-ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነካቢኔያቸው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ
የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማላበስ አዲስ እንቅስቃሴ ሊጀምር ነው፡፡
ከዚህ
ቀደም ግድቡን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው
እንቅስቃሴ ተገትቶ፣ አዲሱ ዘመቻ ፊቱን ወደ ጣሊያንና ኖርዌይ አዙሯል፡፡ ከዚያም ወደተለያዩ አገሮች ይቀጥላል፡፡
ባለፈው
ሳምንት የውኃ ሚኒስትሩ መሐመድ አብዱል ሙታሊብና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነቢል ፋህሚ ወደ ጣሊያን ጉዞ
አድርገዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ዋነኛ ሸሪክና የግድቡ ግንባታ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ባሉዋት
ጣሊያን የተደረገው ጉብኝት ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡
የጣሊያኑ
ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግድቡን ጥናትና ግንባታ የሚያካሂድ በመሆኑ፣ ጣሊያን የግብፆች የአዲሱ ዘመቻ ዓላማ
መሆኗ እየተነገረ ነው፡፡ የውኃ ሚኒስትሩ ሙታሊብ ለግብፅ ሚዲያዎች እንደገለጹት፣
የጣሊያን ጉብኝት ግቡን በመምታቱ
ወደ ሌሎች አገሮችም ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ምንም እንኳ የተገኘው ስኬት ምን እንደሆነ ባይብራራም፣ ሙታሊብ ለጣሊያን
መንግሥት ባለሥልጣናት በግድቡ ምክንያት ግብፅ ሊደርስባት የሚችለውን የውኃ ችግር ማስረዳታቸውን፣ የጣሊያን
ባሥልጣናትም ችግሩን አሁን ገና መስማታቸውን መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚቀጥለው ጉዞም ለህዳሴው ግድብ የገንዘብ
ድጋፍ ታደርጋለች ባሉዋት ኖርዌይ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኖርዌይ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ መቼና
የት እንደሰጠች ግን አላብራሩም፡፡ ግብፆች ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች መካከል አንዷ ኖርዌይ
ናት በማለት ሌሎችም አገሮች ዕርዳታ ይሰጣሉ የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት መሰንዘራቸው ተሰምቷል፡፡
የግብፅ
መንግሥት የሚቀጥለው ዕርምጃ በተለያዩ አገሮች የሚደረግ ጉዞ ሲሆን፣ በየአገሮቹም የግብፅን አቋም በሰፊው
ማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዚህ ጉዞ ዓላማ ለግብፅ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ማስገኘት መሆኑ ተወስቷል፡፡
ከእነዚህ ጉዞዎች ለግብፅ ድጋፍ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማሳጣትም ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ ግብፅን
አይጐዳም እያለች ባለችበት ወቅት፣ ግብፆች ግን ይህ ግድብ በግብፅ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠ ነው በማለት ለዓለም
አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ መዘጋጀታው ተሰምቷል፡፡
ለተመድና
ለአፍሪካ ኅብረት የሚቀርበው አቤቱታ ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ በኋላ የሚመሠረተው መንግሥት ተግባር እንዲሆን ወደጐን
ተገፍቶ፣ አሁን የተያዘው በተለይ በአውሮፓ አገሮች ውስጥ ሰፊ ዘመቻ መጀመር እንደሆነ ሾልከው የወጡ ሪፖርቶች
ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በግድቡ ላይ ጥያቄ
ለማስነሳት ሌላ ዘመቻ መታቀዱም ይሰማል፡፡ ሰሞኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋህሚ ነቢል በታንዛኒያ ጉብኝት
አድርገዋል፡፡ ጉብኝቱንም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዊቴ ማንም አገር ግድብ
ሲገነባ የተፋሰስ አገሮችን ማማከር አለበት ማለታቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የግብፅ
የውኃ ሚኒስትር ሙታሊብ መንግሥታቸው በርካታ አማራጮችን በመያዝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ
እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ስምምነት መድረሱን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በበርካታ አገሮች ግድቡ ግብፅን
እንዴት እንደሚጐዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡ የግብፅን ተለዋዋጭ አቋምና ዕረፍት የለሽ
እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ወገኖች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፀፋው ተዘጋጅቷል ወይ በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጐት መሟላት ወሳኝ መሆኑንና የግድቡን የጥራት
ደረጃ በሚገባ ማሳየት አለባት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እውነታውን ይዛ በግብፅ ፕሮፓጋንዳ መበለጥ የለባትም በማለት
ያስረዳሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐዚም አል ቤብላዊና የሚመሩት ካቢኔ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአገሪቱ ሊካሄድ የሁለት ወራት ዕድሜ ሲቀረው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንታዊው
ምርጫ እስኪከናወን ድረስ አገሪቱን እንዲያስተዳድር የተመረጠው የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርና
የሚመሩት ካቢኔ ባለፈው ሰኞ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ማስገባታቸውን የአገሪቱ
መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡበት ምክንያት
ምን እንደሆነ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡
ጠቅላይ
ሚኒስትሩ በአገሪቱ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ፣ እሳቸውና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ
ጥያቄያቸውን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሊ መንሱር እንዳስገቡ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያውን ለምን
እንዳስገቡ ባይገልጹም፣ ከካቢኔያቸው ጋር የ15 ደቂቃ ውይይት አድርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በግብፅ
መንግሥት ውስጥ ብቻ ለውጥ ማምጣት ትርጉም የለውም፡፡ የግብፅ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚመኘውን ለመሆን በራሱ መጣር
አለበት፤›› ሲሉ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ
ሚኒስትር አል ቤብላዊ፣ ‹‹ግብፅ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆነች ሁሉ ሊጨበጡ የሚገባቸው ትልልቅ
ዕድሎች እየተበላሹባት ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜው ለአገራችን ስንል መስዋዕትነት የምንከፍልበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሙያቸው
ኢኮኖሚስት የሆኑት ቤብላዊ የግብፅ ሕዝብ አገሬ ምን አደረገችልኝ ከማለት ባለፈ፣ ለአገሬ ምን አደረግኩ ብሎ
መጠየቅ እንዳለበት ገልጸው፣ የአጭር ደቂቃ መግለጫቸውን አጠናቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚመሩት ካቢኔ በአጠቃላይ
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ትችት ሲጐርፍባቸው ነበር በማለት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ይገልጻሉ፡፡
በበርካታ መገናኛ ብዙኃን ትችቶችም ሲወርዱባቸው ነበር፡፡
የሙስሊም
ወንድማማቾች ፓርቲን አሸባሪ ብሎ ለመፈረጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረጅም ጊዜ አጥፍተዋል፡፡ በቅርቡ በፀደቀው የደመወዝ
ስኬል የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች እንዳይካተቱ ማድረጋቸው፣ በአገሪቱ ውጥረትና የሽብር ጥቃቶች
እንዲንሰራፉ አድርገዋል በማለት ይተቿቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪና የጨርቃ ጨርቅ
ሠራተኞች፣ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የፖሊስ አባላት፣ የፖስታ ቤት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የሕክምና ዶክተሮች በተቃውሞ
ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ጠቅላይ
ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ያቀረቡትን መልቀቂያ የአገሪቱ ጊዜያዊ መንግሥት ተቀብሎት፣ በአል ቤብላዊ መንግሥት የቤቶች
ሚኒስትር ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ኢብራሂም መህሊብ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሾም ካቢኔያቸውን እንዲመሠርቱ ማክሰኞ
ዕለት ተነግሯቸዋል፡፡
የአገሪቱን
ትልቁን የኮንስትራክሽን ኩባንያ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበሩት መህሊብ፣ የአዲሱ ካቢኔያቸው አባላት
‹‹የቅዱስ ጦርነት ተዋጊዎች›› ይሆናሉ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፀጥታ በማስከበር ሽብርተኝነትን
እንዋጋለን፤›› ያሉት መህሊብ፣ ካቢኔያቸውን በሦስት ቀን ውስጥ እንደሚያዋቅሩ ገልጸዋል፡፡
በሆስኒ
ሙባረክ ዘመን የገዥው ፓርቲ (ናሽናል ዲሞክራቲክ ፓርቲ) አባል የነበሩት መህሊብ ካቢኔውን ሲመሠርቱ፣ አብዛኞቹን
ሚኒስትሮች በነበሩበት ቦታ ላይ ይመድባሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት
እንዳላቸው የሚታወቁት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በግብፅ እንደገና አመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment