ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ተመራማሪ
ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ የተወለዱት አስመራ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አስመራ፣ የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በጅማ ነው የተከታተሉት፡፡
ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ የተወለዱት አስመራ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አስመራ፣ የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በጅማ ነው የተከታተሉት፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል፡፡ ለሁለት ዓመታት ከሠሩ በኋላ ስኮላርሺፕ
አግኝተው እንግሊዝ ከሄዱ በኋላ ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ያጠኑት ታሪክ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና
ተገቢነትን በተለያዩ ጥናቶቻቸው ለሃያ ሦስት ዓመታት ተመልክተዋል፡፡ “Crisis of Ethiopian
Education፡ Implications for nation Building, Rethinking Ethiopian
Education, Ethiopian Education from Crisis to Collapse” በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትም
አሳትመዋል፡፡ የመጀመሪያውና እ.ኤ.አ. በ1990 በሲዳ ስዊድን ድጋፍ የታተመው መጽሐፋቸው ጥሩ ተቀባይነትን
በማግኘቱቶ የመጽሐፉ አምስት መቶ ቅጂዎች አዲስ አበባ ገብተው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ተከስተ በአሁኑ ወቅትም ሆነ
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን በሚመለከት ጥናት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ መጽሐፉ
እ.ኤ.አ. በ2016 ለሕዝብ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ
ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ አምስት ሴቶች ላይ የሚያተኩር የታሪክ መጽሐፍም እያዘጋጁ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ
የትምህርት ጥራት፣ በተለይም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርት ጥራት ችግሮችን በተመለከተ ከምሕረት አስቻለው ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የትምህርት ጥራት በአገሪቱ የተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች እንዴት ይነፃፀራል?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- በደርግ ሥርዓት የኢትዮጵያ ትምህርት ምንም
ዓይነት ፖሊሲ አልነበረውም፡፡ የትምህርት ፖሊሲው የፖለቲካ አይዲዮሎጂው ስለነበር የትምህርት ሥርዓቱ የተዳከመ
ነበር፡፡ በጃንሆይ ዘመን የተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ የተሻለ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ
የትምህርት ፖሊሲ ቢኖርም አጠቃላይ የፖሊሲው ትኩረት ብዛትና ቁጥር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የትምህርት ጥራትና
አግባብነት ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የአገሪቱን
የትምህርት ሥርዓት እየተመለከትኩት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህር ጥራት ችግር መታየት የጀመረው መቼ ነበር?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት መዳከም የጀመረው
ደርግ ሥልጣን ላይ መውጣቱን ተከትሎ የውጭ አገር ዜጐች የሆኑ መምህራን ዩኒቨርሲቲ ለቀው መሄድ ሲጀምሩ ነው፡፡
የደርግ የትምህርት ሲስተሙን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መሞከሩ ጥሩ የነበረ ቢሆንም፣ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን መምህራን
በእንግሊዝኛ የማስተማር ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ይህ በሁለተኛ ደረጃም የነበረ ችግር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ
ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ሁኔታቸው እንደ ዩኒቨርሲቲ ያገለግላሉ ወይ? የሚል ጥያቄን አስነሳ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1980
ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መድከም ጀምረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው
የነበረው የሰው ኃይል ፖለቲካው ስላልጣመው ከዩኒቨርሲቲው ሄደ፡፡ ኢሕአዴግ ፈልጐም ሳይፈልግም በከፍተኛ የትምህርት
ተቋማት ባዶ ቦታዎችን ነው የተረከበው፡፡ ይህ በትምህርት ላይ ትልቅ አንድምታ አለው፡፡ ይህ መንግሥት ከዩኒቨርሲቲ
ጋር የነበረውን ቅራኔ በተግባር ማሳየት ጀመረ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የጃንሆይ ሥርዓት መሠረትና የደርግ ቤት ነው በሚል
ዩኒቨርሲቲውን (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሚገባ አልያዘውም ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም. 43 የዩኒቨርሲቲው ምሁራን
መልቀቃቸውም ይታወሳል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማርን መሠረት ያፈረሱ ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ ያሳደሩ እውነታዎች ምን ነበሩ?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- እ.ኤ.አ. በ2000 በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት
ወሳኝ ጊዜ ነበር፡፡ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መምጣት ነበር፡፡ ትምህርትን በሚመለከት ዋናው ዓላማ መሀይምነትን
ማጥፋት ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ለማስፋፋት ከሞከራችሁ የፍራንክ እጥረት የለም ተባለ፣ መስፋፋቱም
ተጀመረ፡፡ ቅድሚያ ትኩረት ለመስፋፋት ሆነ፡፡ ጥራት አስፈላጊ ሆኖ አልታየም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት
ጥራት ጉዳይ ሲነሳ የመንግሥት መልስ ከብዛት ጥራት ይመጣል፣ ከገባህ ይግባህ ካልገባህ ያንተ ችግር ነው የሚል
ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ትሆናለች በሚል በአንድ ጊዜ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፈቱ፡፡ አሁን
በአገሪቱ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከሰላሳ በላይ ሲሆኑ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት የተፈጠሩና ዕርምጃውም የሰው ኃይልን
ያላገናዘበ ነበር፡፡ እንኳን እንዲህ ብዛት ያለው ዩኒቨርሲቲን የሚያንቀሳቅስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንኳ
በሚገባ እንዲሠራ የሚያደርግ የሰው ኃይል ግን የለም፡፡ የዚህ መስፋፋት ጥቅም የቱ ላይ ነው? ምን ሊረዳ? ምን
ሊያግዝ? ጥራት፣ ተገቢነትና ምርምር ቦታ ከሌላቸው መስፋፋት ምን ማለት ነው? እንኳን አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲም የዩኒቨርሲቲ ገጽታና ዩኒቨርሲቲ ሊያስብለው የሚችል ነገር የለውም፡፡ አንድን ዩኒቨርሲቲ
ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገው አንዱ ምርምር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የማውቀው ከትምህርቴ አንፃር ነው፡፡ እኔ የሶሻል
ሳይንስ ሰው ነኝ፡፡ የታሪክና የትምህርት ፋኩልቲዎችን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ የታሪክ ዲፓርትመንትን
ብንወስድ በተለያዩ ምክንያቶች ራሱን ችሎ አልቆመም፡፡ እንደዚህ ራሱን ችሎ ያልቆመ ዲፓርትመንት የአካዳሚክ ነፃነት
ጥያቄ ይነካዋል ወይ? ቢባል ሊነካው አይችልም ነው መልሱ፡፡ የአካዳሚክ ነፃነት አለመኖር ማለት ለምሳሌ የታሪክ
ዲፓርትመንት አንድ ጥያቄ አንስቶ ጥናቱን ሲያደርግ እንዳይቀጥል ወይም እንዲያቋርጥ ሲገደድ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ
ደረጃ ላይም አልተደረሰም፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉበት ደረጃ የአካዳሚክ ነፃነት ወሬ ብቻ ሳይሆን
ውኃ የማያነሳ ጥያቄም ነው፡፡ መቼ ሥራው ተሠርቶ ነው የአካዳሚክ ነፃነት አለ የለም የሚባለው? ምን ዓይነት ሥራ
ተሠርቶ? ሊሠራስ ታስቦ ነው የአካዳሚክ ነፃነት ጥያቄ የሚነሳው? ይህ በተለይ የታሪክ ዲፓርትመንት ይመለከታል?
ሪፖርተር፡- የትምህርት ዲፓርትመንትስ?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- ለጥናቴ ‹‹ጆርናል ኦፍ ኢትዮጵያን ኤዱኬሽን››
የሚለውንና በትምህርት ጥራትና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚዘጋጀውን የረዥም ዓመታት ሕትመቶች አይቼ ነበር፡፡ በጣም
ደካማ ጥናት ነው፡፡ አንድ ሰው የአርባ ዓመት ሕትመት አይቶ በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ያሉ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው
የሚለውን መመለስ አይችልም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ የአካዳሚክ ነፃነት ሊነሳ የሚችል ጥያቄ
አይደለም፡፡ ከዚህ ጥያቄ ይልቅ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሥራውን ለመሥራት አመቺ ሁኔታ አለው ወይ? ምርምር
ለማድረግ አካባቢው ይፈቅዳል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መሠረት አላቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዋቅር ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ነው?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- የማስተማር፣ የመመራመርና የሕዝብ አገልግሎት ሚና
አለን ብለን እናምናለን፡፡ ማስተማርና ምርምር የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ፣ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ አስተማሪ ማስተማርና
መመራመር ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ይችላል ብቻም ሳይሆን ምርምር ለማድረግ ሁኔታዎች
ይፈቅዱለታል ወይ? እንደ እኔ እምነት አስተማሪ ሥራውን በደንብ ሊያከናውን አይችልም፡፡ ያለው የማስተማር ጫናና
የሚከፈለው ደመወዝ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ጥናት ከማስተማር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁር ምርምር ማድረግ
ካቆመ ቆይቷል፡፡ በአገራችን ባለፉት ሃያ ዓመታት የሚሠሩ ጥናቶች ሁሉ በለጋሾች ስፖንሰር የተደረጉ ናቸው፡፡
አንዳንድ ጥናቶች ለጋሾችን መሠረት ያደረጉ፣ የአጭር ጊዜ ጥናትም ብቻ ሳይሆኑ የ‹‹ኮንሰልተንሲ›› ሪፖርቶችም
ናቸው፡፡ ጥናት እየተባለ ያለውና የምናስተምረው የጥናት ዲዛይንም ይኼው ነው፡፡ ጥናት ምን ማለት ነው? የሚለውን
መመለስ በሚያስቸግር ሁኔታ ጥናት ትርጉሙን እያጣ ነው፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ
በቂ ደመወዝና ተቋማዊ ድጋፍም ያስፈልጋል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እየታየ ያለው ከአሥራ አምስት ዓመታት
በፊት በታንዛኒያም ታይቷል፡፡ ነገሩ እንደማያስኬድ ተረድተው የመምህራንን ደመወዝ አስተካክለዋል፡፡ ታንዛኒያ ዛሬ
ለፕሮፌሰሮቿ አንድ ሺሕ ዶላር መክፈል ችላለች፡፡ አስተማሪን እንደሚገባህ ሥራ ማለት የሚቻለው የሚገባው ሲከፈለው
ነው፡፡ ጥናትና የመንግሥት ሠራተኛ፣ ጥናትና የግል ኩባንያ የት ይገናኛሉ? በኢትዮጵያ የሚታየው የዩኒቨርሲቲ ዓለምና
የመንግሥት ዓለም የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡ የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት ድልድይ አልተሠራም፡፡ ያለን ሳይንስና
ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እንጂ ድልድይ መሆን የሚችል ‹‹ሪሰርች ካውንስል›› አይደለም፡፡ ካውንስሉ ማጥናት የሚችሉ እነማን
ናቸው? እንዲያጠኑስ ምን ያስፈልጋቸዋል? ጥናቱን ካደረጉ በኋላ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር እንዴት
ይገናኛሉና የመሳሰሉ ነገሮችን የሚያይና የሚያመቻች ነው፡፡ የዚህ መንግሥት ሚስጥርና ጉዳዩ ግን የሚገባ አይደለም፡፡
በአንድ በኩል ለምርምር ይኼን ያህል አቀርባለሁ ይላል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንኳ ለዚህ ጥናት
ሲባል የሚገኝ ነገር የለም፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ምንድን ነው? እንዴት ነው የሚመሠረተው? እንዴት
ነው ወደፊት የሚራመደው? የሚለውን በሚገባ የተገነዘበ አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ለትምህርት ጥራት መውረድ የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀመጡ የአካዳሚክ ነፃነትና ተቋማዊ ነፃነት በተደጋጋሚ ይጠቀሳሉ፡፡
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- በተወሰነ መልኩ አስተያየቱን እጋራለሁ ነገር ግን
እዚህ ነገር ላይ ምርምር አደርጋለሁ ተብሎ ክልከላ የሚደረግበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ መጀመሪያ መቼ ምርምር
ማድረግ ተደፈረ? ማን የማይነካ የሚባለውን ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት ሞከረና? የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት
ጥራትን የጐዳ ሌላ ነገር የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ ተማሪዎች ከሥር በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ መሆኑ አማርኛን ብቻም
ሳይሆን እንግሊዝኛንም ጐድቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲታይ አንድ አገር ነው አይደለም የሚለውን ጥያቄ
ያስነሳል፡፡ ግማሹ በትግርኛ ሌላው በኦሮሚኛ፣ ወዘተ ተምሮ ዩኒቨርሲቲ ይመጣል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ መግባቢያው
እንግሊዝኛ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የዚህ መንግሥት የመማሪያ ቋንቋ ፖሊሲ በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ
አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ትተን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንኳ በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛ
ማስተማር አይችልም፡፡ በእርግጥ የማስተማሪያ ቋንቋው እንግሊዝኛ ቢባልም አማርኛ ነው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም
እንግሊዝኛ ወድቆ እያለ ሁለተኛ ደረጃን በእንግሊዝኛ አስተምራለሁ የሚል መንግሥት ከእውነታው የራቀ ነው፡፡ የራሱ
ራዕይ ቢኖረውም ራዕዩ መሬት ላይ ካለው ነገር ጋር አይጣጣምም፡፡
ሪፖርተር፡- በአፄ ኃይለሥላሴም በደርግም የአካዳሚክ ነፃነት ጥያቄ ነበር፡፡ ይህ በተለያዩ ጥናቶችም ተቀምጧል፡፡ ዛሬም እንደ ችግር ይነሳል፡፡
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ነፃነት ጉዳይ
ችግር ፣፣፣አያውቀውም፣ አሁንም ችግር ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩትን 43 ምሁራን
ጉዳይ ብንመለከት የአካዳሚክ ነፃነት ጉዳይ አልነበረም፡፡ የተባረሩትን ብዙዎቹን አውቃቸዋለሁ፣ ነገሩ ከአካዳሚክ
ነፃነት ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡ ለእኔ የአካዳሚ ነፃነት ችግር ሆኖ አያውቅም፣ ችግር ነው የሚለኝን ላገኝ
እፈልጋለሁ፡፡ የአካዳሚክ ነፃነት ከፕሬስ ነፃነት ይለያል፡፡ ጋዜጠኛ በእያንዳንዷ ዕለት የሚጋፈጠው ነገር አለ፡፡
እዚህ ላይም ቢሆን የፕሬስ ነፃነት የሚጠይቀው ጋዜጠኛ ጐበዝ ነው አይደለም የሚለው ሊነሳ ይችላል፡፡ አንድ ምሁር
ይህ የአካዳሚክ ነፃነት ጉዳይ ነው ብሎ ይህንን ማንሳት አትችልም፣ እዚህ ላይ ምርምር አታደርግም የሚል ሥርዓት
በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም፡፡ የምናነሳቸው የብቃት ችግሮች ሁሉ እያሉ የትኛው ምሁር ወይም ተቋም ይህን መንግሥት
እየተጋፈጠው ነው? “Rethinking Ethiopian Education” በሚለው መጽሐፌ ወጣ ብዬ የመንግሥትን
የብሔር ፖሊሲ ተችቼ ነበር፡፡ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር ለነበሩት ወይዘሮ ገነት ዘውዴ መጽሐፉን ሰጥቼያቸው
ነበር፡፡ ይህ ያንተ የፖለቲካ አቋም ነው፣ እኛ ደግሞ የራሳችን አለን በሚል ነው የተለያየነው፡፡ ምን አገባህ?
ለምን እንዲህ አልክ? ተብዬ አላውቅም፡፡ ለምን እዚህ ላይ ጥናት አደረግህ? በጥናቱ ለምን እንዲህ አልክ? የሚል
ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ ለምን የአካዳሚክ ነፃነት ጉዳይ በተደጋጋሚ ይነሳል?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- እውነት ነው ይነሳል፡፡ ነገር ግን ደሞ ብዙ
ሰነፍ መምህራንም እኮ አሉ፡፡ ሥራ የማይሠራ ሰው ለምን አልሠራህም ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በእርግጥ እውነቱ
ምንድነው ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ለምርምር አካባቢው የተመቸ አይደለም፣ ሁኔታዎች አይፈቅዱም፡፡ ጥሩ ጥናት የሠራ ሰው
አይሸለምም፣ ዕውቅናም አይሰጠውም፡፡
ሪፖርተር፡- በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት መውረድ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች በደረጃ ይቀመጡ ቢባል?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- ዋናው ምክንያት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን
ወደፊት የማራመድ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ኃላፊነታቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች ተቋማቱን እንዴት
ወደፊት እንደሚያራምዱ አያውቁም፡፡ እንዴት የተወሳሰበ እንደሆነ ሳያውቁ ዝም ብለው የሚያሰፉት ሲስተም ችግር
ይፈጥራል እንጂ ችግር አይፈታም፡፡ ሁለተኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን እንዲጫወቱ በአግባቡ ገንዘብ
እያገኙ አለመሆኑ ነው፡፡ ተቋማቱን ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ የሚሆን ካውንስል አለመኖሩም ሌላ
ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹ሪሰርች ካውንስል›› የሌላት ብቸኛዋ አገር ስትሆን፣ ይህ ደግሞ ለምርምር የሚያነሳሳና
የሚያካሂድ አካልም የለም ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከመደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ መምህራንን የሚመድበውም መንግሥት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ችግር አይደለም?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- መንግሥታት ሁሌም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት
ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ለበጐ ከሆነ ይህ በራሱ ችግር የለውም፡፡ የአገሪቱን የዕድገት ፍላጐት መሠረት ያደረገ የተባለው
70/30ም በራሱ ችግር አይደለም፡፡ በተማሪ ማጣት ዛሬ የተዘጉ ዲፓርትመንቶች ነገ ይከፈታሉ፡፡ በእርግጥ ብዙ የግል
ተቋማት ስላሉ በእነሱ የሚካካስበትም መንገድ አለ፡፡ ትልቁ ችግር ይህ ሳይሆን መንግሥት ተቋማቱን በሚገባ ፋይናንስ
ሳያደርግና ሳያደራጅ ይህን ያህል አስተምሩልኝ ማለቱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት አቅም ኖሮት የመማር ማስተማር ቋንቋውን አማርኛ ማድረግ አለበት፡፡ ዕርምጃው ጊዜ የሚወስድ
ቢሆንም ያስኬዳል፡፡ በእርግጥ እኔ ስሟገት መሆን አለበት የምለው አማርኛና ኦሮሚኛን ነው፡፡ እንግሊዝኛ ደግሞ
እንደ አንድ ትምህርት ኮርስ በሚገባ ይጠናል፣ በሁሉም ደረጃ፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ጂኦግራፊ… በእንግሊዝኛ
ማስተማር አይቻልም፡፡ በእንግሊዝኛ ለማስተማር በእንግሊዝኛ ማሰብ መቻል ያስፈልጋል፡፡ ህንዶችን ጨምሮ ብዙዎች ይህን
እየተገበሩት ነው፡፡ በሁሉም ደረጃ በቋንቋችን መማር እስካልቻልን ድረስ ነገሮች አስቸጋሪ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡
ይህ ውሳኔ መቼ ይወሰናል? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ እንኳ የዩኒቨርሲቲውን ደካማነት ማየት ይቻላል፡፡ እኔ
በእዚህ ጉዳይ ላይ “ፐብሊክ ሌክቸር” ሰጥቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ሥርዓት ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት አዎንታዊ ገጽታ ይኖረዋል?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- መስፋቱ ጥሩ ነው ብዙ ሰዎችን ተጠቃሚ
ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ተጣምረው መሄድ ያለባቸው ነገሮች አይሄዱም፡፡ ጥራት ሳይታይ፣ የመማር ማስተማር ሒደት
ሳይታይ ቢሰፋ ያ የተፈጠረው አዎንታዊ ነገር ይበላሻል፡፡ ይህ መንግሥት “ሪስክ” ይወስዳል ግን በደንብ አያዳምጥም፣
እሱ የሚፈልገውን ብቻ ነው የሚያዳምጠው፡፡ የመንግሥት ዋና መገለጫ በውጭ አገር ኩባንያዎች ጥናት መመራት ነው፡፡
እንደ ዓለም ባንክ የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡ በአገሩ ምሁራን ላይ እምነት የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- ምሁሩ በአንድ ጎራ ተሠልፎ የመተቸት አዝማሚያ ብቻ ይታይበታል?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- መተቸት’ኮ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሌም
አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ መጠቆም አለበት፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የለም ወድቋል ብለን የምናምን
ከሆነ፣ እንዴት ከወደቀበት ማንሳት እንችላለን ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ አማራጭ የማይሰጥ ትችት ዋጋ የለውም፡፡
እንደሚመስለኝ ግን መንግሥት ትልቁን የወቀሳ ድርሻ የሚወስድ ይሆናል፡፡ በእጁ ላይ ያለውን ሀብት ማንቀሳቀስ
ይችላል፡፡ ያለውን የተማረ የሰው ኃይል ማቅረብና ማሠራት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩን ለመቅረፍ ጠቃሚ ነው የሚሉት ነገር ካለ?
ፕሮፌሰር ተከስተ፡- የጥናት ምክር ቤት መቋቋም አስፈላጊነት ትልቅ
ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ የቋንቋ ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚያስፈራ ነገር አይታየኝም፡፡ እንግሊዝኛ’ኮ በቀላሉ
የሚጠና ቋንቋ ነው፡፡ እንደ አንድ የትምህርት ኮርስ ይጠናል፡፡ ደግሞ መጠናትም አለበት፡፡ እንግሊዝኛን እንደ
መማርያ ቋንቋ አድርገን ስንጠቀምበት ነው ችግሩ፡፡ ለምንድን ነው የአገራችንን ታሪክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የምንማረው?
አንችለውም’ኮ፡፡ የአገራችንን ሁኔታ ተንትነን መፍትሔ አግኝተን መማር ያለብን በራሳችን ቋንቋ ነው፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment