የቀድሞዋ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ቅኝ ገዥ ፣ ፈረንሳይ፣ የእርስ በርስ መተላለቅ እንዳይከሠት ፣ የህዝብ
መፈናቀልም እንዳይደርስ ለመግታት ፣«ሳንጋሪስ» የተሰኘ ልዩ ግብረ ኃይል ከላከች አንድ ወር ቢሆንም ፣ አንዳች
ፋይዳ አለማስገኘቱን ራሷ
አመነች።ሰላም እስከባሪው ኃይል ቦንጊ ከገባ በኋላ ነው እንዲያውም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው፣ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ከቀየው የተፈናቀለው።
በኅዳር ወር ማለቂያ ገደማ ላይ ነበር፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍርንሷ ዖላንድ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ
ውሳኔ ላይ በመድረስ ነበረ፤ ወደ ቀድሞዋ ቅኝ ግዛት 1,200
ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የላኩት። እነዚህም
ነበሩ ቀደም ሲል በዚያ ሠፍረው የነበሩትን 400 ፈረንሳውያን ወታደሮችና 3,500 ውን የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም
አስከባሪ ኃይሎች ለማገዝ የተሠማሩት። ፈረንሳይ ዖላንድ በገቡት ቃል መሠረትና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው
ም/ቤትም ስምምነት ላይ በመድረሱ ነበረ ፣ በማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይከተል ለመግታት ጦር
ያዘመተችበትን እርምጃ የወሰደች።
ይሁን እንጂ ፤ በዓለም ዙሪያ በደል ለሚደርስባቸው ነባር ህዝቦች መብት የሚቆረቆረው የጀርመን ድርጅት ተጠሪ Ulrich Delius የባሰ እንጂ የተሻለ ሁኔታ አለመከሰቱን ነው ያስታወቁት።
ሥልጣን በጨበጡት «ሴሌካ« አማጽያንና ከሥልጣን በተፈናቀሉት ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ቦዚዜ ደጋፊዎች መካከል
፣ ትንንቁ እልባት ሳይገኝ ነው የቀጠለው። በአንድ ወር ውስጥ 1,000 ያህል ሰዎች ናቸው የተገደሉት፤ሰላም
ማሥፈኑም ሆነ ፤ ሚሊሺያ ጦረኞችን ትጥቅ ማስፈታቱ ከቶ አልሠመረም።
ተልእኮው የከሸፈበት አንዱ ምክንያት ፤ የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ የስልታዊ ግንኑነት ጉዳይ ተቋም ፤
የምርምር ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዣን -ክሎድ አላርድ እንደሚሉት በቂ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ባለመሠማራታቸው
ነው። ከሞላ ጎደል አንድ ሚሊዮን ገደማ ኑዋሪዎች ላሏት ለመዲናይቱ ለቦንጊ ፤ ለመሆኑ በምን ስሌት ነው 1,600
ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የተመደቡት በማለትም በአንክሮ ይጠይቃሉ። እንደ አላርድ ግምት በማዕከላዊት አፍሪቃ ሰላም
እንዲሠፍን ለማድረግ ፣ 6,000 ወታደሮች እንኳ አይበቁም።
የፈረንሳይ ወታደሮች ፤ በቦንጊ እንደተሠማሩ በአማዛኙ ሙስሊሞቹን የ«ሴሌካ» አማጽያን ኃይሎችን ነበረ
ትጥቅ ማስፈታት የጀመሩት። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፤ የክርስቲያኖቹ ሚሊሺያ ጦረኞች በቁጥር አነስተኛ በሆኑት
የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ጥቃት መሠንዘር ጀመሩ። በዚህም ሳቢያ በሥጋት የተዋጠው የከተማይቱ ኑዋሪ ገሚሱ
መዲናይቱን ቦንጊን ለቆ ወጥቷል። በሴሌካ አማጽያን የሚደገፉት የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሚሸል ጆቶዲያ፤
ከሚገኙበት ጦር ሠፈር ውጭ ተጽእኖአቸው በሌላው ያስገኘው አንዳች ፋይዳ የለም።
የቀድሞው የቦንጊ ከንቲባ፤ ጆሴፍ ቤንዱንጋ ለዚህ ለተባባሰ ውዝግብ ኀላፊዋ ድሮ የማዕከላዊት አፍሪቃ
ሪፓብሊክ ቅኝ ገዢ የነበረችው ፈረንሳይ ናት በማለት ነቅፈዋል። የችግሩ አሳሳቢነት በፈረንሳይ መንግሥትም በኩልም
ቀደም ሲል ይታወቅ እንጂ መላ አልተፈለገለትም።
የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሎራ ፋቢዩስ ፣ አገራቸው ፣ ጆቶዲያ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት እያደረገች
እንደሁ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ፈረንሳይ፤ እንዲሁ ታዛቢ እንጂ ሌሎች ውሳኔዎችን እንዲቀበሉ የምታስገድድ
አይደለችም፤ስለማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ መጻዔ ዕድል ውሳኔ የሚያሳልፉ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሃገራት ናቸው
ማለታቸው ተጠቅሷል።
በዛሬው ዕለት በቻድ የተሰበሰቡት የማዕከላዊው አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ አባል ሀገራት ተጠሪዎች፤
የሽግግሩ ፕሬዚዳንት ጆቶዲያ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ግፊት ማድረጋቸው እንደማይቀር ተነግሯል። ራሳቸው ጆቶዲያ፤
ጠ/ሚንስትሩን ኒኮላ ቲያንጋዬንና የብሔራዊውን የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር አሌክሳንደር ፈርዲናንድ እንጉየንዴን
ይዘው በተጠቀሰው በቻድ በተከፈተው ጉባዔ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በመሃሉ፤ የአውሮፓው ኅብረት፤ በማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ የተሠማሩትን የፈረንሳይ ወታደሮች የሚያግዝ
ጦር ለመላክ ማቀዱን አስታውቋል። የ 28 ቱ አባል ሃገራት አምባሳደሮች ከ 700 እስከ 1,000 ያህል ወታደሮች
ለመላክ ነገ ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
Source: www.dw.de
No comments:
Post a Comment