Time in Ethiopia:

Nov 24, 2013

አቶ ያረጋል አይሸሹም ከ5 የሙስና ክሶች በ4ቱ ነፃ ሆኑ

Geez Bet | Sunday, November 24, 2013
በተለያዩ ከተሞች በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በልጆቻቸው ስም 17 ቦታዎችንና ቤቶችን ይዘዋል ከሚለው ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡
ከባለቤታቸው ጋር ምንጩ ያልታወቀ 490ሺ ብር በባንክ አንቀሳቅሰዋል ከሚለው ክስ ነፃ ናቸው ተብሏል:: የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ያረጋል አይሸሹም፤ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ከቀረቡባቸው አምስት ክሶች መካከል በአንዱ ብቻ “ጥፋተኛ ናቸው” የተባሉ ሲሆን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል በሚል ከቀረበባቸው ክሶች ነፃ ሆኑ፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ሃብታሙ ሂካ፣ ከሁለት የግል ድርጅት ሃላፊዎች ከአቶ ጌዲዮን ደመቀና ከቶ አሰፋ ገበየ ጋር “ጥፋተኛ ናቸው” የሚል ውሳኔ የተላለፈባቸው፤ ለሦስት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ከወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ ክስ ነው፡፡ ህገወጥ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር  ለመምህራን ኮሌጅ፣ ለአዳሪ ት/ቤት እና ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የግንባታ ጨረታ ከመንግስት መመሪያ ውጪ እንዲከናወን አድርገዋል በሚለው ክስ 4ቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ የከፍተኛው ፍ/ቤት ችሎት ሐሙስ እለት ገልጿል፡፡ 
አቶ ያረጋል እና አቶ ብርሃኑ ለተቋማቱ ግንባታ  የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን እያወቁ በግልጽ ተወዳዳሪዎችን ጋብዘው ማጫረት ሲገባቸው፣ የሶስቱንም ፕሮጀክቶች የዲዛይን፣ የቁጥጥር እና የኮንትራት ጨረታ በህገወጥ መንገድ ለጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት በጥቅሉ በ250ሺህ ብር ሰጥተዋል ይላል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቀረበው ክስ፡፡ አቶ ያረጋል ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ጨረታዎቹ  አቶ ሃብታሙ በሚመሩት የትምህርት ቢሮ በኩል እንዲከናወኑ አድርገዋል የሚለው የኮሚሽኑ ክስ፣ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ስራው  በ “ውስን ጨረታ” እንዲከናወን በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ብሏል፡፡  ለዚህ ወረታም አቶ ያረጋል ከ3ኛ ተከሳሽ ከአቶ ጌዲዮን ደመቀ፤ 50ሺህ ብር እንዲሁም አቶ ሃብታሙ 75ሺህ ብር እጅ መንሻ መቀበላቸው በክሱ ተገልጿል፡፡
“ጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት” ፕሮጀክቶቹን የመምራት አቅም እንደሌለው እያወቁ ውል የፈረሙት አቶ ጌዲዮንና ወኪላቸው አቶ አሰፋ ገበየሁ፤ ስራውን ለ5 ዓመታት በማጓተት መንግስትን ለ2.8 ሚ.ብር ተጨማሪ ወጪ ዳርገዋል ብሏል - የፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡
ፍ/ቤቱም በአራቱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ባለስልጣናቱና ፕሮጀክቶቹን እንዲመራ የተደረገው አማካሪ ድርጅት፤ በህገወጥ የጥቅም ትስስር፣ የትምህርት ተቋማቱን ግንባታ ለሦስት ድርጅቶች ሰጥተዋል የሚለው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ የሚመሩት “ጋድ ኮንስትራክሽን” በ40 ሚ. ብር የአዳሪ ት/ቤትና በ18ሚ ብር የመምህራን ኮሌጅ እንዲገነባ፣ አቶ መክብብ የሚመሩት ንብረት ለሆነው “ኮለን ኮንስትራክሽን” ደግሞ በ17 ሚ. የቴክኒክና ሙያ ተቋም እንዲገነባ በመስጠት ስራው አጓትተዋል ብሏል፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም ከዚህ ክስ ነፃ መሆናቸውን ፍ/ቤቱ ገልፆ፣ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና አራቱ የግል ድርጅት ሃላፊዎች ግን ጥፋተኛ ናቸው በማለት ወስኗል፡፡
ሌላኛው ክስ፣ አቶ ያረጋል፣ እንዲሁም የትምህርት ቢሮ ሃላፊውና ወንድማቸው ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል የሚል ነው፡፡
ርዕሠ መስተዳደር በነበሩበት ወቅት ደሞዛቸው 4500 ብር እንደነበረና ከዚያም  የፌደራል የህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲሠሩ 5670 ብር ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበረ የሚገልፀው የኮሚሽኑ ክስ፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ሃብት አካብተዋል በማለት ከሷቸዋል፡፡
አቶ ያረጋል በራሳቸው ስም በአዲስ አበባ በተለያዩ ከተሞች አራት ቦታዎችንና ቤት ይዘዋል የሚለው የክስ ዝርዝር፣ በባለቤታቸው ስም ደግሞ በ7 ሚሊየን ብር የሚገመት ሆቴልና ድርጅት እንዲሁም ስምንት ቦታ፣ የንግድ ሱቆችና ቤቶችን ቦታዎችን በተለያዩ ከተሞች ይዘዋል ይላል፡፡ በቤንሻንጉል ውስጥም በሁለት ልጆቻቸው ስምም 5 ቦታዎች ይዘዋል፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ቅርንጫፎች በራሣቸው እናበባለቤታቸው ስም ከ490 ሺ ብር በላይ አንቀሳቅሰዋል ብሏል - ፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡
የባለስልጣናት ሃብት ምዝገባ ሲከናወን ሃብታቸውን ሙሉ በሙሉ አላሣወቁም የተባሉት አቶ ያረጋል፤ “ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል” የሚለውን ክስ በበቂ ማስረጃ መከላከል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡
የትምህርት ቢሮ ሃላፊውም እንዲሁ ከወንድማቸው ጋር ከተመሳሳይ ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በሁሉም ክሶች ላይ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ባለ 170 ገጽ ትንተና በንባብ ለማሰማት ሁለት ቀን ፈጅቶበታል፡፡
የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠባቸው ክሶች ላይ ከከሳሽ እና ከተከሳሽ የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለህዳር 26 ቀን ተቀጥሯል፡፡
Source: Addis Admass

No comments:

Post a Comment