‹‹በስሚ ስሚ ከየትም የሚለቃቀሙ ታሪኮች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት››
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በጋዜጠኝነትና በዲፕሎማትነት ሲታወቁ በዚህ ዘመን ደግሞ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ ናቸው፡፡
ታሪክ ሲጽፉም ማስረጃዎችን በሚገባ እንደሚያገላብጡና
እንደሚመረምሩ ይነገርላቸዋል፡፡ በተለይ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ለንባብ ባበቋቸው የታሪክ መጻሕፍት የበለጠ
ይታወቃሉ፡፡ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ፣
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ታሪክ›› የሚባሉት መጻሕፍት የበለጠ ታዋቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና
አገልግሎት ድርጅትን መሥርተው በኃላፊነት ከመምራታቸው በፊት፣ የቤተ መንግሥት ዘጋቢ የነበሩ ሲሆን፣ ረዳት ሚኒስትር
ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በዲፕሎማሲው ዓለም ደግሞ በተለያዩ አገሮች በተለያዩ ኃላፊነቶችና በአምባሳደርነት ጭምር
አገልግለዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን
መንግሥት ከጅምሩ እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ የሚተነትነውና በበርካታ መረጃዎች የታጀበው አዲሱ መጽሐፋቸው አንባቢያን ዘንድ ደርሶ እየተነበበ ነው፡፡ ቀጣዩን ክፍል ለመጻፍ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ቀርቧል፡፡
መንግሥት ከጅምሩ እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ የሚተነትነውና በበርካታ መረጃዎች የታጀበው አዲሱ መጽሐፋቸው አንባቢያን ዘንድ ደርሶ እየተነበበ ነው፡፡ ቀጣዩን ክፍል ለመጻፍ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- አምባሳደር ዘውዴ የሕይወት ታሪክዎ ምን ይመስላል? እስቲ ባጭሩ ይግለጹልን?
አምባሳደር ዘውዴ፡- አመሰግናለሁ፡፡ የተወለድኩት በአዲስ አበባ ከተማ
ነው፡፡ በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ሥጋ ቤት ሠፈር ተብሎ በሚጠራውና በአሁኑ ስሙ ኦርማ ጋራዥ በሚባለው አካባቢ
ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም. ነው የተወለድኩት፡፡ ዕድገቴም በዚያው አካባቢ ነው፡፡ የተማርኩት በፊት ደጃዝማች
ገብረ ማርያም የአርበኞች ትምህርት ቤት በሚባለው ከዚያም ሊሴ ገብረ ማርያም በተባለው ትምህርት ቤት ነው፡፡
የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት እዚያ ነው፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደ ሥራ ዓለም ነው
ያመራሁት፡፡ በሬዲዮ መናገርን እንደ ሕልም አየው ስለነበር፣ ንባብም ስለምደፍርና ሰዎችም ያደፋፍሩኝ ስለነበር
አጋጣሚ ሆኖ እዚያው ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ሳለሁ አንድ ሁለት ቴአትሮችን አዘጋጅቼ ታወቅኩ፡፡ በጊዜው
የገንዘብና የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ክቡር አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ በእርግጥ ያኔ ሚኒስቴር አይባልም
የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤትን ይመሩ ስለነበር፣ አመልክቼ በሬዲዮ አንባቢነትና በቤተ መንግሥት ዜና አቅራቢነት
ተቀጥሬ ለሦስት ዓመት ያህል ሠራሁ፡፡ ከዚያም ወደ ፈረንሳይ አገር ተልኬ የጋዜጠኝነትን ሙያ አጠናሁ፡፡ ከአራት
ዓመት ቆይታ በኋላም ዲፕሎማዬን ይዤ ተመለስኩኝና በኢትዮጵያ ድምፅ ዕለታዊ ጋዜጣና ወርኃዊው የመነን መጽሔት
ዳይሬክተር ሆኜ ሠራሁ፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ በመንግሥቱ ነዋይ ኩዴታ ምክንያት በጊዜው ከነበረው ችግር አኳያ ሠራተኞችን ከሚሠሩበት ቦታ
መቀያየር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ እኔም ከጋዜጣውና ከመጽሔቱ ኃላፊነት ተነስቼ ወደ ሬዲዮ ተመለስኩኝ፡፡ የብሔራዊው
የአማርኛ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሆኜ ሠራሁ፡፡ ከዚያም በጊዜው የወሬ ምንጭ እየተባለ ይጠራ የነበረውን የዜና
አገልግሎት አቋቋምኩና በዋና ዳይሬክተርነት መሥራት ጀምሬ የረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ አገኘሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ
ዲፕሎማሲው ሥራ አመራሁና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በፓሪስ የአምባሳደሩ ምክትል ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ
ተመልሼም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር በመሆን ካገለገልኩ በኋላ፣ በሮም የንጉሠ ነገሥቱ አምባሳደር ሆኜ
ተመደብኩ፡፡ በቱኒዚያና በሌሎችም አገሮች በተከታታይ በአምባሳደርነት ሠርቼያለሁ፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት ፈርሶ
ደርግ ሲመጣ እኔም አብሬ ከኃላፊነቴ ተሰናበትኩኝ፡፡ በጊዜው ትንሽ ችግር ቢደርስብኝም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ መሥሪያ ቤት የመንግሥታት ግንኙነትና
የፖለቲካ ኃላፊ ሆኜ ለአሥራ ሦስት ዓመታት ያህል ካገለገልኩ በኋላ ዕድሜዬ ለጡረታ በመድረሱ ጡረታ ወጣሁ፡፡ አሁን
በዘመኔ ያየሁትንና የተመራመርኩትን ሁሉ ለአገር ይጠቅማል በሚል እሳቤ በመጻፍ ላይ እገኛለሁ፡፡ እስካሁንም ሦስት
ያህል መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እስቲ ስለነዚህ ሦስት መጻሕፍት ይንገሩን?
አምባሳደር ዘውዴ፡- የመጀመሪያው ‹‹የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ አፄ
ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት›› የሚል ነበር፡፡ ይህም የተጻፈበት ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ኤርትራ እንዴት
በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር እንደገባች ብዙ ነገር ይባል ስለነበር ነው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች አፄ ኃይለ ሥላሴ
ኤርትራን ከዓለም መንግሥታት ጋር በመደራደር ወደራሳቸው እንደቀላቀሏት ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ፍርድ በተጓደለ ሁኔታ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ለኢትዮጵያ እንደተሰጠች ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ኤርትራ ራሷ ፈልጋ
ከኢትዮጵያ ጋር እንደተቀላቀለች የሚገልጹም አሉ፡፡ ስለዚህ እኔ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለኤርትራውያን እውነተኛው
ታሪክ ለምን አይወጣም ብዬ በማሰብ መጽሐፉን አዘጋጅቻለሁ፡፡ ኤርትራ የሚለው ቃል ከየት እንደመጣ፣ በምን ሁኔታ
የጣሊያን ቅኝ እንደነበረች፣ ከዚያም እንግሊዞች ጣሊያኖችን አባረው በምን ምክንያት ለአሥር ዓመታት እንዳስተዳደሯት፣
የኢትዮጵያ መንግሥትም ኤርትራ ወደ እናት አገሯ መቀላቀል አለባት ብሎ ምን ያህል እንደተከራከረ የሚያስረዳ፣
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ጉዳዩን በምን መልኩ እንደመረመረና ምን ዓይነት ፍርድም እንደሰጠ ደህና አድርጎ
የሚያብራራ መጽሐፍ ነው የጻፍኩት፡፡ በዚህ መጽሐፍ የተነሳ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ኤርትራውያንም የተደሰቱበት
በመሆኑ አሁን ድረስ እየደወሉ መጽሐፉን እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ይጠይቁኛል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም ተጨማሪ
ቅጅዎችን ለማሳተም እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡
ሁለተኛው መጽሐፍ ‹‹ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ›› ይባላል፡፡ ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያን ለ58
ዓመታት የመሯት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበረ፣ የልጅ እያሱ ጉዳይ፣
ከልጅ እያሱም በኋላ የንግሥት ዘውዲቱ መምጣትና ራስ ተፈሪም እንዴት አልጋ ወራሽ ሆነው ሥልጣን ላይ እንደወጡ
የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም በዘመኑ የነበረውን የአስተዳደር ሁኔታ መረጃዎችን ሰብስቤ ነው የጻፍኩት፡፡ ይህ መጽሐፍ
ባጭሩ የተፈሪ መኮንን የሥልጣን ታሪክ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ከልጅነት ጀምሮ ያለውን ረዥሙን ጊዜ መዳሰስ
ያስፈለገው እሳቸው ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ ያለፉባቸውን ሁኔታዎች በማስታወስ፣ እንዴት የመሪነት ሥልጣኑን እንደያዙ
ለማሳየትና በዘመናቸውም የነበራቸውን ታሪክ በተሻለ ሁኔታ ለመግለጽ በማሰብ ነው፡፡ ይህንን ያነበቡ ሰዎችም በቀጣይ
የጻፍኩትን ታሪካቸውን ለማንበብ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ሦስተኛው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት
ታሪክ›› የሚለው ነው፡፡ እንግዲህ ይህ መጽሐፍ የተከለሰው ሕገ መንግሥት እስከፀደቀበት እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ
ያለውን ታሪክ በስፋት የሚተርክ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ዕድሜና ጤናው ካለ ከዚያ በኋላ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸውና
የመንግሥታቸው ማብቂያ ድረስ ያለውን ለመቀጠል እሞክራለሁ፡፡ በእርግጥ ያለው ሁኔታም ለዚያ የሚጋብዝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ ብዙ እንደመረዳትዎ አሁን ላይ ሆነው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሕገ መንግሥት ከማግኘቷ በፊትና በኋላ ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ዘውዴ፡- መቼም የኢትዮጵያ አስተዳደር በልምድ እንዲህ
እንዲህ እያለ በነአፄ ምንሊክ ጭምር ተመሳሳይ ሆኖ የመጣ ነው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ሲደርስ ግን መልኩን
ቀይሯል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም መንግሥታት እስካሁን ድረስ ከልማዳዊው አስተዳደር አልወጡም፣ ፊውዳሎች ናቸው፣
ወዘተ ይሉናል የሚለው ሥጋት በመኖሩና አዲስ የአስተዳደር ዕቅድ የማውጣት ፍላጎቱም ስለነበር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነውን ሕገ መንግሥት ሠርተው አቀረቡ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ምንድነው? በመጠኑም ቢሆን ሕዝብ
ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ የሚነጋገርበትና የሚወያይበት ነው፡፡ በእርግጥ እንደራሴዎች በሕዝብ በቀጥታ ተመርጠው ወደ
ፓርላማ የገቡበት አይደለም፡፡ መንግሥት በሕዝብ ስም መርጧቸውና ብዙ ያውቃሉ የተባሉ የሕዝብ እንደራሴዎች ነበሩ
የተወከሉት፡፡ ስለዚህም በሕዝብ ምክር ቤቱ የሕዝብን ጉዳይ እናዳምጥ ብለው የመሠረቱት ጉባዔ ነበር፡፡ ይኼ ደግሞ
የመጀመሪያው የመረማመጃ እርከን ነበር፡፡ በዚህም ለሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ከመሩ በኋላ በ1948 ዓ.ም.
የተሻሻለውን ሁለተኛውን ሕገ መንግሥት ሠርተው አቀረቡ፡፡ ይኼኛው ደግሞ እንደሚታወቀው የሕዝብ እንደራሴዎች በቀጥታ
የሚመረጡበት ነበር፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልነበሩም፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ጅማሬ እንደ አመጣጡ ሊሰምር አልቻለም፡፡ በመቀጠል መከናወን የነበረባቸው
በመተዋቸው ቆይቶ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ? ከፍፁማዊ ዘውዳዊ ሥርዓት
ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሸጋገር አይቻልም ነበር?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደረጃ በደረጃ ነው
የሄዱት፡፡ አዲስ የአስተዳደር ዕቅድ የነደፉት ተራማጅ ስለነበሩም ነበር፡፡ ከውጭ እንጂ ከአገር ውስጥ የቀረበላቸው
ጥያቄም ሆነ አስተያየት አልነበረም፡፡ በጄኔቭ የመንግሥታቱ ስብሰባም ላይ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ለማመቻቸትና
በዘመኑ የአስተዳደር ዘይቤ ለመቀጠል ቃል ገብተዋል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ያለምንም ችግር ለሃያ
አምስት ዓመታት ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ሁለተኛውንም ሕገ መንግሥት ስንመለከት ማንም ቀርቦ ይሻሻል አላላቸውም፡፡ እኔ
እስከማውቀው እሳቸው ናቸው መሻሻል አለበት የሚል ሐሳብ ያቀረቡት፡፡ እሳቸው ሲባል ደግሞ ረዳቶቻቸውን ጨምሮ ማለት
ነው፡፡ አሁን እንግዲህ እሳቸው ምልክት ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ መንግሥት እንዲቋቋም ሐሳብ ቀርቦላቸው
ነበር የሚባለውን ስንመለከት፣ በእርግጥ ይህን ሐሳብ ያቀረቡ ሰዎች ከሩቅ ሆነው ጉዳዩን የሚመለከቱ እንጂ በቅርብ
የነበሩ አይደሉም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህን ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩና አገሪቱም ገና
ያላደገች ስለነበረች ነው፡፡ በጊዜው የነበረው አስተሳሰብ ንጉሥ ይመራል፣ ያስተዳድራል፣ ይገዛል የሚል ነበር፡፡
አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው ሥርዓት አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖር ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልጋል፡፡
ይኼ በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ ያን ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ የሁለተኛውን ሕገ መንግሥት አዳክመውና ለሥልጣናቸው
አመቻችተው ነው ያቀረቡት የሚለው ተቃውሞ አሁን ነው የመጣው፡፡ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት በሁለተኛው ሲተካ
ሁለተኛውም ለተወሰኑ ዓመታት ቆይቶ መለወጥ ወይም ደግሞ ዘመናዊውን እሳቤ መያዝ ነበረበት፡፡ ባለበት ዛገ ነው
የተባለው፡፡
ሪፖርተር፡- ለዚያም እኮ ነው መቀጠል የነበረበት ጅምር ተኮላሽቶ በንግሥት ዘውዲቱ ጊዜ
ጠቅልለው የወሰዱትን ሥልጣን በፍፁማዊ አገዛዝ መምራቱን ለማስቀጠል ሞከሩ የሚባለው፡፡ ለምንድነው ያንን የተሻለ
አካሄድ ማስቀጠል ያልተቻለው?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ማለፊያ፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ምልክት የሆኑበት
ምክንያት እኮ ሌላ አይደለም፡፡ ያን ጊዜ ንግሥት ለመሪነት አልተዘጋጁም ነበር፡፡ የአፄ ምንሊክን ሥርወ መንግሥት
ለማስቀጠል በነበረ ፍላጎት ተፈሪ መኮንንን አልጋ ወራሽ አድርገው ያመጡ ባለሟሎች የነበራቸው አስተሳሰብ እንደዛሬው
ባለመሆኑ፣ የነበረውን ሥርዓት በዘር ሐረግ የማስቀጠልን ሒደት ነበር የመረጡት፡፡ ያንጊዜ ንግሥት ዘውዲቱ ምንም
ዓይነት የመሪነት ክህሎት አልነበራቸውም፡፡ በዘውዱ ዙሪያ ከነበሩት አማካሪዎች ጋር ነበር የሚመካከሩት፡፡ ያም ሆነ
ይህ አስተዳደሩን በዘመናዊ ዕቅድ መያዝ አለብን ይሉ የነበሩት ራሳቸው ራስ ተፈሪ ናቸው እንጂ ይህንን ማንም
አይቀበለውም ነበር፡፡ ለዚህ ፍላጎታቸውም ብዙ ችግሮችን አልፈዋል፡፡ ይህን የተራማጅነት አስተሳሰባቸውን መዘንጋት
የለብንም፡፡ እሳቸውን የሚተካና የነበረውን ሁኔታ አስተካክሎ ለመምራት የተዘጋጀ ሰውም አልነበረም፡፡ ችግሩ ግን
የተፈጠረው መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ደህና መጥተው መጨረሻው ላይ ምን መሥራት እንደነበረባቸው ዝግጁነቱ
እንዴት አልነበረም ነው የሚባለው፡፡
ሪፖርተር፡- በካቲት 66 የፈነዳው አብዮት ከጀርባው የተማሪዎችና የተራማጅ ኃይሎች ግፊት
ነበረበት፡፡ በሌላ በኩል ዘመነ መሳፍንትን ለማስቀጠል የሚረባረቡ ኃይሎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሀል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ሁለቱን ኃይሎች መቆጣጠር ወይም ማመጣጠን ባለመቻላቸው ሚዛናቸውን ስተው ወድቀዋል ይባላል፡፡ ይህንንስ እንዴት
ያዩታል?
አምባሳደር ዘውዴ፡- እርግጥ ነው መጨረሻቸው አላማረም፡፡ አንዱ
ምክንያት የዕድሜ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በጊዜው 80 ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ሰው እንዲያውም በ80 ዓመታቸው የሕገ መንግሥት
ለውጥ አዘጋጅተው መተካካቱን ያስቀጥላሉ ብሎ ነበር የጠበቀው፡፡ አልጋ ወራሽም ይታመሙ ነበር፡፡ ልዑል መኮንንም
እንደሚታወቀው የሉም፡፡ ሰው እንደሚናገረው ባልተዘጋጀ ሥርዓት ላይ ሁሉ ነገር መደፍረስ ቻለ ማለት ነው፡፡ እንደኔ
እምነት ታዲያ እሳቸው ‹እኔ እንግዲህ ይኼው ዕድሜ ሰጥቶኝ ሰማንያ ዓመት ድረስ ከሕዝቤ ጋር ቆየሁ፤ አሁን ደግሞ
ለወደፊቱ በማሰብና የዘመናዊ ዕቅዱን ለመተግበር ይኼ ይኼ ይስተካከል› ብለው ከሕዝቡ ጋር ተነጋግረው ቢሆን ኖሮ፣
ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላ የተከሰተው ሁሉ ባልተከሰተ ነበር እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ሁለተኛው የተሻሻለ ሕገ መንግሥት ለአገሪቷ ምን አምጥቷል ማለት ይቻላል?
አምባሳደር ዘውዴ፡- በበኩሌ የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ብዙ ቁም
ነገሮችን ለኢትዮጵያ አምጥቷል ባይ ነኝ፡፡ በመጀመሪያ በሕዝብ የተመረጠ እንደራሴ ነበር ወደ ፓርላማ የሚገባው፡፡
ይኼ ደግሞ አንድ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት አንተ ለዚህ ሕዝብ ወኪል ትሆንለታለህ ብሎ ነበር
የሚሾመው፡፡ ሁለተኛው ማንኛውም የመንግሥት በጀትና ዕቅድ ተፈጻሚ የሚሆነው ለፓርላማ ከቀረበ በኋላ ነበር፡፡ ሌላው
መንግሥት ማንኛውንም ጉዳይ ከውጭ አገሮች ጋር ሲያከናውን የሚፀድቀው በፓርላማው ነበር፡፡ እንግዲህ እዚህ ደረጃ
ከተደረሰ በኋላ ለምን እዚያው ላይ ቀረ? ለምን ወደፊት አልገፋም? የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እኔም በዚህ
እስማማለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ንጉሡ የነበረው መልካም ጅማሬ ወደፊት እንዳይገፋና ለገዛ ሕልውናቸው ሲሉ መንገድ የመዝጋት ፍላጎት አልነበራቸውም ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ይኼ እንግዲህ እንደ ሰው ስሜት የተለያየ ነው፡፡
አንዳንዱ የፈለገውን ያህል ተራማጅ ቢሆንም የሠራሁት በቂ ነው ብሎ ካሰበ ሒደቱን የሆነ ደረጃ ሲደርስ ሊያቆመው
ይችላል፡፡ ያም ጅማሬ በቆመበት ቀርቷል፡፡ ያ የነበራቸው ኃይል ያስኬዳቸው እስከዚያ ድረስ ነበር፡፡ በዚያ ላይ
ደግሞ መካሪም አለ፡፡ በቂ ነው እኮ! ሰጥተዋል እኮ! ይኼ ፓርላማ ሚኒስትሮችን እያንቀጠቀጠ ይጠይቃል ከዚህ በላይ
ምን ይምጣ? ብለው የሚመክሩም አይጠፉም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለምን? ብሎ የሚጠይቅ የለም ነበር፡፡ ስለዚህም ዋናው
ችግር ለተሻሻለው ሕገ መንግሥት የቀረበ ሌላ ማሻሻያ አለመቅረቡ ነበር፡፡ ለዚህም ደግሞ መልስ የሚሰጡ አይጠፉም፡፡
በ1958 ዓ.ም. ንጉሡ ባወጡት አዋጅ የሚሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስትሮችን እየመረጠ ለፓርማውና ለንጉሡ ያቀርባል
የሚል ነበር፡፡ ይህም ቀላል ዕርምጃ አልነበረም፡፡ ይህ ግን በሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንዴት?
ብለው የሚጠይቁ ተቀናቃኞች መጡ፡፡ መቼም ያው ሙከራ ነበር ነው ሊባል የሚችለው፡፡
ሪፖርተር፡- የጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለንጉሡ እንደ ማንቂያ ደውል
ነበር የሚሉ ወገኖች ያኔ ነበር የቤት ሥራው መጀመር የነበረበት ብለው ያስባሉ፡፡ ለምን ነበር ክስተቱን እንደ
አጋጣሚ መውሰድ ያልተቻለው?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ልክ ነው፡፡ የመንግሥቱ ነዋይ ኩዴታ የማንቂያ
ደውል ነበር የሚባለውን ሙሉ ለሙሉ እስማማበታለሁ፡፡ ነገር ግን የተደራጀ ኩዴታ አልነበረም፡፡ ማንቂያ ነው፡፡
በሥርዓት ተዘጋጅቶና ተጠንቶ የተካሄደ አልነበረም፡፡ እኔ ራሴ እንደሌሎቹ ሁሉ አጠገባቸው ሆኜ ጨፍሬያለሁ፡፡ ደንበኛ
ማንቂያ ነው፡፡ በመሪዎቻችን ዘንድ የተለመደው ግን ይህ ዓይነቱ ነገር አይደለም፡፡ በግድ ሳይሆን ራሱ አዘጋጅቶና
አመቻችቶ ሲለቅ ነው ደስ የሚለው፡፡ ተማሪው ይህን ስለጠየቀ እንዲህ ይሁንለት፣ ወታደሩ እንዲህ ስላለ ይፈቀድለት፣
ወዘተ የሚል ነገር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አልነበረም፡፡ የተወሰነ ነገር ተሞክሯል፡፡ የሆኑ ኮሚቴዎች
ተቋቋሙ፣ የሥራ ቅልጥፍና ተጀመረ፣ ወደፊት የምንለው ብዙ ነገር አለ ተባለ፡፡ ይሁንና ግን አንዱም ነገር ሥራ ላይ
አልዋለም፡፡ ሰው ጭጭ ብሎ ስለተቀመጠና ጊዜውም ስላለፈ ተዘነጋ እንጂ በመጀመሪያ ጊዜማ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ለካ
ንጉሥን መድፈር ይቻላል የሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስሜትም ተፈጠረ፡፡ ያ ትንሽ ነገር አልነበረም በቂ ምልክት
ሰጥቷል፡፡ ያን ተከትሎ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ቢወሰዱ ለአገሪቱ በጣም ጥሩ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ያ ሙከራ ቢሳካና ነገሮች በታሰበላቸው አቅጣጫ ሄደው ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ጉዳዩ የመንግሥቱ ነዋይ ብቻ አይመስለኝም፡፡
በውጭ የነበረው ገርማሜ ነዋይ በጣም የተማረ ሰው ነበር፡፡ በውጭ አገር ብዙ ልምድ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም እሱ
የሚከተላቸውና ወደ ግራ የሚያዘሙ ጉዳዮችን በደንብ አልተገነዘብናቸው ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ሙከራው ብዙ
ዝግጅት አልነበረውም፡፡ የተገኘም ሰነድ አልነበረም፡፡ ተጣድፈው ያደረጉት ነበር፡፡ የተጣደፉበት ምክንያትም ይኖር
ይሆናል፡፡ እናም ሳይደርሱብን እንቅደማቸው ዓይነት ነገር ነው፡፡ እኔ ራሴ ገና ወጣት ነበርኩኝና የተሻለ ነገር
በመጠበቅ ምንም ዕውቀቱ ሳይኖረኝ ነበር የጨፈርኩት፡፡ በጃንሆይ በኩል ግን ተገዶ ለውጥ ማምጣት የማይታሰብ ነበር፡፡
ምን ይፈጠር ነበር ለሚለውም ያው ግምት ብቻ ነው፡፡ እናም የ1953 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያልተጠበቀ
ነበር፡፡ ነብይ የነበሩ ሰዎች ያወሩት ካልሆነ በቀር፡፡
ሪፖርተር፡- የኤርትራስ ጉዳይ ምን መልክ ይኖረው ነበር?
አምባሳደር ዘውዴ፡- የኤርትራ ጉዳይ እኮ ቀደም ብሎም ያለቀ ነበር፡፡
የኤርትራ ጉዳይ በፌዴራላዊ ሥርዓት ከተዋቀረ ከአሥር ዓመት በኋላ ለምን ቀረ? ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ
ሳይሆኑ ኤርትራውያኑም ተጠያቂ ናቸው፡፡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ፌዴሬሽኑ አንድነታችንን ያላላዋል ብለው እንደገመቱት
የበኸር ልጅ አደረገን ያሉም ነበሩ፡፡ በትክክል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰጠው ፍርድ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ ጉዳይ በአንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚባለው ኤርትራን ትቶ አሰብን ለኢትዮጵያ የሚሰጥ አካሄድም ነበረው ይባላል፡፡ እንደ ታሪክ ተመራማሪነትዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
አምባሳደር ዘውዴ፡- እኔ ስለዚህ ጉዳይ የምሰጠው ምላሽ በትክክል
አጥንቼ የደረስኩበትንና የነበርኩበትን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል፡፡ ምንም የሚያከራክር አይደለም
ብለው የጮኹና የተከራከሩ የኢትዮጵያ ወዳጆች ብቻ አይደሉም ጠላቶችም ጭምር ነበሩ፡፡ እንደ ሩሲያ፣ ፓኪስታንና
ጣሊያን የመሳሰሉት አገሮች ይህን ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ በተባበሩት መንግሥት ድርጅት
ስብሰባ ላይ በንጉሥ ነገሥቱ ስም የተቃወሙት እኛ ታሪክን ወደነበረበት እንመልስ ብለው ነው፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ
አካል ነች፡፡ የኤርትራ ሕዝብም ኢትዮጵያዊነቱን አምኖ የሚቀበል ነው በማለት ነው፡፡ በመሆኑም ኤርትራ ከነሙሉ አካሏ
ወደ ኢትዮጵያ ትመጣለች የሚል እንጂ የተገነጣጠለ ነገር ማለትም አሰብ ወደ ኢትዮጵያ፣ ቆላው ወደ ሱዳን ምናምን
የሚል አቋም አልነበረም፡፡ አሰብን ማግኘት እኮ ያኔ ለኢትዮጵያ ምንም የሚያስቸግር ነገር አልነበረም፡፡ መጀመሪያም
አሰብ የኤርትራ ግዛት አልነበረም፡፡ በቋንቋውም፣ በግዛቱም ሆነ በአስተዳደሩም አሰብ የኢትዮጵያ አካል ነበር፡፡
አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶችም የፈለጉት ኢትዮጵያ አሰብን ወስዳ ኤርትራ በሞግዚት ወይ ከጣሊያን ጋር፣ ወይ
ከእንግሊዝ ጋር እንደትቀር ነበር፡፡ የኤርትራ ሰዎችም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ብለው ብዙ መከራ የተቀበሉ፣ የሞቱና
የተሰደዱ ናቸው፡፡ ይህን እውነተኛ ታሪክ ስንመለከት ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን እናዝናለን፡፡ ለኢትዮጵያዊነት የታገሉ
እነሱ ናቸው፡፡ እኛ በአደባባይና በዳኝነቱ ታገልን እንጂ መጀመሪያ በአራቱ ኃያላን ኮሚሽን፣ ቀጥሎም በተባበሩት
መንግሥታት ድርጅት በተደረገ ምርመራ ከሰባ በመቶ በላይ ኤርትራውያን ኢትዮጵያዊነትን ደግፈዋል፡፡ በተባበሩት
መንግሥታት ድርጅት የተላኩ መርማሪዎች እኮ የኢትዮጵያ ጠላቶች እነ ፓኪስታን፣ በርማና ደቡብ አፍሪካ እኮ ነበሩ፡፡
ይህም ሆኖ ግን ተቸግረዋል፡፡ እውነቱን መደበቅ አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት አሜሪካ መጣች፡፡ ምን አለ ለዘመናት
አብሮ የኖረውን ሕዝብ ባንለያየው? የኤርትራ ሕዝብ አንድ የሆነ የአስተዳደር መዋቅር ተሠርቶለት ይተዳደር፡፡
ኢትዮጵያም በወደቦቹ እየተገለገለች ትቀጥል የሚል ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ የተበለሻሸውና ችግሩ
የተፈጠረው ፌዴሬሽኑ ሲፈርስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት እንግዲህ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ የአገሪቱ ጉዳይ ሆኖአል፡፡ በዓባይ ጉዳይ ላይ ንጉሡ ምን ዓይነት አቋም እንደነበራቸው ማወቅ ይቻል ይሆን?
አምባሳደር ዘውዴ፡- እኔ በእውነቱ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያጠናሁትም
ሆነ የተዘጋጀሁበት ነገር የለም፡፡ ይሁንና ንጉሡ ኢትዮጵያ የራሷን ውኃ የመጠቀም መብት አላት ይገባታልም ሲሉ ገና
በአልጋ ወራሽነት ጊዜያቸው ጀምሮ ሲጻጻፉ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህን ደግሞ ወደፊት በአግባቡ
እመለከተዋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ እንግዲህ በሦስቱም ተከታታይ መጻሕፍትዎችዎ የንጉሡን ዓውደ ሕይወት ተርከዋል፡፡ ይሁንና ግን ወደ ውዳሴው አድልተዋል ለሚሉ ወቃሽዎች ምን ምላሽ ይኖርዎታል?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ሁሉንም መጻሕፍት የጻፍኩት ከራሴ ጋር ተማምኜና ተዘጋጅቼ ነው፡፡
ችግራቸውንም ገልጬያለሁ፡፡ የእርሳቸውን ትልቅነት ብቻ አሳየን ብለው የሚተቹና የሚሳደቡም አሉ፡፡ ታሪክ ጸሐፊ ተቺ፣
ተሳዳቢ ወይም አሞጋሽ አይደለም፡፡ ታሪክ ጸሐፊ ታሪክን ተመርኩዞ ይጽፋል፡፡ ያልሆነ ነገር ተጻፈ ከተባለ ለመታረም
በሬ ክፍት ነው፡፡ የጻፍኩት ሁሉ ግን በነበረው ሁኔታና ጊዜ ላይ የተሞረኮዘ ነው፡፡ ስለዚህም በተለይ ለወጣቱ
ትውልድ የምለው ያየሁትና ያወቅኩት ይኼ ነው፡፡ ከወቀስኳቸውም እኔ ሳልሆን ታሪኩ ነው፡፡ ከተሞገሱበትም እንዲሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ታሪክ ጸሐፊነትዎ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በደካማም ሆነ በጠንካራ ጎናቸው ቢገልጿቸው? የተለያዩ የውጭ ጸሐፍትም በልዩ ልዩ መንገድ ስለገለጿቸው፡፡
አምባሳደር ዘውዴ፡- አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ትልቅ መሪ ናቸው
ብዬ ነው የምገልጻለቸው፡፡ አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም ለ58 ዓመታት የደከሙ መሪ ናቸው፡፡ አንጀሎ ዴልቦካ የተባለ
የጣሊያን ጸሐፊ ትንሽ ይሞክራል፡፡ ከእኔም ጋር ይነጋገራል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከየትም ለቃቅመው ይጽፋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ በአዲሱ መጽሐፍዎ ሁለት ግለሰቦች የተለየ ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ልክ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች ቀዳማዊ ኃይለ
ሥላሴን እጃቸውን ይዘው የመሩና የመንግሥቱ ፊታውራሪዎች ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀው ጃንሆይ ከዝቅተኛው የኅብረተሰብ
ክፍል የመጡትን ያቀርባሉ፡፡ የሚቀናቀኗቸውንና ላቅ የሚሉባቸውን ለመገዳደር ብለው እነዚህን ሁለት ሰዎች አስጠግተው
ነው የሠሩት፡፡ በጣም ታማኝና አደራ የሚጣልባቸውም ሰዎች ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- የምንሊክ ሥልጣን በቀጥታ ወደ ልጅ ኢያሱ እንዳይተላለፍ የራስ ተፈሪ አሻጥር
እንደነበር የሚገልጹ ሰዎች፣ እርስዎን የራስ ተፈሪ ወገንተኛ በማድረግ የልጅ ኢያሱን ታሪክ አድበስብሰው አልፈውታል
ይላሉ፡፡
አምባሳደር ዘውዴ፡- እኔ ምንም አላድበሰበስኩም፡፡ ልጅ እያሱ
የሥልጣኑን ነገር አላወቁበትም፡፡ እዚህ ሸዋ ሲመክር እሳቸው እዚያ ሐረር ሄደው ይጨፍራሉ፡፡ የጃንሆይ ጠላት ነን
ተቃዋሚ ነን የሚሉ እንደነ በጅሮንድ ተክለ ሐዋሪያትና ራስ እምሩ ያሉ ትልልቅ ሰዎች እንኳን ይህንን ጽፈውታል፡፡
ምን ዓይነት ሰው እንደነበሩና ጊዜያቸውን እንዴት ያሳልፉ እንደነበር ተጽፏል፡፡ የሚወቅሱኝ ካሉ እሺ፡፡ ስለዚህ
ከታላላቆቼ የሰማሁትን ነገር ነው የጻፍኩት፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል የሚሰነዘርብኝን ነገር በይቅርታ አልፈዋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በልጅ ኢያሱ አሟሟት ላይ የተቀነባበሩ ነገሮች እንዳሉ የሚወሩ ሚስጥሮች አሉ፡፡ እርስዎን ይህንን አላገናዘቡም ነው የሚሉዎት፡፡
አምባሳደር ዘውዴ፡- እነዚህን ነገሮች በመረጃነት በጭራሽ
አላገኘሁም፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ እንዲያውም ውጭ አገር ነበርኩ፡፡ እንዲያውም በቦታው የነበሩት ሰዎች ናቸው ይህን
ማለት ካለባቸው የሚሉት፡፡ ልጅ ኢያሱን ሳያውቁ የሚወዱ አሉ፡፡ የሚጠሉ አሉ፡፡ ጃንሆይንም እንዲሁ ሳያውቁ የሚጠሉና
የሚወዱ አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው፡፡ በተጨባጭ መረጃ የሚወቅሱ ካሉ መልካም፡፡ እኔ
ከልጅ ኢያሱ ጋር የሚያገናኘኝ ምንም ጉዳይ የለም፡፡ ልጅ ኢያሱ ለኢትዮጵያ መሪነት ያደረጉት ቁም ነገር የለም፡፡
ይህን ደግሞ እነራስ እምሩ ሳይቀር ጽፈውታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ታዲያ ለጃንሆይ ብለው አልጻፉም፡፡
ሪፖርተር፡- በቫቲካን ሊቀ ጳጳስና በሞሶሎኒ መካከል የነበረውን ግንኙነት አስመልክቶ የጻፉት ጉዳይ ብዙ ተቃውሞ ያስነሳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለዚህ ያለዎት ምላሽ ምንድነው?
አምባሳደር ዘውዴ፡- እኔ ጣሊያን አገር ለሰላሳ አምስት ዓመታት ነው
የኖርኩት፡፡ እኔ የቀሳውስት ቤተሰብ ነኝ፡፡ ኦርቶዶክስ ነኝ፡፡ የአገሬን ጥቅም በምንም መልኩ አሳልፌ አልሰጥም፡፡
የጻፍኩት ነገር የማያሳፍረኝ ነው፡፡ የዘመኑ ጳጳስ ፒዮስ 11ኛ የሙሶሎኒ ደጋፊ አልነበሩም፡፡ ከፍርኃት በስተቀር፡፡
ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት አዋጅ ከማወጁ ከሰላሳ ሦስት ቀናት በፊት አንድ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ይህም
መግለጫ ግዛትን ለማስፋፋት የሚደረግና ግዛትን ለመከላከል የሚደረግ ጦርነት አንድ ዓይነት አይደለም የሚል ነበር፡፡
ስለሆነም ግዛትን ለማስፋፋት የሚደረግ ጦርነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረው በምላሹም ከሙሶሎኒ
የማስጠንቀቂያ ደበዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ ለእኛ የተነገረን ታዲያ የሮም ሊቀ ጳጳስ ሙሶሎኒ ወታደሮቹን በመርከብ ወደ
ኢትዮጵያ ሲልክ እየባረከ ሲሸኝ ነበር ተብሎ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በቂ ጥናት
ተደርጎበታል፡፡ የተባለው ቢሆን ኖሮ የዲፕሎማሲ ግንኙነቱም አይፈጠርም ነበር፡፡ ስለዚህ በጥናቱ ጳጳሱ ሳይሆኑ
አንዳንድ ፋሽስት ቄሶች ይህንን አድርገዋል፡፡ የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ግን ይህን አላደረጉም ብዬአለሁ፡፡
ይኼ ደግሞ ውሸት አይደለም፡፡ ጦሩን ባርከው አልሸኙም፡፡ አላደረጉም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ግፍ
ተሠርቷል፡፡ ወንጀል ነው ብለው መስቀላቸውን ከፍ አድርገው አልተቃወሙም፡፡ ይኼን ደግሞ ጽፌያለሁ፡፡ ስለዚህ ጳጳሱ
ጎድተውናልም ጠቅመውናልም አላልኩም፡፡ ይህንን የሚሞግቱ ከዚህ የተሻለ ሐሳብና ማስረጃ ካለ ያቅርቡና የማልታረምበት
ምክንያት የለም ብዬ ነበር፡፡ ማስረጃ ከማምጣትና ከመከራከር ይልቅ ስድባቸውን ቀጠሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ ቫቲካን ለዚህስ ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ የለባትም? በስማቸው በፋሺስት ጣሊያን አዲስ አበባ መንገድ የተሰየመላቸው የካርዲናል ማሳያ ጉዳይስ?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ይቅርታ መጠየቅ የለባትም አላልኩም፡፡ እኔ
በጊዜው የነበሩትን ፒዮስን አስመልክቶ የተነገረውን የተዛባ ወሬ ነው ለማጥናትና ለማረጋገጥ የፈለግኩት፡፡ ጣሊያን
ኢትዮጵያን ያዘች ሲባል ለመጀመሪያ ጊዜ እንኳን ደስ ያለን ብለው ደስታቸውን የገለጹት እሳቸው እንደሆኑ ስለተነገረ
ነው ያጣራሁት፡፡ የፒዮስና የማሳያን ትስስር ደግሞ እኔ አላውቅም፡፡ መንገድ የተሰየመላቸው ካርዲናል ማሳያን እኔ
አላውቃቸውም፡፡ ስለሳቸውም ያልኩት ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- የሦስተኛው መጽሐፍዎ ዋጋ 450 ብር ነው፡፡ አልተወደደም?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ኧረ እባካችሁ!... እኔ በምንም ዓይነት ሁኔታ
ከ300 ብር እንዳያልፍ ነበር የተዋዋልኩት፡፡ እንዲህ ከሆነ ውሉን አፈርሳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በስፋት
እንዲዳረስ ነው የምፈልገው፡፡ አሁን የታተመው አምስት ሺሕ ያህል ቅጂ ስላለቀ በእሱ ላይ መነጋገር አልችል
ይሆናል፡፡ በሚቀጥለው ግን ይኼ አይሆንም፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በአገራችን በርካታ የታሪክ መጻሕፍት እየተጻፉ ለገበያ እየቀረቡ ነው፡፡ አነጋጋሪ፣ አከራካሪና አወዛጋቢ የሆኑም አሉ፡፡ ለመሆኑ የታሪክ መጻሕፍት እንዴት ነው መጻፍ ያለባቸው?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ታሪክ እንደነበረው በማስረጃ ተደግፎ መጻፍ
አለበት፡፡ በስሚ ስሚ ከየትም የሚለቃቀሙ ታሪኮች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡ አንዳንዱ የጻፈውን እንኳን
ማስረዳት አይችልም፡፡ ስለዚህ አሁን የተጀመረው ሁኔታ ወደፊት አገራችንን ብዙ የሚያተራምስ ነው ብዬ እሰጋለሁ፡፡
አንድ ምሳሌ ላንሳ የወልደ ጊዮርጊስንና የሀብተ ወልዶችን ጉዳይ ነው፡፡ ወልደ ጊዮርጊስ የእኔ ቤተሰቦች ጠላት
ነው፡፡ ይሁንና ግን ታሪኩን ስጽፍ የነበረውን ያንኑ ነው፡፡ አልቀንስም አልጨምርም፡፡ ዘመዶቻቸው ሁሉ ያልጠበቁት
ነገር በመሆኑ ምሥጋና ሁሉ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ስለጣሊያንና ስለኢትዮጵያ ብጽፍ ሌላ ጉዳይ በመሆኑ የአገሬን ጉዳይ
አስቀድም ይሆናል፡፡ እኛው ለእኛ ግን እውነቱን ነው ማሳየት ያለብን፡፡ አሁን ያለው አሳሳቢ ችግር መቀየር
አለበት፡፡ አስጊ ነው፡፡ በእርግጥ ይኼንንም ማጣራት እየተጀመረ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከጃንሆይ ጋር የተለየ ቅርበት እንደነበረዎት ይነገራል፡፡ ለምን ነበር?
አምባሳደር ዘውዴ፡- ምንም የተለየ ቅርበት አልነበረንም፡፡ በልጅነቴ ነው የማውቃቸው፡፡ ምናልባት ጋዜጠኛ ሆኜ ሥሠራ አማርኛዬን ይወዱት ነበር፡፡ ከዚህ የተለየ ቅርበት የለንም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment