Time in Ethiopia:

Nov 21, 2013

የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጤንነት እያነጋገረ ነው

Geez Bet | Thursday, November 21, 2013
- «ፕሬዚዳንቱ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ» አቶ የማነ ገብረመስቀል
- አሜሪካ ዜጎችዋ ወደ ኤርትራ እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች
ከመገናኛ ብዙኃንና ከሕዝብ እይታ ከራቁ ከአንድ ወር በላይ የሆናቸው  የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጤንነት ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡

አስማሪኖ የተባለውና መቀመጫውን በካሊፎርኒያ አሜሪካ ያደረገው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ድረ ገጽ እንደጻፈው፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከወትሮው በተለየ ከመገናኛ ብዙኃን ርቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለመጨረሻ ጊዜ በሚዲያ የታዩት ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የአንበጣ መቆጣጠሪያ ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት 58ኛ ጉባዔ ላይ መሆኑን ድረ ገጹ ጽፏል፡፡
ከዚያም በጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. በጉበት ሕመም ምክንያት አስመራ በሚገኘው የአየር ኃይል ሐኪም ቤት ለስድስት ሰዓታት ያህል ሕክምና ተደርጐላቸው  ወደ ቤተ መንግሥት መመለሳቸውን ጽፏል፡፡ በመቀጠልም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ወይም ኳታር ለተጨማሪ ሕክምና መሄዳቸው እንዳልቀረ አትቷል፡፡
ስለ ጉዳዩ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ የማነ ገብረመስቀልን በትዊተር ገጻቸው ለሪፖርተር ማብራሪያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ «አስቂኝ ቅዠት ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
«ፕሬዚዳንቱ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው፤» በማለት መሠረተ ቢስ የሆነ ወሬ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ «ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ አስማሪኖ ውሸት ማውራት ስለፈለገ ነው፡፡ ማንኛውንም የአስመራ ነዋሪ መጠየቅ ይቻላል፤ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ወደ ቢሮአቸው ሲገቡ ያዩአቸዋል፤» ብለዋል፡፡
 ከዚህ ቀደም ከሚያዝያ 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንድ ወር በላይ ከመገናኛ ብዙኃን መጥፋታቸው መነጋገሪያ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 
በተያያዘ ዜናም የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የቆንስላ ጉዳዮች ቢሮ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ኤርትራ ምንም ዓይነት ጉዞ እንዳያደርጉ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በአገሪቷ ላይ የሚታየውን የፀጥታ ችግር እንደ ምክንያት በመግለጽ ከአሁን በፊት በግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ያወጣውን የጉዞ ማዕቀብ ማስጠንቀቂያ አጠናክሯል፡፡
ስቴት ዲፓርትመንት በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ የአሜሪካና የኤርትራ ድርብ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ያለምንም ምክንያት እየታሠሩ ነው፡፡ በተጨማሪም በመርከብ የሚጓዙ የአሜሪካ ዜጎች በኤርትራ የባህር ዳርቻ እንዳይጓዙና መልህቆቻቸውን እንዳይጥሉ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ አስተላልፏል፡፡ 
የኤርትራ መንግሥት መቀመጫው ሶማሊያ ለሆነው የአልሸባብ አክራሪ ቡድን ድጋፍ ያደርጋል በማለት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በታኅሳስ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. የመሣሪያ ማዕቀብ መጣሉ ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ኮሚቴ ግን የኤርትራ መንግሥት ለአልሸባብ «ቀጥታ» ዕርዳታ እንደማያደርግ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
Source: http://www.ethiopianreporter.com
 

No comments:

Post a Comment