Time in Ethiopia:

Jan 21, 2014

ያሳከከው ፓርላማ ጥርስም ያውጣ

Geez Bet | Tuesday, January 21, 2014
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 55 ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ይዘረዝራል፡፡
በዚህም መሠረት የበላይ ሕግ አውጪ የሆነው ይህ ምክር ቤት የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣
የማኅበራዊ፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ያፀድቃል፡፡ የአገሪቱን ገንዘብ፣ የብሔራዊ ባንክ አስተዳደር፣ የውጭ ምንዛሪንና ልውውጥን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ከማውጣት ባለፈ የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲን ያፀድቃል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ሕጎችን ከማውጣትም ባለፈ የፌዴራል መንግሥት፣ የአገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን ይወስናል፡፡ ብቻ በአጭሩ የአገሪቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነው፡፡ 
እንግዲህ ይህ ወሳኝ አካል የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ በርካታ ሕጎች የሚወጡበት ነው፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ከዚህ አካል ብዙ ትጠብቃለች፡፡ ስለዚህ የሁሉም ዓይኖች እዚህ አካል ላይ ያተኩራሉ፡፡ 
ከጥቂት ወራት በፊት ፓርላማው ‹‹ጥርስ ባያወጣም እያሳከከው ይመስላል›› ብለን ነበር፡፡ በእርግጥ በፓርላማው ለየት ያሉ አዎንታዊ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ይህንን የምንለው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለፓርላማው ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት እንደ ቀድሞው ያለጥያቄ በጭብጨባና በድጋፍ ከማፅደቅ ይልቅ፣ ሪፖርቶች ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ሲቀርብባቸው መመልከት በመለመዱ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ችግሮች በግልጽ እንዲታዩና ተገቢው ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ተደርገዋል፡፡ ለአንዳንዶቹም የመፍትሔ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ 
ከዚህ በፊት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣናት የሚቀርቡ ሪፖርቶች ጥርስ ስለሌላቸው የማይናከሱ ነበሩ፡፡ ቢናከሱም እንኳን ጥርስ ስለሌላቸው የማያሳምሙና ሀቁን የማያወጡ በመሆናቸው እውነታን የሚያድበሰብሱ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ማለት ባይቻልም በከፊል እንደዚህ ዓይነት ሪፖርቶች ለፓርላማው ሲቀርቡ በዝምታ አይታለፉም፡፡ ምንም እንኳን ውይይትና ክርክር እንዲሁም ተቃውሞ የሚገጥማቸው በርካታ ሪፖርቶች በስተመጨረሻ ቢፀድቁም፣ ፓርላማው እንደ ቀድሞው በዝምታ ከማፅደቅ አንድ ዕርምጃ መራመድ ችሏል፡፡ ለዚህም ነው ፓርላማው ጥርስ ባያወጣም እያሳከከው ነው ያልነው፡፡ ይህ ግን የመጨረሻው ሊሆን አይገባም፡፡ ያሳከከው ድድ ጥርስ ማውጣቱ እንደማይቀር ሁሉ፣ የአገሪቱ ፓርላማም ከማሳከክ ወደ ጥርስ ማውጣት መሸጋገር አለበት፡፡ ለዚህም ነው ያኔ ወደ ጥርስ ማውጣት ያሸጋግራችሁ ብለን የመረቅነው፡፡ 
ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የፓርላማውን ከ99 በመቶ በላይ መቀመጫ እንደ መቆጣጠሩ መጠን፣ የድርጅቱ የፓርላማ ተወካዮች የብቃትና የትምህርት ሁኔታ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ያቀረባቸው የፓርላማ አባላት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪና ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃት ያላቸው እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ፓርላማው ወሳኝና አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሕጐችና ፖሊሲዎች ላይ ውይይትና ክርክር ሲያደርግ አልፎ አልፎ የሚስተዋለው ነገር የፓርላማ አባላቱን ብቃት ጥያቄ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ፓርላማው ከፍተኛው የሕግ አውጪ አካል እንደመሆኑ መጠን የሚወጡት ሕጐችና ፖሊሲዎች በአባላቱ ችሎታና ብቃት ላይ የተመሠረቱ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የሚወጡት ሕጐችና ፖሊሲዎች ደግሞ በዕለት ተዕለት የሕዝቡ እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ፓርላማው ጥርስ ሊኖረው ይገባል የምንለው፡፡ 
ኢሕአዴግ ምንም እንኳን ከ99 በመቶ በላይ የሆነውን የፓርላማ መቀመጫ ቢይዝም፣ ለአምስት ዓመታት የተሰጠው ጊዜያዊ ኮንትራት መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ አሁን የተሰጠው ኮንትራት ሊጠናቀቅ የቀረው አንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ በቀጣዩ የ2007 ብሔራዊ ምርጫ ኢሕአዴግ ከባድ ፈተና ስለሚገጥመው ከአሁኑ በሚገባ የቤት ሥራውን ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ይህ ግን የሚመለከተው ኢሕአዴግን ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ምርጫ ሊወዳደሩ የሚያስቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ፓርላማው ጥርስ ሊያወጣ የሚችለው በትምህርትም ሆነ በብቃታቸው የላቁ አባላት ሲኖሩት ብቻ ነው፡፡ 
ፓርላማው እስካሁን ጥርስ ያለማውጣቱ ጉዳይ አጠያያቂ ቢሆንም፣ አሁን የሚታየው ጭላንጭል ግን ተዳፍኖ መቅረት የለበትም፡፡ ይልቁንም የበለጠ ብርሃን አብርቶ ሕዝቡን ሊያገለግል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በአሥርት ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ትንቅንቅ እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ ፖሊሲዎችንና ሕጐችን ከሚያወጣውና ከሚያፀድቀው ፓርላማ ብዙ ይጠበቃል፡፡ የአንበሳ ኢኮኖሚ ይኖረን ዘንድም የአንበሳ ጥርስ ያስፈልገናል፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ነገር የራሱ ሒደት ቢኖረውም፣ የፓርላማው ጥርስ የማውጣት ሒደት ዘግይቷል እንላለን፡፡ በመሆኑም ፓርላማው በማሳከክ ብቻ ሳይቆም ጥርስ ያውጣ፡፡ 
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment