ጊዚያዊ ጥቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት የሩሲያ ጦር በሳቸዉ አገላለጥ ለክሪሚያ «ገንጣይና ከፋፋዮች» ከለላ መስጠቱ
እዉነት ነዉ።የዚያኑ ያክል ያዜንዩክና ጓዶቻቸዉ በዩናይትድ ስቴስና በተባባሪዎችዋ እቅፍ ዉስጥ መሆናቸዉም ሐቅ።
የኪየቭ-አዲስ መሪዎች የትንሽ ግዛታቸዉን ትንሽ ጠላቶቻቸዉን ትተዉ የትልቅ ጎረቤታቸዉን ትልቅ ጠላታቸዉን እያወገዙ ደግሞ በተቃራኒዉ እንደራደር ይላሉ።የበርሊን-ለንደን-ፓሪስ መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ኪየቮችን ለፍጥጫ እያጃገኑ፤ ሞስኮዎችን ለመቅጣት እየዛቱ ከኪየቮች ጋር ተወያዩ ይላሉ።ኪየቭ-ብራስልሶችን የሚመሩት የዋሽግተን መሪዎች ሞስኮዎችን የሚያስፈራራ ጦር እያዘመቱ፤ ሞስኮዎችን እየቀጡ፤ ለተጨማሪ ቅጣት እየዛቱ ከሞስኮዎች ጋር ይደራደራሉ።የሞስኮ ጠላቶች የሌሉ ያክል የዘነጓቸዉ የክሪሚያ የሞስኮ ታማኞች ትንሺቱን፤ ጥንታዊቱን ሥልታዊ ግዛታቸዉን ለሞስኮዎች ለማስረከብ ወሰኑ።ሩሲያዎችም አስወሰኑ።የጦር ዘመቻ፤ የቅጣት እርምጃ፤ ፉከራዉ ገቢር ይሆን-ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
በሩሲያ የሚደገፉት የዩክሬንዋ ትንሽ-ልሳነ ምድር ግዛት የክሪሚያ ራስ-ገዝ መስተዳድር ጠቅላይ ሚንስትር ስርጌይ አክሲየኖቭ፤ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ቭላድሚር ኮንስታንቲኖቭ ከየካቲት ማብቂያ ጀምሮ-ካቢኔ ምክር ቤታቸዉን እንዳስወሰኑ፤ እንደዛቱ፤ እንደፎከሩት በርግጥም አደረጉት።
የትንሺቱ ሥልታዊ ምድር ሕዝብ ግዛቲቱ ከሩሲያ ጋር ዳግም እንድትዋሐድ በድምፁ ወሰነ።ሲምፌሮፖል-ትናንት።«ወደ ሩሲያ እንኳን ደሕና መጣሽ።»እስከ ትናንት ከክሪሚያ ትናንሽ ጠላቶቻቸዉ ይልቅ-የሞስኮ ጠንካሮችን ሲያወግዙ ሲወነጅሉ የከረሙት የኪየቭ አዲስ መሪዎች ትናንት እኒያን የትንሽ ግዛታቸዉን መሪዎች አስታወሱ፤ ወነጀሉ፤ ሊቀጡ- ሊያስቀጡ ዛቱም።ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር አርሴኒ ያዜንዩክ።
«የዩክሬን መንግሥት እኒያን በሩሲያ ወታደሮች የተከለሉትን የዩክሬንን ነፃነት ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ የመገንጠልና የመከፋፈል ቀለበት መሪዎችን እንደሚይዛቸዉ ምንም ጥርጥር የለዉም።ዓ,መት፤ ሁለት ዓመት ይወስድ
ይሆናል ግን ሁሉንም እናገኛቸዋለን።ለፍርድ እናቀርባቸዋለን።በዩሬንና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንከሳቸዋለን።የቆሙባት ምድር ታጋያቸዋለች።»
የያዜንዩኒክን-ዉንጀላ፤ ጠላቶቻቸዉን የማጥፋት መቅጣት ማስቀጣት ቃል-ዕቅድን ገቢራዊነት ለማየት-መስማት ሲያንስ አንድ ሲበዛ ሁለት ዓመት መጠበቅ ይኖርብናል።ጊዚያዊ ጥቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት የሩሲያ ጦር በሳቸዉ አገላለጥ ለክሪሚያ «ገንጣይና ከፋፋዮች» ከለላ መስጠቱ እዉነት ነዉ።የዚያኑ ያክል ያዜንዩክና ጓዶቻቸዉ በዩናይትድ ስቴስና በተባባሪዎችዋ እቅፍ ዉስጥ መሆናቸዉም ሐቅ።
USS ትራክስተን የተሰኘችዉ የዩናይትድ ስቴትስ ሚሳዬል ደምሳሽ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ጥቁር ባሕር ደቡባዊ ጠረፍ መሕለቋን ከጣለች-ትናንት አስረኛ ቀኗ።መርከቢቱ የጫነችዉ ሰወስት መቶ ባሕር ወለድ ጦር ከሩሜንያና ከቡልጋሪያ ባሕር ኃይል ባልደረቦቹ ጋር የሚያደርገዉን የዉጊያ ልምምድም ትናት አገባደደ።
ከጥቁር ባሕር በስተሰሜን ክሪሚያ ጠረፍ የሰፈረዉ የሩሲያ
ጦርም ልክ እንደአሜሪካኖቹ ሁሉ በምድር በባሕር ዉጊያ ልምምድ ተጠምዶ ነዉ የሰነበተዉ።ከጥቁር ባሕር ሰሜንና ደቡብ
የተፋጠጡት የሁለቱ ኃያልን ፈርጣማ ወታደሮች ባሕር ምድሩን በልምድ ተኩስ ሲያተረማሱት ሰማዩ የተረጋጋ መስሎ
ነበር።ብዙ ግን አልቆየም።
ዩናይትድ ስቴትስ ያዘመተቻቸዉ አስራ-ሁለት F-16 ዘመናይ ተዋጊ ጄቶች ከሪሚያ ልሳነ ምድርን ወደ ደቡብ ትተዉ የስማዩን ሠላም
እያደፈረሱ ፖላድ አላማዉ ፤ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ ክሪሚያ የሰፈረዉን የሩሲያ ጦር ከደቡብ በባሕር ሐይል ከሰሜን
በአየር ሐይል አጣብቆ ሞሶኮዎች በጀመሩት እንዳይቀጥሉ ለማስፈራራት ነበር።ግን ቢያንስ ለጊዜዉ አልሆነም።
የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አዉሮፕላኖች ፖላንድ ሲሰፍሩ
ሩሲያ ዘመናይ የጦር አዉሮፕላኖችዋን ፖላንድ ምሥራቃዊ ጥግ ቤሎ ሩስ ዉስጥ አሰፈረች።ቆጵሮስ አጠገብ መሕልቋን
የጣለችዉ የሩሲያ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ የተሸከመቻቸዉ ዘመናይ የጦር አዉሮፕላኖችም በሜድትራኒያን ባሕር ሰማይ
ላይ በአየር ላየር ዉጊያ ስልት «ይደንሱ» ገቡ።
የፖለቲካና የወታደራዊዉ ጉዳይ ታዛቢዎች የጦር ዘመቻ-ዝግጅቱ ጡንቻን ከማሳየት ባለፍ ወደ ዉጊያ ይቀየራል የሚል ሥጋት የላቸዉም።ተራዉ ሰዉ ግን ዩናትድ ስቴትስ የሚኖሩት ዩክሬንያዊት ወይዘሮ እንደሚሉት መስጋቱ አልአረም።
«ሥጋቱ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይኖር ነዉ።» የዩክሬኑ ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ያዜንዩክ የአሜሪካኖችን ቱፍታ-ምርቃት ለመቀበል ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት ወታደራዊዉ ፍጥጫዉ በጋመበት፤ ተራዉን ሰዉ ባሰጋበት መሐል ነበር።ባለፈዉ ሳምንት ሮብ። ራሳቸዉም ጓዶቻቸዉም የኪየቭን ቤተ-መንግሥት የተቆጣጠሩት በአደባባይ ሰልፍ-ግጭት፤ ሩሲያና ተባባሪዎቻቿ እንደሚሉት ደግሞ በ«ሕገ-ወጥ» መንገድ ቢሆንም ዋይት ሐዉስም፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትም የሐገር መሪነት ሙሉ ክብርና ማዕረግ አላጓደሉባቸዉም።
ዲፕሎማሲያዊ አሰጥ አገባ ኒዮርክ ሆነዉ ሐገራቸዉ ጥግ የሰፈረዉን ጦር ቃታ ሊያሰብ ወደሚችል ዛቻ አናሩት።«ጦርነት ትፈልጋላችሁ-ብለዉ ጠየቁ ሩሲያዎችን»-ጦርነት እፈልጋለሁ ብሎ-የሚዋጋ ያለ ይመስል።
«ለሩሲያ ፌደሬሽን ልናገር።ጦርነት ትፈልጋላችሁ።እንደ ዩክሬን ጠቅላይ ሚንስትር ጦርነት የምትፈልጉ አይመስለኝም።»
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን መመለስ ያለባቸዉን የዚያኑ ዕለት ለያዜንዩክ መልሰዉላቸዋል።«ጦርነት አንፈልግም።» ብለዉ።ጦርነት የለም፤እፈልጋለሁ የሚልም አይኖርም-የለምም።የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባለፈዉ አርብ ለንደን ዉስጥ ያደረጉት ዉይይትም ጦርነትን ሳይሆን-ፍጥጫዉን ለማስቀረት ከሆነ ደግሞ የክሪሚያን ሕዝበ ዉሳኔ ለማሰረዝ ወይም ለማዘግየት ነበር።
በማዕቀብ ቅጣት፤ ዛቻ ፉከራ የታጀበዉ ዉይይት ከዉይይቱ
በፊት ብዙዎች እንደጠበቁት ያመጣዉ ዉጤት የለም።ዉግዘት ዛቻዉ፤ ዲፖሎማሲያዊ ፍትግዉ አልተቋረጠም።የክሪሚያ መሪዎች
ከሕዝበ ዉሳኔዉ በፊት የሩሲያን ባንዲራ ሲምፌሮድ አደባባይ ሠቅለዉ ሕዝባቸዉ የሚሹትን እንዲያደረግ ሲያግባቡ-ዩናይትድ ስቴትስ ከሕዝበ ዉሳኔዉ በፊት የመጨረሻ ዲፕሎማሲያዊ ጥይቷን ከኒዮርክ ተከሶች።
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የክሪያሚያ ህዝበ ዉሳኔን አለያም በዉሳኔዉ መሠረት ግዛቲቱ ከሩሲያ መቀላቀሏን እንዲያወግዝ ዩናትድስቴት ለምክር ቤቱ ረቂቅ-የዉሳኔ ሐሳብ አቀረበች።አደተጠበቀዉ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላት ሩሲያ ረቂቁን ዉድቅ አደረገችዉ።ቻይና ድምጿን አቀበች።
የዩናይትድ ስቴትሷ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር ግን እንደ ገና ሩሲያን አወገዙ ዛቱም። «ሩሲያ
ሕገወጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቷን ለመደገፍ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኗን ተጠቅማለች።ልክ የዛሬ ሰባ ዓመት
ወረራን በመቃወም በተዋጉ ሐገራት ላይ የተሰጠዉ አይነት ድምፅን በድምፅ የመሻር ዉሳኔ ነዉ።ያም ሆኖ ሩሲያ ይሕን
በማድረግና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጣስ የሚደርሰዉን አፀፋ መቋቋምም ሆነ የወደፊቱን እዉነትኛ ጉዞ መቀልበስ
አትችልም።የክሪሚያን ይዞታም መለወጥ አትችልም።ክሪሚያ ዛሬ የዩክሬን አካል ናት።ነገም የዩክሬን አካል
ናት።በሚቀጥለዉ ሳምንትም የዩክሬን አካል ናት።ወደፊትም የዩክሬንና የዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደዉ መሠረት ይዞታዋ
እስካልተቀየረ ድረስ የዩክሬን አካል እንደሆነች ትኖራለች።»
የዛሬ ሰባ ዓመት።ሶቭት ሕብረትን በመቃወም ያንገራገሩ
የምሥራቅ አዉሮፓ ሀገራት ፖለቲከኞችን ጥያቄ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንዲደግፍ ምዕራባዉያን ሐገራት ያቀረቡትን
ረቂቅ ሶቬት ሕብረት ዉድቅ አድራጋዉ ነበር።
ከሰባ ዓመት በፊት ግን የያኔዉ የሶቬት ሕብረት ገዢ ጆሴፍ ስታሊን ክሪሚያ ዉስጥ አብላጫ ቁጥር የነበራቸዉን ታታሮችን እያጋዙ ሳይቤሪያ በረዶ ላይ ሲጥሏቸዉ ለሰብአዊ-መብት፤ ለሕዝብ ነጻነት እንቆረቆራለን የሚሉት የአዉሮጳ-አሜሪካ መሪዎች ከቁብ አልቆጠሩትም ነበር።
አምባሳደር ፖውር የዛሬ ሰባ ዓመቱን ታሪክ ባስታወሱበት ንግግራቸዉ ነገ-ባሉት
ትናንት ድምፁን የሰጠዉ የክሪሚያ ሕዝብ ግዛቲቱ ከሩሲያ ጋር እንድትዋሐድ ወስኗል።በከዘጠና ስድስት ከምቶ
ድምፅ።የሕዝበ ዉሳኔዉ አስተባባሪዎች እንዳሉት ድምፅ መስጠት ከሚችለዉ ሕዝብ ከሰማንያ ከሰወስት የሚብልጠዉ ድምፁን
ስጥቷል።እሳቸዉ አንዱ ናቸዉ።
«ሕይወቴን በሙሉ የምመኘዉን ደግፌ ነዉ ድምፄን የሰጠሁት።ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ነፃ መሆን እንፈልጋለን።አሁን የተሳካልን ይመስለኛል።አሁን እዚሕ የሆነዉና የምናየዉ የምንፈልገዉ ነዉ።»
ስታሊን ከክሪሚያ ካጋዙዋቸዉ በሕዋላ የግዛቲቱ አናሳ ነዋሪዎች የሆኑት ታታሮች ግዛታቸዉ ባያት-አባቶቸቸዉ ላይ ግፍ በፈፀመችባቸዉ ሞስኮ ስር መተዳደሯን አልተቀበሉትም።የድምፅ መስጪያዉ ካርድ ግዛቱቱ ከሩሲያ ጋር ትዋሐድ ከሚለዉ ሌላ ያለዉ አማራጭ የ1992 (ዩክሬን ከሶቬት ሕብረት የተገነጠለችበት) ሁኔታ እነደነበረ እንዲቀጥል ትፈልጋለሕ የሚል ነዉ ያለዉ።እሳቸዉ ታታር ናቸዉ። ግዛቱቲ ከዩክሬን ጋር መቆየቷን ቢደግፉም ሁለተኛዉ አማራጭ አልገባቸዉም።
«በድምፅ መስጫዉ ካርድ ያለዉን ሁለተኛ ጥያቄ ከመመለስ በስተቀር ሌላ ምርጫ የለኝም።ክሪሚያ የዩክሬን አካል እንደሆነች ትቀጥል የሚል ምርጫ የለም።በዚሕም ምክንያት ይሕን ሕዝብ-ዉሳኔ አላዉቅም።ሌሎቹ የክሪሚያ ታታሮችም እንደኔዉ ናቸዉ።»
አብዛኛዉ ሕዝብ ግን ወስነ።ሴትዮዋ እንዳሉት ተደሰተም። «ተስፋ
እንዳደረግ ነዉ የሩሲያ አካል በመሆናችን በጣም ደስ ብሎናል።ይሕ በመሆኑ ከመጥፎ ታሪክ እንወጣለን።እዚሕ ለበርካታ
አመታት ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም።አሁን ግን ወደ ጥሩዉ አቅጣጫ መራመድ ጀምረናል።ዛሬ በሕይወታችን
በጣም አስደሳቹ ቀን ነዉ።»
ሲምፌሮፖል-ሥትቦርቅ የምዕራባዉያን የቅጣት ዱላ ተሰነዘረ።ብራስልስ። የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሃያ-አንድ የሩሲያ፤ የዩክሬንና የክሪሚያ ተባባሪዎችዋ ባለሥልጣናት ላይ የጉዞና ገንዘብ የማንቀሳቀስ ማዕቀብ ጣሉ።ዛሬ።ዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም በአስራ-አንድ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አዘዋል።
ደግሞ በዚያ ላይ ምዕራባዉያን ሐገራት ከሩሲያ ጋር አሁንም ድርድር ይላሉ።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ካትሪን አሽተን ቀዳሚዋ ናቸዉ።
«ሁል ጊዜ እንዳደረግሁት ሁሉ፤ ሩሲያ ከዩክሬን መሪዎች ጋር እንድትደራ,ደር፤
ከዓለም ከቀፉ ማሕበረሰብ ጋር መወያየቷን እንድትቀጥል፤ ሁኔታዉን ለማብረድ ፖፐቲካዊ መፍትሔ እንድትከተል
እጠይቃለሁ።በመጨረሻ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር መልካም ግንኙነት መመሥረት ትፈልጋለች።የአዉሮጳ ሕብረት፤ ሌላዉ ዓለምም
እንደዚሁ።»
የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይንማየር ግን-ሩሲያ ያሻትን ስታደርግ አርፈን አንቀመጥም አሉ።
«ፍጥጫዉን አልፈለግነዉም።እንዲያዉም በተቃራኒዉ ከዚሕ ቀዉስና አስጊ ሁኔታ የምንወጣበትን ሁኔታ ላለፉት ተከታታይ ቀናት ሥናፈላልግ ነበር።ያቀረብናቸዉ ሐሳቦች ሰሚ አላገኙም።ሥለዚሕ አሁን እዚሕ (ብራስልስ) የምንገኘዉ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ሐሳብ ለመለዋወጥ ሳይሆን በግልፅ እንደሚታወቀዉ ምላሽ ለስጠት ነዉ።»
ምላሹ? ማዕቀብ።ዋሽግተኖችም፤ብራስልሶችም
የጣሉት ማዕቀብ ግን ክሪሚያ ከሩሲያ እንድትቀየጥ በግንባር ቀደምትነት ያስወሰኑትን ወይም ፍጥጫዉን በበላይነት
የሚዘዉሩትን ቭላድሚር ፑቲንና ከፍተኛ ሹማምንቶቻቸዉን አይነካም።ድንቅ-ነዉ።የሩሲያ አፃፋ ምን-ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ለዛሬ ይብቃን።
Source: www.dw.de
No comments:
Post a Comment