Time in Ethiopia:

Dec 26, 2013

ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የተስማማችባቸውና ያልተስማማችባቸው ነጥቦች ይፋ ተደረጉ

Geez Bet | Thursday, December 26, 2013
ግብፅ የቅኝ ግዛት የውኃ ኮታዋ እንዲከበር አሁንም ጠይቃለች
•ለመስማማት የገባችውን ቃል አፍርሳለች
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር እያደረገ የሚገኘውን ድርድር ውጤት አስታወቀ፡፡ የግብፅ መንግሥት ያቀረባቸው የግዴታ ሐሳቦች በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኙም፡፡ 

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከግብፅና ከሱዳን አቻ ሚኒስቴሮች ጋር በህዳሴው ግድብ ላይ እያደረጋቸው የሚገኙ ድርድሮችን ማክሰኞ ዕለት ለባለድርሻ አካላትና ለመገናኛ ብዙኃን ሲያሳውቅ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የተስማማችባቸውንና ያልተስማማችባቸውን ነጥቦች ይፋ አድርጓል፡፡ 
በሚኒስቴሩ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ሚኒስቴሩና ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን ሥልታዊና የተጠና እንቅስቃሴ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጐን እንድትቆም ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ባለፈው ዓመት መጨረሻ
ላይ ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ሪፖርትን ኢትዮጵያና ሱዳን መቀበላቸውን የገለጹት አቶ ፈቅ፣ ይህ ሪፖርት በግብፅ በኩል ተቀባይነትን ያላገኘ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ተገናኝተው በተስማሙት መሠረት፣ የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተግባራዊነት ላይ ውይይት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ 
በጥቅምት ወር መጨረሻ ሱዳን የተገናኙት የሦስቱ አገሮች ሚኒስትሮች በመፍትሔ ሐሳቡ ተግባራዊነት ላይ በመወያየት የሚያመቻችና የሚከታተል ኮሚቴ ለመመሥረት በሐሳብ ደረጃ መስማማታቸውን፣ ነገር ግን በኮሚቴው አባላት ስብጥር ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ውይይቱ ተቋርጦ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውሰዋል፡፡ 
የኮሚቴው አባላት ሙሉ በሙሉ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ብቻ መሆን አለባቸው በሚለው የኢትዮጵያ ፍላጎት መኖሩና በግብፅ በኩል የውጭ ባለሙያዎች እንዲካተቱ አቋም መያዙ፣ የልዩነቱ ምክንያቶች እንደነበሩ አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡ 
ይህንን ልዩነት ለመፍታት ከተያዘው ቀጠሮ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ኮሚሽን ዓመታዊ ጉባዔን ምክንያት በማድረግ ወደ ሱዳን ማቅናቱንና በወቅቱም በሦስቱ አገሮች ድርድር ላይ የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያን አቋም እንዲረዳ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ 
የሱዳን የውኃና የኤሌክትሪሲቲ ሚኒስትር መንግሥታቸው የኢትዮጵያን አቋም ሙሉ በሙሉ ከመቀበል ባለፈ፣ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የማግባባት ሚና እንደሚኖራት በመተማመን ሁለተኛው የሦስቱ አገሮች ድርድር ከመጀመሩ ቀናት በፊት ወደ ግብፅ ማቅናታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
የሱዳን ሚኒስትር በካይሮ ቆይታቸው ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳታቸውንና የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን ሐሳብ እንደሚደግፍ ተገልጾላቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ከፍታ ዝቅ ይበል የሚል ሐሳቧን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የገንዘብ ብድር እንዳታገኝ የማደርገውን ሩጫ አቆማለሁ በማለት ለሱዳኑ ሚኒስትር ቃል ገብታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለተኛው ዙር ድርድር እንዲቀጥል ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ፈቅ፣ በዚህ ድርድር ላይ ግብፅ ይዛ የቀረበችው ሰነድ ከገባችው ቃል የተለየ ነበር ብለዋል፡፡ 
በግብፅ በኩል ለሁለተኛው ዙር ድርድር የቀረበው ሰነድ በሦስቱ አገሮች የሚቋቋመው ኮሚቴ በኢትዮጵያ በኩል የሚገኙ አዳዲስ የጥናት ውጤቶችን እንዲዳስስና የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ኮሚቴው እንዲከታተል ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ማለትም የግብፅና የሱዳን የውኃ ደኅንነትና ፍላጐት ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት የሚሉ ነጥቦችን በድጋሚ በሰነዱ አካታ ማቅረቧን ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ይህንን በጭራሽ ኢትዮጵያ የምትቀበለው አይደለም፤›› ያሉት አቶ ፈቅ፣ በዚህና በሌሎች የመወያያ ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደተሞከረ ገልጸዋል፡፡ 
በውይይቱ ላይ ግብፅ ከ20 በላይ ባለሙያዎችን እንዳሳተፈች በኢትዮጵያ በኩል ግን ስድስት ባለሙያዎች እንደተወከሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በግብፅ በኩል ሆን ተብሎ ውይይቶችን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በማጓተት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን የማዳከም ጥረታቸው ውጤት አልባ እንዲሆን በጥንካሬ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ጥረት በሚመሠረተው ኮሚቴ አባላት ስብጥር ዙሪያ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኮሚቴው በሚቋቋምበት ዓላማና በተወሰኑ የኮሚቴው ተግባርና ኃላፊነቶች ላይ ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሐሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
ኮሚቴው ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊነት የመከታተል ዓላማ የሚኖረው በመሆኑ፣ እስካሁን በሦስቱ አገሮች ተቀባይነት ካገኙ የኮሚቴው ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸው ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦችን ማስጠናትና የጥናት ውጤቱን ማፀደቅ ይገኝበታል፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎቹ ቡድን ባቀረባቸው ሁለት ሐሳቦች በግድቡ ላይ ተጨማሪ የኃይድሮሎጂ፣ የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ጥናቶች እንዲደረጉ ጠይቋል፡፡ 
በመሆኑም ኮሚቴው ለሁለቱ ጥናቶች አማካሪ ድርጅቶችን መቅጠርና ማስጠናት፣ የጥናቱን ሪፖርት መገምገም፣ ማስተካከልና ማቅረብ፣ በዚህ የጥናት ሪፖርት ላይ የኮሚቴው አባላት መግባባት ካልቻሉ ጉዳዩ ለሚኒስትሮች ቀርቦ እልባት እንዲያገኝ፣ በዚህ ካልተፈታ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየት እንዲያቀርቡ የሚረዳ የቅጥርና የሥራ ዝርዝር ኮሚቴው እንዲያዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በቀሩ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትም ሦስቱ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ በሱዳን ተገናኝተው ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአማካሪ የሚጠኑት ሁለት ጥናቶች ሪፖርት ግምገማ ላይ የኮሚቴ አባላቱም ሆኑ ሚኒስትሮቹ መስማማት ካልቻሉ፣ ሙያዊ አስተያየት የሚሰጥ አማካሪ ለመቅጠር ስምምነት ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ሙያዊ አስተያየት የሚሰጠው አማካሪ ቡድን ቅጥር የሚፈጸመው በሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ስምምነት ነው የሚለው ላይ ከስምምነት አልተደረሰም፡፡ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጥ የሚቋቋመው ቡድን በጥናቶቹ የመጨረሻ ሪፖርት ላይ ብቻ አስተያየቱ ይወሰናል በሚለው የኢትዮጵያ አቋም ላይ ያለውን አለመግባባት መቅረፍ ሌላው የውይይቱ አካል ነው፡፡ 
እስካሁን የተደረጉ ድርድሮችን ውጤቶቹን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ በእጅጉ አድንቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የትኞቹንም የተፋሰስ አገሮች እንደማይጐዳ ለማሳወቅ ዩኒቨርሲቲው በአገር ውስጥ እያደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ በማስፋት ወደ ጐረቤት አገሮች እንደሚዘልቅ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በመጪው መጋቢት ወር በሱዳን ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ከካርቱም ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment