በርካታ ሰዎች ተደብድበዋል በላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ከ70 በላይ ሰዎች ታስረዋል
በሳኡዲ አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና
እንግልት ለመቃወም በትላንትናው እለት ሰማያዊ ፓርቲ ጠርቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በፀጥታ ሀይሎች የከሸፈ ሲሆን፤
ለሰልፉ የወጡት ሰዎች፣ መንገደኞች፣ በተለያየ ምክንያት ጥቁር የለበሱና ሌሎችም ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ ጋዜጠኞችን
ጨምሮ ከሰባ በላይ ሰዎች በላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል፡፡
በድብደባው ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሃይሎችም እንደተጐዱ የላንቻ
ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ ገልፀዋል፡፡ ሰልፉን የጠራው ፓርቲ አመራሮች ከፅፈት ቤታቸው ሳይወጡ መታሰራቸው የተሰማ ሲሆን
የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ አካባቢ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ተከቦ ውሏል፡፡ ወደ ኤምባሲው የሚጠጋ፣ ሰብሰብ
ብሎ የቆመ፣ ፎቶ ሲያነሳ የተገኘና ሌሎችም በፖሊስ ነጭ ፒክ አፕ መኪና እየተጫኑ ላንቻ አካባቢ በሚገኘው የወረዳ
18 ፖሊስ የተወሰዱ ሲሆን፤ ፖሊስ ጣቢያ ከገቡት ውስጥ የ70 አመት አሮጊት እና የ62 አመት አዛውንት
ይገኙበታል፡፡
“ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ከልጄ ጋር መንገድ እየሄድኩ ነው
የተያዝኩት” ብለዋል፤ የ70 ዓመቷ አሮጊት፡፡ ከታሰሩት መካከል በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ኢዮብ አርጋው
የተባለ ወጣት፤ አብረውት በታሰሩት ሰዎች ጉትጐታና ለቅሶ ፖሊስ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ወስዶታል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ
ረቡዕ ማታ በሰጠው መግለጫ፤ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ አራት ዋና ዋና ነገሮች እንደሚከናወኑ ገልፆ ነበር፡፡ ሰላማዊ
ሰልፍ የሚወጡ ሁሉ በሳኡዲ የሞቱትን፣ የታሰሩትን እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማሰብና ሀዘናቸውን
ለመግለጽ ጥቁር እንዲለብሱና ጥቁር ሪቫን ክንዳቸው ላይ እንዲያስሩ፣ ሙስሊሙ በዕለቱ በጁምአ ሶላት እንዲፀልይ
እንዲሁም፣ በሳኡዲ ኤምባሲ በር ላይ ተቃውሞ ከመሰማቱ በፊት ለሞቱት የህሊና ፀሎት ለማድረግና በሳኡዲ አረቢያ
እየደረሰ ስላለው አጠቃላይ ጉዳት የሚያትት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጽሑፍ ቀርቦ ሰልፉ እንደሚበተን ገልፆ ነበር።
ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ፓርቲው ለከተማው መስተዳድር በደብዳቤ
ማሳወቁን እና መስተዳድሩ ምላሽ አለመስጠቱን፤ ይህ ደግሞ ሰልፉ መፈቀዱን የሚያሳይ እንደሆነ ኢ/ር ይልቃል ቀደም
ብለው ገልፀው ነበር፡፡ የፓርቲው አባላት እንደገለፁት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች
ለሰልፉ ከፓርቲው ጽ/ቤት ሳይወጡ ነው በፖሊስ የተወሰዱት፡፡ በስፍራው ተገኝተን እንደታዘብነው “ልጆቻችን ታረዱ
ተገደሉ” እያሉ የሚያለቅሱ እናቶች የነበሩ ሲሆን “ፖሊስ በህዝቡ ላይ ድብደባና እንግልት ማድረሱ አግባብ አይደለም፤
ይህ ኢትዮጵያ ሳይሆን ሳኡዲ ማለት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ “ፎቶ አንስታችኋል” በሚል ከሌሎች ሰዎች ጋር
በፖሊስ ተይዘው ወረዳ 18 ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ከስድስት ሰዓት እስከ ስምንት ተኩል ቆይተዋል፡፡
በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ከነበሩት መካከል አብዛኞቹ መንገደኞችና
ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ጋዜጠኞች ብቻ ተጠርተን የጣቢያው ሃላፊ
ያነጋገሩን ሲሆን፤ “ሰልፉ አልተፈቀደም፣ ህገወጥ ነው፤ ህዝቡ ኤምባሲውን ሰብሮ ሊገባ ሲል ዝም ብሎ ማየት
አይቻልም፣ ነገሩን በክፉ አትዩት ጉዳዩን የኢትዮጵየ መንግስትና የአለም መንግስታት እየተከታተሉት ነው” በማለት
ካሜራችንን እና መታወቂያችንን የመለሱልን ሲሆን አንድ ጋዜጠኛ በሞባይሉ ያነሳውን ፎቶ እንዲያጠፋ ተደርጐ
ተለቀናል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ ከ70 በላይ ሰዎች ማተሚያ ቤት እስክንገባ ድረስ በእስር ላይ እንደነበሩ
የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
Soorce: http://www.addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment