Time in Ethiopia:

Feb 5, 2014

ግብፅ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ጀመረች

Geez Bet | Wednesday, February 05, 2014
-የግብፅ የልዑካን ቡድን በህዳሴው ግድብ ላይ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ሊነጋገር ነው
የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ በተመለከተ ሱዳን ለኢትዮጵያ የሰጠችውን ድጋፍ ለማጨናገፍ፣ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ መጀመርዋን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡
የተለያዩ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን እንደዘገቡት፣ የግብፅ መንግሥት የተለያዩ የመንግሥት አመራሮችና ፖለቲከኞች ከሱዳን መንግሥት አቻዎቻቸው ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምረዋል፡፡

ለአብነት ከተጠቀሱት መካከል የግብፅ አል ዋፍድ ፓርቲ ሊቀመንበር ሳይድ አል ባዳዊ በካይሮ ከሱዳን አምባሳደር ከማል ሐሰን ዓሊ ጋር በሁለቱ አገሮች ድንበር የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በዋነኝነት መክረዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ድንበር የጦር መሣሪያ ዝውውር ለማስቆም የተነጋገሩት ሁለቱ ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ
እየገነባችው ባለው የታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብና በሱዳን አቋም ላይ ተነጋግረዋል፡፡
ከውይይታቸው በኋላ አል ባዳዊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላት አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው መባሉ በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ተባራሪ ወሬ ነው ብለዋል፡፡ 
በግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች ጥልቅ ውይይት አካሂደው የሁሉንም ወገን ጥያቄዎች በሚመለስ ደረጃ መግባባት ይኖርባቸዋል የሚሉት አል ባዳዊ፣ ሱዳን የግብፅን የውኃ ፍላጐት በሚነካና ብሔራዊ ደኅንነቷን በሚጐዳ ጉዳይ ላይ አሉታዊ አቋም አትይዝም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ 
የሱዳን የመገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሰኞ ዘገባዎቻቸው የሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ወደ ካይሮ በማቅናት ከግብፅ አቻቸው ከፊልድ ማርሻል አብዱልፋታህ አል ሲሲ ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ወደ ግብፅ በዚህ ሳምንት እንደሚያመሩ የሱዳን ትሪቡን ዘገባ ያመለክታል፡፡ 
የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማቆም እንደሚገባት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ከፈለገች መጠኑ አነስተኛ መሆን ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡ እንደሳቸው አባባል የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከታቀደው ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማለት አለበት፡፡ በዚህ ስሌት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ወደ 1,800 ሜጋ ዋት መውረድ አለበት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ 45 አባላትን የያዘ የግብፅ የዲፕሎማሲ ቡድን ከጥር 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ተቃውሞ ለአፍሪካ ኅብረት እንደሚያሳውቅና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትንም እንደሚያነጋግር ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያን የሚጐበኘው የልዑካን ቡድን በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ኃላፊ አምባሳደር ዓሊ ኣል ሃዲዴ የሚመራ መሆኑን በኢትዮጵያ የግብፅ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊና ከኅብረቱ የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ጋር እንደሚመክር የተያዘው ፕሮግራም ያስረዳል፡፡ 
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ ከዓባይ ተፋሰስ ዳይሬክቶሬትና ከሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ኃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገር ታውቋል፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመገናኘት በህዳሴው ግድብ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቅርቡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የወገነችው ለራሷ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በአጋጣሚ ለድርድር በካርቱም በቆዩባቸው ጊዜያት በተለያዩ መስጊዶች ውስጥ ሳይቀር የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሱዳንን እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል ሲሰበክ በግርምት መታዘባቸውን በመግለጽ፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጐን ለራሷ ጥቅም ስትል መቆሟን መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ውይይትም ሆነ ድርድር ሱዳን የግብፅን ጥቅም የሚፃረር አቋም እንድትይዝ አለመፈለጋቸው ቢነገርም፣ ሱዳን እስካሁን የግድቡን ግንባታ እንደምትደግፍ ነው የሚታወቀው፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን ለመሰለፍ የቻለችው በሦስቱ አገሮች ተወክሎ ሲሠራ የነበረውና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተው የኤክስፐርቶች ፓነል ሪፖርት ድምዳሜን አገናዝባ ነው፡፡ በሪፖርቱ ግድቡ በሱዳንም ሆነ በግብፅ ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንደማያደርስ ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የግብፅ ባለሥልጣን የሱዳን አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ወግኗል መባሉን ተባራሪ ወሬ ነው ቢሉም፣ የሱዳን ባለሥልጣናት በአደባባይ ድጋፋቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ 
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment