Time in Ethiopia:

Dec 19, 2013

ደቡብ ሱዳንና የተሰናከለው የዴሞክራሲ ተስፋ

Geez Bet | Thursday, December 19, 2013
የሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ከእሁዱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ዛሬ መረጋጋትዋ ተዘግቧል ። ነዋሪዎች ዛሬ ከቤታቸው መውጣት ጀምረዋል ። አልፎ አልፎ ተኩስ መሰማቱ ግን አልቆመም ። መንግሥት እንዳስታወቀው ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 10 ሰዎችን አስሯል ። 
ተዘግቶ የቆየው የጁባ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲከፈት መንግሥት ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም አንዳንድ አየር መንገዶች ወደ ጁባ ከመብረራቸው በፊት የፀጥታ ዋስትና ጠይቀዋል ። ዩናይትድ ስቴትስ ዜጎቿን ማስወጣት እንደምትጀምር አስታውቃለች ። በደቡብ ሱዳን የኃይል እርምጃ ማገርሸቱ የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ተስፋ እንዳያሰናክል አስግቷል ። በጎሳ የተከፋፈሉ የደቡብ በሱዳን ጦር ሠራዊት አባላት ባለፈው እሁድ ለሊት ጁባ አቅራቢያ ከተታኮሱ በኋላ የተፈጠረውን መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ብሎታል ።
በዚያን ለሊት የሆነው ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እንደ ሁል ጊዜው ጥቁር ሱፍና የተለመደውን ኮፊያቸውን አድርገው ሳይሆን የወታደር ልብስና መለዮ አጥልቀው ከትናንት በስተያ በሰጡት መግለጫ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ባለፈው ሐምሌ ከሥልጣን በተወገዱት የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማሻር ታማኞች መካሄዱን አስታውቀዋል ። ይሁንና ማሻር ዛሬ ታትሞ ለወጣ አንድ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ ክሱን አስተባብለው ይልቁንም ፕሬዝዳንት ኪር ደፈር ብለው የሚናገሯቸውን ለማስወገድ አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው ያሳወቁት ። ፕሬዝዳንንት ኪር በመግለጫቸው ጥቃት የሰነዘሩት ሸሽተው ጦር ኃይሉ እየተከታተላቸው መሆኑንም ተናግረዋል ። ከዚሁ ጋር በተቀናቃኞቻቸው ላይ ፍትህ ድል ያደርጋል ማለታቸው ታዛቢዎቻቸውን አስግቷል ። በደቡብ ሱዳን የኃይል እርምጃ ማገርሸቱ ጀርመናዊቷ የሱዳን ጉዳዮች አጥኚ አኔተ ቬበር እንደሚሉት በሃገሪቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ወታደራዊ አማራጮች የመሄድ ልምድ መኖሩን ነው የሚያመለክተው ።
« የንቅናቄዎቹ ቅርፅ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ይፈቅዳል ። ይህ የሱዳን ፖለቲከኞች ትውልድ በጦርነትና በግጭት የፈጀው ጊዜ ሲታይ ፣ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ የሚያሳየው ሊያደርጉ የሚችሉት ይህ ብቻ መሆኑን ነው ። ይኽውም ግጭቶችን በወታደራዊ መንገዶች መፍታት ነው ።»
እስካሁን የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በቀድሞው አማፂ ቡድን በሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በምህፃሩ SPLM የበላይነት ነው የሚመራው ። ከሱዳን ፓርላማ 90 በመቶው በላይ መቀመጫ በነዚሁ ፖለቲከኞች ነው የተያዘው ። ጦር ሠራዊቱ ፖሊሲና ቢሮክራሲውም ቅርበቱ ለዚሁ የፖለቲከኞች ድርጅት ነው ። ምንም እንኳን በይፋ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተዘርግቷል ቢባልም እስካሁን አንዳችም አማራጭ የፖለቲካ መንገድ አልታየም ።
የጁባ መንግስት ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ 7 የቀድሞ ሚኒስትሮችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ማሰሩን አስታውቋል ።የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪካ ማሻርን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችንም ለጥያቄ እፈልጋቸዋለሁ ብሏል ። ከሥራ የተባረሩት የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ማሻር ሰዎች ባለፈው ታህሳስ መግቢያ ላይ ሳልቫ ኪርን አምባገነን ሆነሃል ብለው ዘልፈው ነበር ። በዚሁ ወቅት አዲስ ምርጫ እንዲጠራም ጠይቀዋል ። ይሁንና ኪርና ደጋፊዎቻቸው ያኔ ጥሬያቸውን ወደ ጎን በመተው ይልቁንም ተቃዋሚዎቹ ሃገሪቱን ካበላሹት ሙሰኞች መካከል ናቸው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል ። በአሁኑ
  Salvakar ሳልቫ ኪር
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም ኪር ወዲያውኑ የወነጀሉት እነዚህኑ ሰዎች ነው ። ከመካከላቸው የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ና የSPLM ዋና ፀሃፊን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አሁን ታስረዋል ። የቀድሞው የSPLM መሪ የሟቹ የጆን ጋራንግ ባለቤት ሬቤላ ጋራንግ ንያንዴንግ ከማክሰኞ አንስቶ በቁም እስር ላይ ናቸው ። ከፈረንሳይ ብሔራዊ ሳይንሳዊ የምርምርና ልማት ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ ማርክ ላቬርኝ በSPLM ውስጥ ችግር የፈጠረው የፖለቲካ መቃቃር ብቻ ሳይሆን የጎሳ ልዩነትም ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ
« SPLM ውስጥ ትልቁ ለውጥ የተከሰተው በ1991 ነው ። ያኔ ሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር በጠላትነት ነበር የሚተያዩት ። ይህም 100 ሺህ ሰዎችያለቁበትን የርስ በርስ ጦርነት አስከትሏል ። ከፖለቲካው ሽኩቻ በተጨማሪ በአናሳዎቹ በኑዌሮችና በብዙሃኑ በዲንቃዎች መካከል የጎሳ ግጭት አለ ። የሁለቱም ጎሳ የቋንቋና የዘር ሃረግ ናይል ሲሆን ሁለቱም ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ከብት አርቢዎች ናቸው ። ሁለቱም የሚቀራረቡና በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙ ወነኛ ቡድኖች ናቸው ። »
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመዲናይቱ ከጁባ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ትናንት እንዳስታወቀው ሁለት ሆስፒታሎች በሰሞኑ ግርግር ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ተመዝግበዋል ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ዲፕሎማት የቆሰሉት ቁጥር 800 መድረሱን ተናግረዋል ።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ
Source: www.dw.de

No comments:

Post a Comment