የሚጠጉ ሰዎች የግቢውን በር በእርግጫ ሰብረው መግባታቸውን ያስታወሱት ሃላፊው፤ሰዎቹ በቀጥታ ፊት ለፊት ያገኙትን እቃ መሰብሰብ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ታርጋ በሌላቸው ሞተርሳይክሎች እንደመጡ የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ማንነታቸውን እንዳልገለፁ፣ ምን እየሰሩ እንደነበር  አለመጠየቃቸውንና ምን እንደሚፈልጉ አለማሳወቃቸውን ገልፀው፤ እጃቸው ላይ የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ፕሮግራም፣ የግል ማስታወሻ ደብተራቸውን፣በአጠቃላይ ፊት ለፊት ያገኟቸውን ንብረቶች ሰብስበው እንደወሰዱ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሃላፊውን 16ሺህ ብር የሚያወጣ ተንቀሳቃሽ ስልክ አንገቱን በከረባቱ በማነቅ እንደወሰዱበት አቶ ዳንኤል እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 
ንብረቱን የወሰዱት አራት ሰዎች ቀድመው ሲሄዱ፣ ሌሎቹ አራቱ አብረዋቸው እንደቀሩ ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፤ ህገ ወጥ ስብሰባ ስላደረጋችሁ ፖሊስ ይምጣና ወደ ጣቢያ ትሄዳላችሁ እንዳሏቸው ገልፀው፣ በኋላም ከፖሊሶች ጋር ወደከተማው ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን ይገልፃሉ፡፡
“ፖሊስ ጣቢያ እንደደረስን የወላይታ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑትን ሻለቃ ላሊሼ አሌን አገኘናቸው” ያሉት አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ፖሊስ ለምን አመጣሃቸው ተብሎ ሲጠየቅ “ህገ-ወጥ ስብሰባ ሲያደርጉ አገኘኋቸው” የሚል ምላሽ እንደሰጠ ተናግረዋል፡፡
“በኋላም ሞባይላችሁን ፊት ለፊት ቁጭ አድርጉ ተብለን፣የፖሊስ አዛዡን በማመንና ህግ አስከባሪነታቸውን በመቀበል የታዘዝነውን አደረግን” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ወደ ሌላ ክፍል ተወስደው እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ልክ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ የከተማው መብራት ጠፋ፤ ይሄኔ የእኔና የሌሎች 20 የአንድነት የወረዳ አመራሮች ስልክ ባልታወቀ ፈሳሽ ኬሚካል ተነክሮና በአረፋ ተጥለቅልቆ ተሰጠን” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ስድስት ሰዓት ላይ ውጡ ሲባሉ ለደህንነታቸው ሰግተው ላለመሄድ አመንትተው እንደነበር፤ ነገር ግን ፖሊስ ጣቢያውም የበለጠ ስለሚያስፈራ ወጥተው ወደያዙት መኝታ መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ የሁሉም ሞባይል ስልክ ከጥቅም ውጭ ሆኖ እንደመጣ ጠቁመው፣ ባለ 16 ሺህ ብሩ የአቶ ዳንኤል ሺበሺ ሞባይል ስልክ ግን ከእነአካቴው እንዳልተመለሰ ተናግረዋል፡፡ “እኛ ህጋዊና በህጋዊ መንገድ የምንቀሳቀስ የፓርቲ አመራሮችና አባላት ብንሆንም በከተማው ህገ ወጥ ሰዎች የደረሰብን እንግልት፣ እስራትና የንብረት ውድመት አሳፋሪ ነው” ሲሉ አቶ ዳንኤል አውግዘውታል፡፡ 
“ህገወጥ ስብሰባ አላደረግንም፣ ልንወያይ የነበረው በአጠቃላይ በዞኑ የፓርቲው እንቅስቃሴ፣ በተሻሻለው የአንድነት ፕሮግራምና በአካባቢው ያሉ የአንድነት አባላትና አመራሮች ለ2007ቱ ምርጫ በገንዘብም ሆነ በእውቀት አቅማቸውን እንዴት ይገንቡ በሚለው ጉዳይ ላይ ነው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ህገወጥ ስብሰባ አደረጉ በሚል ባልዋልንበት አውለውናል ብለዋል፡፡ “ህጋዊ ስብሰባ ማድረግ እየቻልን እንዴት ህገወጥ ስብሰባ እናደርጋለን?” ሲሉም የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ዳንኤል ተፈራ ጠይቀዋል፡፡   
ጉዳዩን በተመለከተ በስልክ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ላሊሼ ኦሌ፤ ለምን ጉዳይ እንደምንፈልጋቸው ጠይቀውን ከነገርናቸው በኋላ “አሁን ስብሰባ ላይ ነኝ፤ ስጨርስ እደውላለሁ” ብለውን ነበር፡፡ እሳቸው ባለመደወላቸው እኛ ደጋግመን የደወልን ቢሆንም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  

Source: Addis Admass

No comments:

Post a Comment